በአሜሪካ 10 ሰዎችን ገድሎ በርካቶችን ያቆሰለው ግለሰብ ሞቶ ተገኘ

የካሊፎርኒያ ፖሊስ ሎስ አንጀለስ ውስጥ ጥቃት ፈጽሞ 10 ሰዎችን የገደለው የ72 ዓመት አዛውንት በአንድ መኪና ውስጥ ሞቶ እንዳገኘው አስታወቀ።

ግለሰቡ በቆመ መኪና ውስጥ እራሱ በጥይት ከመታ በኋላ እዚያው ሞቶ እንደተገኘ የሎስ አንጀለስ አካባቢ ፖሊስ ሮበርት ሉና ይፋ አድርገዋል።

በርካታ ትውልዳቸው ከእስያ አገራት የሆኑ ማኅበረሰቦች ባሉባት ሞንቴሬይ ፓርክ በምትባለው ከተማ ውስጥ የቻይናውያን እና የሌሎች የእስያ አገራት የአዲስ ዓመትን የሚያከብሩ ሰዎች በተሰባሰቡበት ስፍራ ነበር ጥቃቱ የተፈጸመው።

ግለሰቡ በርካታ ሰዎችን ለገደለበት እና ላቆሰለበት ጥቃት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ፖሊስ አስካሁን ያወቀው ነገር የለም።

ከተገደሉት 10 ሰዎች በተጨማሪ 10 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን፣ ሰባቱ አሁንም ሆስፒታል ውስጥ ይገኛሉ። ከመካከላቸው አንዳንዶቹ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ እንዳለው በጥቃቱ የተገደሉትን 10 ሰዎች ማንነት ለማወቅ እየጣረ ሲሆን፣ “ምናልባትም በ50ዎቹ፣ በ60ዎቹ አንዳንዶቹ ደግሞ ከዚያም በላይ በሆነ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።”

ባለሥልጣናት ቀደም ብለው በሰጡት መረጃ የተገደሉት አምስት ሴቶች እና አምስት ወንዶች መሆናቸውን ገልጸው፣ “ምናልባትም የእስያ ዝርያ ያላቸው ሳይሆኑ አይቀሩም” ተብሏል።

በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ እጅግ የከፋው ነው የተባለው ይህ የጅምላ ግድያ ቅዳሜ ሌሊት ከሎስ አንጀለስ በስተምሥራቅ 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሞንቴሬይ ፓርክ ውስጥ የተፈጸመ ነው።

ከዚያም ከ30 ደቂቃ በኋላ ጥቃት ፈጻሚው ታጣቂ ከሞንቴሬይ ፓርክ በቀርብ ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው አልሃምብራ ወደ ተባለች ከተማ ሄዶ ወደ አንድ ጭፈራ ቤት ገብቶ እንደነበር ተዘግቧል።

እዚያም ሁለት ሰዎች ግለሰቡን ተናንቀውት በመያዝ የታጠቀውን መሳሪያ አስጥለውታል፤ ነገር ግን አምልጧቸው ሄዷል።

ፖሊስ እንደሚያምነው ግለሰቡ የታጠቃቸው የጦር መሳሪያዎች በካሊፎርኒያ ውስጥ ሕገ ወጥ መሆናቸውን እና ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልገው ገልጿል።

ጥቃት ፈጻሚው ነው የተባለው ግለሰብ ሞቶ ከመገኘቱ በፊት ፖሊሶች የሎስ አንጀለስ አካባቢዎችን ለሰዓታት ሲያስሱ ቆይተዋል።

ከጥቃቱ 12 ሰዓታት በኋላ ከሞንቴሬይ ፓርክ ከተማ 48 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ልዩ የፖሊስ ኃይል አባላት ነጭ መኪና አግኝተው በመክበብ ባደረጉት ፍተሻ ግለሰቡን አግኝተውታል።

ፖሊሶቹ መኪናዋን እየተጠጉ በነበረበት ጊዜ አንድ የጥይት ተኩስ የሰሙ ሲሆን፣ ወደ መኪና ውስጥ ሲመለከቱ ተጠርጣሪው ከመኪናው መሪ ላይ ተደፍቶ አግኝተውታል። ግለሰቡ ጥቃት ፈጻሚው እንደሆነ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ አብሮት ሽጉጥ ተገኝቷል።

ፖሊስ እንዳለው ሲጠቀምበት የነበረው መኪና የሰሌዳ ቁጥር የተሰረቀ ሳይሆን እንዳልሆነ ገምቶ፣ ግለሰቡ ጥቃቱን የፈጸመው ብቻውን እንደሆነ እና ሌላ ተጠርጣሪ የለም ብሏል።

በሞንቴሬይ ፓርክ ከተማ ውስጥ ካለው ሕዝብ 65 በመቶ የሚሆኑት ትውልደ እስያውያን የአሜሪካ ዜጎች ናቸው። በዚህም በዋናው የአሜሪካ መሬት ላይ አብዛኛው የአስያ ዝርያ ያላቸው ነዋሪዎች የሚገኙበት የመጀመሪያው ከተማ ሆኗል።

እሁድ ዕለት የተጀመረውን የቻይና አዲስ ዓመትን በማስመልከት የተዘጋጀው ክብረ በዓል ጥቃቱን ተከትሎ እንደሰረዝ ተደርጓል። በንግድ ተቋማት እና በከተማዋ መንገዶች ላይ ለአዲስ ዓመት የተሰቀሉ ጌጣ ጌጦች በሐዘን ምክንያት እየተነሱ ነው።