የሶማሊያ ወታደሮች የአል-ሻባብ ታጣቂዎችን ከበባ ጥሰው ማዘጋጃ ቤቱን ተቆጣጠሩ

የሶማሊያ ወታደሮች የአል-ሻባብ ታጣቂዎች ለአምስት ሰዓታት የቆየ ከበባን ሰብረው ማዘጋጃ ቤት መግባታቸውን የሶማሊያ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

የሶማሊያ ኮማንዶዎች በመዲናዋ ሞቃዲሾ የሚገኘው ማዘጋጃ ቤትን ለአምስት ሰዓታት ይዘው የቆዩትን የአል-ሻባብ ታጣቂዎች ጥሰው ትናንት እሑድ ጥር 14/2015 ዓ.ም. እንደገቡ ተገልጿል።

በኦፕሬሽኑ ወቅት አምስት ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውም ተገልጿል።

ታጣቂዎቹ ጥቃት የከፈቱት ማዘጋጃ ቤቱ በር ላይ በመኪና ቦምብ በማፈንዳት ሲሆን፣ የሶማሊያ ወታደሮች እንደሆኑ በማስመሰል ቅጥር ግቢውን ጥሰው ገብተዋል።

የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዳለው፣ የሶማሊያ ወታደሮች የመንግሥት ሠራተኞችን በአጠቃላይ ማዳን ችለዋል።

ስድስት ታጣቂዎችን እንደገደሉም ተገልጿል።

ከአል-ሻባብ ጋር ቁርኝት ያላቸው ሚዲያዎች የቡድኑን ቃል አቀባይ ጠቅሰው “34 ከሃዲዎች” በጥቃቱ መገደላቸውን ገልጸዋል።

ይህ አገላለጽ እስላማዊ አክራሪ ታጣቂ ቡድኑ መንግሥትን የሚጠራበት ሲሆን፣ የሶማሊያ መንግሥት ቡድኑን ጽንፈኛ ሲል ይጠራዋል።

የሞቃዲሹ ከንቲባ ዩሱፍ ሑሴን ጂማሌ ጥቃቱ ሲፈጸም ከአገር ውጭ ነበሩ።

እአአ በ2019 ቡድኑ ማዘጋጃ ቤቱ ላይ ባደረሰው ጥቃት የከተማው ከንቲባ የነበሩት አብዲራህማን ኦማር ኦስማን መገደላቸው ይታወሳል።

የሶማሊያ መንግሥት ሶና ለተባለው መገናኛ ብዙኃን በሰጠው ቃል፣ የአል-ሻባብ ሰሞነኛ “ትርጉም አልባ” ነውጥ “ቡድኑ ከአገር መወገድ እንዳለበት ማሳያ” ነው ብሏል።

በቅርብ ወራት ቡድኑ ቁልፍ ቦታዎችን በሶማሊያ ብሔራዊ ወታደሮች እና አጋር የሆኑ የጎሳ ሚሊሻዎች ቢነጠቅም አሁንም መንግሥት ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅም እንዳለው ማሳያ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ባለፈው ሳምንት መንግሥታቸው ያለፈው ነሐሴ ላይ የጀመረው አል-ሻባብ ላይ የሚያደርሰው “የመጀመሪያ ዙር እርምጃ ሊጠናቀቅ መቃረቡን” ገልጸው ነበር። አያይዘውም በቅርቡ የዚህ እርምጃ “ሁለተኛ ዙር” እንደሚጀመር ተናግረዋል።