ቻይና የኮቪድ ፖሊሲ ተቺዎችን የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶች አገደች

ቻይና የመንግሥትን የኮቪድ ፖሊሲዎች የሚተቹ ከአንድ ሺህ በላይ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን (ገጾችን) አገደች። ከአካውንቶቹ መካከል የተወሰኑት በሚሊየን የሚቆጠሩ ተከታዮች አላቸው።

የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ ዌቦ፣ በቻይና የኮቪድ ባለሙያዎች ላይ "ግላዊ ጥቃት" ፈፅመዋል ያላቸውን አካውንቶች ማገዱን ገልጿል።

ይሁን እንጂ ዌቦ የትኞቹ ጽሑፎች ለእርምጃው እንዳነሳሳው አልገለጸም።

ቻይና ጥላው የነበረውን ጥብቅ የዜሮ ኮቪድ ፖሊሲዋን ታኅሥሣ ወር ላይ ያነሳች ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በወረርሽኙ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሰዎች ለሳምንታት ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩ የሚያደርገው የእንቅስቃሴ ገደብን ጨምሮ ጥብቅ የሆነው የኮቪድ ወረርሽኝ ቁጥጥር ላይ ያነጣጠሩ ትችቶች በኢንተርኔት አማካይነት ሲሰጡ ነበር።

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች ግን ትኩረት ያደረጉት ገደቦችን ለማንሳት የተላለፉ ድንገተኛ ውሳኔዎችን ሲቃወሙ በነበሩ ባለሙያዎች ላይ ነው።

ዌቦ በባለሙያዎች፣ ምሁራን እና የሕክምና ባለሙያዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን ጨምሮ 13 ሺህ የሚሆኑ ጥሰቶችን ለይቻለሁ ብሏል። ከእነዚህ መካከልም 1ሺህ 120 የሚሆኑ ገጾችን በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት እንዲታገዱ ወስኗል።

ዌቦ ባወጣው መግለጫ “የተለያየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች መስደብ አሊያም ግለሰብ ላይ ያነጣጠሩ እና ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ጽሑፎችን ማተም ተቀባይነት የለውም” ብሏል።

"በዌቦ ማኅበረሰብ ላይ ማንኛውም አጥፊ የሆነ እንቅስቃሴን እንደ ቀልድ አልመለከትም” ብሏል በመግለጫው።

ቻይና በኮቪድ ፖሊሲዋ ላይ የተቀሰቀሰ ታሪካዊ የተባለውን ተቃውሞ ተከተሎ ቁልፍ የሆኑ የዜሮ ኮቪድ ፖሊሲዎቿን ከተወች ጀምሮ ሆስፒታሎች እና የአስክሬን ክፍሎች መጨናነቃቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች እየወጡ ነው።

ነገር ግን ቻይና ዕለታዊ የኮቪድ ሪፖርቶችን ማውጣት አቁማለች። የራሷን መስፈርት በመጠቀምም ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ የተመዘገበው የኮቪድ ሞት 22 ብቻ መሆኑን አስታውቃለች።

ቅዳሜ ዕለት ቻይና የ40 ቀናት ሉናር አዲስ ዓመትን የመጀመሪያ ቀን አክብራለች።

ሉናር የቻይናውያን አዲስ ዓመት ሲሆን በድምቀት የሚከበር በዓል ነው። ይህ በዓል በዓለማችን በርካታ ሰዎች ጉዞ የሚያደርጉበት ወቅት ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዓሉን ለማክበር ወደ አገራቸው ይገባሉ።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር በሚቀጥሉት አርባ ቀናት ከ2 ቢሊየን በላይ መንገደኞች ይጓዛሉ ብሎ እንደሚጠበቅም ገልጿል።

ነገር ግን በዓሉ በተለይም በቂ የሕክምና ቁሳቁስ፣ የጽኑ ህሙማን አልጋ እና ኦክስጅን በሌለባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ወረርሽኙን ሊያዛምት እና የከፋ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ቻይና ከእሁድ ጀምሮ ከውጭ ወደ ቻይና ለሚገቡ መንገደኞች ራሳቸውን እንዲያገሉ ጥላው የነበረውን ገደብ ታነሳለች ተብሏል። በመሆኑም በርካታ ቻይናውያን ከሦስት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገራቸው ያለገደብ ሊጓዙ ይችላሉ።