ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኬንያ ውስጥ በስፋት እየተዛመተ ያለ የተለየ ዝርያ ያለው የጨብጥ በሽታ ተገኘ
የኬንያ የሕክምና ምርምር ተቋም (ኬምሪ) አጥኚዎች በመዲናዋ ናይሮቢ በስፋት እየተዛመት ያለ አዲስ የጨብጥ ዝርያ መለየታቸውን አስታወቁ።
አጥኚዎቹ ይህ በሽታውን ለማከም ጥቅም ላይ የሚለውን ፀረ ተህዋሲ መድኃኒትን (አንቲባዮቲክ) መቋቋም ይችላል ያሉት ዝርያ በተለይ በሴተኛ አዳሪዎች ላይ በስፋት እየታየ ነው።
ተመራማሪዎቹ ይህ የተለየ ዝርያ ያለው የጨብጥ በሽታ በስፋት እንዲዛመት ቀዳሚው ምክንያት የተሳሳተ መረጃ ነው ይላሉ።
እንደ ባለሙያዎቹ ከሆነ በየዕለቱ የፀረ ኤችአይቪ ህክምና እንክብሎችን የሚወስዱ ሴተኛ አዳሪዎች መድኃኒቱ ሌሎች በልቅ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን እንደሚከላከልላቸው የተሳሳተ ዕምነት አላቸው።
ይህ አዲስ የጨብጥ ዝርያው መስፋፋትን ያመለከተው ጥናት ላይ 350 ሴተኛ አዳሪዎች ተሳትፎ ማድረጋቸውን የምርምር ተቋሙ (ኬምሪ) ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሴቶች የተሻለ ክፍያ ለማግኘት ሲሉ ከደንበኞቻቸው ጋር ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል በሁለት ሳምንታት ውስጥ ከተለያዩ 29 ሰዎች ጋር ወሲብ መፈጸማቸውን የገለጹም ይገኙበታል።
አጥኚዎቹ የኬንያ መንግሥት ለበሽታው ትኩረት እንዲሰጥ እና የበሽታውን የስርጭት መጠን በትክክል ለመረዳት ሰፊ ጥናት እና ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በመላው ዓለም ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት በስፋት ከሚተላለፉ በሽታዎች መካከል አንዱ ጨብጥ ነው።
በዓለም ላይ በየዓመቱ 80 ሚሊዮን ሰዎች በጨብጥ በሽታ መያዛቸውን ሪፖርት ይደረጋሉ።
የጨብጥ በሽታ ምንድነው?
- በሽታው የሚከሰተው ኔሴሪያ ጎኖሪያ በተባለ ባክቴሪያ አማካይነት ነው
- ጨብጥ በመራቢያ አካል እና ከመራቢያ አካል ውጪ በሚደረጉ ልቅ የወሲብ ግንኙነት ይተላለፋል
- በበሽታው ከሚያዙ 10 ወንዶች አንዱ እንዲሁም ከ10 ሴቶች ሦስቱ በቀላሉ የሚለይ የበሽታ ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ።
- ከምልክቶቹ መካከል አረንጓዴ ወይም ቢጫ ፈሳሽ ከብልት መውጣት፣ ሽንት ሲሸና የህመም ስሜት መሰማት እንዲሁም በሴቶች የወረ አበባ መካከል የደም መፍሰስ ዋነኞቹ ናቸው።
- የሕክምና ክትትል ካልተደረገ የጨብጥ በሽታ በታማሚውን ላይ መካንነት ሊያስከትል ይችላል።
- በሴቶች ላይ የመራቢያ አካል መቆጣትን ያስከትላል እንዲሁም በእርግዝና ወቅት በሽታው ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፍ ይችላል።