የበዓል ዕቅዳቸው እንዳይስተጓጎል ሆን ብለው ራሳቸውን በኮቪድ የሚያስያዙት የቻይና ወጣቶች

ቼን 85 ዓመታቸው ነው። ባለፈው ወር በኮቪድ-19 ተያዙና ደከሙ። ነገር ግን አምቡላንስ መጥራትም፤ አልጋ ማግኘትም የሚታሰብ አልሆነም።

ሲጨንቅ ወደ ቤጂንግ ቻዎያንግ ሆስፒታል ሄዱ። በዚያ “አልጋ የለም፤ ሌላ ቦታ ይሞክሩ” ተባሉ።

ሌላው አማራጭ እዚያው ሆስፒታል ኮሪደር ላይ ተኝተው መታከም ነበር። ለዚያውም በኮሪደር ላይ ቦታ ከተገኘ ነው።

በኮቪድ በሽተኛ መተላለፊያው ተጥለቅልቋል። ሰው በሰው ላይ ነው ተኝቶ ያለው።

አሁን በቻይና ተህዋሲው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ተሰግቷል።

በተለይ ቻይና በኮቪድ ላይ የነበራትን ጥብቅ አቋም ካላላች በኋላ ነገሮች እየከፉ ይመስላል።

ይሁንና ቻይና ነገሮች አልከፉም፤ ሚዲያው የሚያራግበው የፖለቲካ አጀንዳ ነው ትላለች።

በኮቪድ-19 የሞቱብኝ ሰዎች በመቶ የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው ትላለች።

ቻይና ይህን ትበል እንጂ ኤየርፊኒቲ የተባለ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሳይንስ ጥናት ኩባንያ ግን በቻይና አሁን 2 ሚሊዮን ሰዎች በተህዋሲው ተይዘዋል ይላል።

በየቀኑ በወረርሽኙ ሰበብ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ14ሺህ ቢበልጡ እንጂ አያንሱም ነው የሚለው።

የዓለም ጤና ድርጅት ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ የቻይና ቁጥር የማሳነስ ነገር አሳስቦኛል ብሎ ነበር።

ቻይና ለሦስት ዓመታት በኮቪድ ላይ ያደረገችው ጥብቅ ክትትል ከንቱ ነበር ይላሉ ተንታኞች።

ምክንያቱም ሁሉንም ገደብ ድንገት እና በአንድ ጊዜ ማንሳቷ ከዚህ ቀደም የሠራችውን ሥራ ሁሉ ከንቱ ያደርገዋል።

አሁን በቻይና ኮቪድ ነገሮችን እያመሰቃቀለ ነው። አገሮች ከቻይና ለሚመጡ ተጓዦች ጤንነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እየጠየቁ ነው።

በበሽታው የመያዝ ፍላጎት ለምን?

ከዚህ ሁሉ ጭንቅ በበሽታው ተይዞ ነገሩን ማለፍ ይሻላል ያሉ ወጣቶችም ተከስተዋል።

ለቢቢሲ ስማቸውን ሳይገልጹ ሐሳባቸውን የተናገሩ ወጣቶች በገዛ ፈቃዳቸው ተህዋሲው እንዲይዛቸው እያደረጉ ነው።

የ27 ዓመቱ ስሙን ያልገለጸ የኮምፒውተር አዋቂ አንዱንም የኮቪድ መከላከያ ክትባት የቻይና ክትባትን አልወሰደም።

በቅርቡ በገዛ ፈቃዱ ራሱን በተህዋሲው አስጠቅቷል።

ይህን ያደረገው ለምን እንደሆነ ሲጠየቅ የአዲስ ዓመት እቅዴ እንዳይበላሽብኝ ነው ይላል።

ይህን ሲያብራራ በራሴ ጊዜ በተህዋሲው ተይዤ፣ ቶሎ ከበሽታው አገግሜ በዓሉን በሰላም ያለ ሥጋት ለማሳለፍ ካለኝ ቁርጠኝነት የተነሳ ነው ይህን እርምጃ የወሰድኩት ብሏል።

