ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያዋን ጥቁር ፕሬዝዳንት ሾመ

ሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያዋን ጥቁር ፕሬዝዳንት ሾመ።

ዶ/ር ክላውዲን ጌይ ዩኒቨርስቲውን በመምራት የመጀመሪያዋ ጥቁር ሰው ሲሆኑ፣ ዩኒቨርስቲውን በመምራት ሁለተኛዋ ሴትም ናቸው።

ሹመቱ የዴሞክራሲ ምሑሯን ዶ/ር ክላውዲን 30ኛዋ የሐርቫርድ ፕሬዝዳንት ያደርጋቸዋል።

ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ሎውረንስ ባኮው ነው ኃላፊነቱን የሚረከቡት።

እአአ በ2023 ትልቅ ዩኒቨርስቲ በመምራት ብቸኛዋ ጥቁር ሲሆኑ፣ ከኮሌጆቹ አንዱን በመምራት ደግሞ ሁለተኛዋ ጥቁር ሴት ናቸው።

የሐርቫርድ ፕሬዝዳንት ቅጥር ኮሚቴ ሊቀ መንበር የሆኑት ፔኒ ፕሪዝከር “ዶ/ር ክላውዲን የሰላ ሐሳብ በመሰንዘር፣ አካታችነትን በማረጋገጥ፣ ተቋማዊ የእድገት ተስፋ በመሰነቅና ትህትና በመላበስ ነው ኃላፊነቱን ያገኙት” ብለዋል።

ዶ/ር ክላውዲን ኃላፊነቱ ሲሰጣቸው “እውነት አይመስልም አይደል? በጣም ሐሴት ይሰማኛል። ‘የማይሰበር የልሂቃን ስብስብ’ የሚለው አስተሳሰብ ያረጀ፣ ያፈጀ ነው። ሁላችንም የከፍታው አካል ነን” በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።

ሐርቫርድ ማኅበረሰቡን የማገልገልና አካታችነትን የማስፈን ኃላፊነት እንደተጣለበትም አክለዋል።

ከሄይቲ ስደተኛ ቤተሰቦች የተወለዱት ዶ/ር ክላውዲን እአአ በ1992 በስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ ነው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት።

በ1998 ዶክትሬታቸውን ከሐርቫርድ አግኝተዋል።

በፖለቲካ ሳይንስ ምርጡን መመረቂያ ጽሑፍ በመሥራት የቶፐን ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

በ2006 የሐርቫርድ አስተደዳር ትምህርት ክፍል መምህርት ሆነው ከገቡ በኋላ በ2007 የአፍሪካ እና የአፍሪካ-አሜሪካ መምህርት ሆነዋል።

ጥናቶቻቸው የአሜሪካ የዘር እና ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ።

ሐርቫርድ ቅበላ የሚያደርግበትን ሂደት (በተለይም ከዘር ጋር በተያያዘ) እንዲከልስ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩ እየታየ ባለበት ወቅት ነው የዶ/ር ክላውዲን ሹመት የተሰማው።