የኤኳዋዶሩ ፕሬዘደንት በታጠቁ ነውጠኛ የዕፅ አዛዋዋሪ ቡድኖች ላይ ጦርነት አወጁ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኤኳዎዶሩ ፕሬዝደንት የታጠቁ ዕፅ አዘዋዋሪዎች አንድ የተሌቪዥን ጣቢያን ካጠቁ በኋላ ቡድኖቹ ላይ ጦርነት አወጁ።
የፊት ጭምብል የለበሱ ታጣቂዎች ቲሲ ወደተሰኘ አንድ የመንግሥት ቴሌቪዠን ዘልቀው ገብተው የቀጥታ ሥርጭት ላይ የነበሩ ሠራተኞች መሬት አስተኝተዋል።
በጥቃቱ ሁለት ሠራተኞች ጉዳት ሲደርስባቸው 13 ታጣቂዎች ደግሞ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ኤኳዎዶር ባለፈው ሰኞ ለ60 ቀናት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጣች በኋላ በተነሳ ግርግር ቢያንስ 10 ሰዎች ተገድለዋል።
ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀችው አንድ ነውጠኛ የዕፅ አዋዋሪ ቡድን መሪ ከእሥር ቤት ከጠፋ በኋላ ነው።
በቅፅል ስሙ ፊቶ እየተባለ የሚጠራው የቼኖሮስ ነውጠኛ ቡድን መሪ አዶልፎ ቪላማር የቴሌቪዥን ጣቢያው በሚገኝበት ከተማ ነው ከእሥር ቤት ደብዛው የጠፋው።
ፕሬዘደንት ኖቦዋ ማክሰኞ ዕለት በሀገሪቱ ባለው “የታጣቂዎች ግጭት” ምክንያት መከለካያ ሠራዊቱ “ወታደራዊ እርምጃ” እንዲወስድ አዘዋል።
ፕሬዝደንቱ ነውጠኛ ቡድኖቹን “የተደራጁ ወንጀለኞች፣ ሽብርተኛ ቡድኖች እና አደገኛ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ” ኢሰሉ ገልጠዋቸዋል።
ጎረቤት ሀገር ፔሩ ደግሞ የነውጠኛ ዕፅ አዘዋዋሪ አባላት ዘልቀው እንዳይገቡ የፖሊስ ኃይል ወደ ድንበር እንዲሰማራ አዛለች።
ዩናይትድ ስቴትስ በኤኳዋዶር የተሰነዘረውን “ጥቃት” አውግዛ ከፕሬዝደንት ዳኒኤል ኖቦዋ መንግሥት ጋር “በቅርበት” እየሠራች፤ እንዲሁም “አስፈላጊውን እርዳታ ለማቅረብ” ዝግጁ መሆኗን አሳውቃለች።
ኤኳዶር የዓለማችን ቁጥር አንድ የሙዝ አከፋፋይ ስትሆን፣ ነዳጅ፣ ቡና፣ ኮኮዋ፣ ሽሪምፕ እና ሌሎችም የዓሳ ምርቶችንም ወደ ውጭ ትልካለች።
ኮኬይን ወደ አሜሪካ እና አውሮፓ የሚሉ ዕፅ ሀገር ቤት ከሀገር ውጭ ያሉ አዘዋዋሪዎች በሀገሪቱ ነውጥ በመፍጠር ላይ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ትናንት ማክሰኞ በቴሌቪዥን ስቱዲዮ በነበረው እገታና ጥቃት አንድ ጭምብል የለበሰ ታጣቂ ሽጉጥ በጋዜጠኛ ላይ ደግኖ ይታይ ነበር።
ሌላ ታጣቂ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ጣልቃ እንዳይገቡ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ ቅረጹኝ እያለ ሲጠይቅ ነበር።
ሌላ ሴት ደግሞ “እባካችሁ አትተኩሱ’ እያለች ስትማጸን በቀጥታ ተላልፏል።
አንድ ሌላ የቴሌቪዥን ሠራተኛ ለኤኤፍፒ በዋትስአፕ ባሾለከው መረጃ “ሊገደሉን መጥተዋል። እዚህ ስቱዲዮ ነው ያሉት። ፈጣሪ ሆይ አድነን። ወንጀለⶉቹ በቀጥታ ሥርጭት ላይ ናቸው” ሲል መልእክት ልኮ ነበር።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአገሪቱ እስር ቤቶች ውስጥ የአደገኛ እጽ አዘዋዋሪ አደገኛ ቦዘኔዎች አስነሱት በተባለ ነውጥ በርካቶች ተገድለዋል።
ነውጦቹ ብዙውን ጊዜ በአደገኛ እጽ ቡድኖች መካከል የሚነሱ ናቸው።
ኮኔሮስ የሚባለውና የኢኳዶር አደገኛ የእጽ አዘዋዋሪ ቡድን እንደሆነ የሚነገርለት ኃይል በአገሪቱ ለሚነሱ አመጾች ዋንኛው ተጠያቂ ይደረጋል።
ፊቶ በሚል ስም የሚታወቀው የቡድኑ አደገኛና ሞገደኛ መሪ ጥብቅ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት ማምለጡን ተከትሎ ሁለት የከርቸሌው ጠባቂዎች ምናልባት እንዲያመልጥ ሳይረዱት አይቀሩም በሚል በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
የፊቶ ማምለጥ ለወጣቱና አዲሱ ፕሬዝዳንት መጥፎ ዜና ሆኗል።
ፕሬዝዳንቱ በኢኳዶር የአደገኛ እጽ ሰንሰለትን እበጣጥሳለሁ ብለው ቃል ገብተው ነበር በቅርብ ጊዜ ወደ ሥልጣን የመጡት።
በዚህ የፕሬዝዳንቱ ምርጫ እጩ የነበሩትና ከፍተኛ የማሸነፍ ግምት የተሰጣቸው ፈርናንዶ ቪላቪሴንሲዮ በታጣቂ መገደላቸው አይዘነጋም።
ፈርናንዶ ቪላቪሴንሲዮ ከዚህ ፊቶ ከሚባለው ሞገደኛ አደገኛ ቦዘኔ የሞት ዛቻ በደረሳቸው በማግስቱ ነበር የተገደሉት።
ኢኳዶር በደቡብ አሜሪካ የምትገኝና ፔሩና ኮሎምቢያን የምትጎራበት አገር ስትሆን ሕዝቧ 17 ሚሊዮን ይጠጋል።