ራሱን በተህዋሲው ካስጠቃ በኋላ ግን ካሰበው በባሰ ታመመ።

“እውነት ለመናገር የጡንቻ ህመሙን አላሰብኩት ነበር” ይላል።

ከዚያ ባሻገር ግን ህመሙ እና የበሽታው ምልክቶቹ እንደጠበቀው ነው ያገኛቸው።

የቻይና አዲስ ዓመት አብዛኛው የአገሪቱ ዜጋ በጉጉት የሚጠበቅ እና በታላቅ ደስታ ከቤተሰቡ ጋር የሚያከብረው ታላቅ በዓል ነው።

የቻይና አዲስ ዓመት ከሁለት ሳምንት በኋላ ጥር 14/2015 ዓ.ም. ይገባል። ለዚህም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተበተኑት ይሰባሰባሉ።

ከእዚያው ከቻይና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚያቀኑበት ነው።

ስለዚህም በክብረ በዓሉ ላይ ከቤተሰብ፣ ከወዳጅ እና ከዘመድ ጋር በዓሉን በደስታ ለማክበር ሁሉም ቀድሞ ያቅዳል፣ ቀድሞ ጉዞ ይጀምራል።

ሌላ የ26 ዓመት የሻንጋይ ነዋሪ ወጣት ቢቢሲ ስሟን እንዲጠቅሰው አልፈቀደችም።

በተህዋሲው የተያዘች ጓደኛዋ ዘንድ ሆን ብላ በመሄድ ነው። ኮቪድ እንዲይዘኝ ፈልጌ እና ፈቅጄ ነው ቤቷ የሄድኩት ትላለች።

ከተያዘች በኋላ ግን በሽታው እንደጸናባት አምናለች።

“እኔ ያሰብኩት ከጉንፋን ትንሽ ከፍ ያለ ህመም ነበር። አለመታደል ሆኖ ብዙ ተሰቃየሁ” ብላለች።

የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱ በሽታውን አባባሰው?

የ29 ዓመቷ የዣይሺንግ ነዋሪ ለቢቢሲ ስትናገር የቻይና መንግሥት ድንበሮች በሙሉ ይከፈቱ፣ እንቅስቃሴ ገደቡ ይነሳ ብሎ ሲያዝ ደስተኛ ነበርኩ ትላለች።

ወደ ሌሎች የቻይና ግዛቶች ለመጓዝና ዘመድ ቤተሰብ ለመጠየቅ መጓጓቷንም ገልጣለች።

ቀደም ሲል ግን ለእያንዳንዱ ጉዞዬ አለቃዬን አስፈቅጄ መሆን ስለነበረበት ደስተኛ አልነበርኩም ብላለች።

“ይሁን እና ገደቡ መነሳቱ ነገሮችን ቀላል አድርጎልኛል።”

ነገሮች ለእርሷ ቀላል የሆኑ ቢሆንም በዕድሜ ለገፉት ግን ፈተና እንደሚሆን አላጣችውም።

“ሽማግሌዎችን ሳስብ ያስጨንቀኛል” ብላለች።

እንደፈራችውም አያቷ ተያዙ። ሆስፒታል ሄዶ ለመንገላታት ግን አልፈቀዱም። እምቢኝ አሻፈረኝ አሉ። ሆስፒታሎች ውስጥ ያለውን እንግልት አላጡትም።

እርሷም ቢሆን በወሬ ወሬ፣ ሬሳ በሬሳ ላይ እየተከመረ እንደሆነ እየሰማች እንደሆነ፤ ሆስፒታሎች መተላለፊያዎቻቸው ሳይቀሩ በበሽተኞች መጥለቅለቃቸውን ትናገራለች።

የአያቷ መጨረሻም እያስጨነቃት ነው።

እርሷ ለጊዜው ኮቪድ አልያዛትም።

ባለቤቷ በታመመ ጊዜ ከፍርሃቷ የተነሳ ስትተኛ እንኳ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ አታወልቅም ነበር።

“ዋናው ሁለታችንም በተመሳሳይ ጊዜ መታመም የለብንም ብዬ ነው ያን ጥንቃቄ ያደረገኩት” ትላለች።

ነገር ግን ተህዋሲውን ያን ያህልም እንደማትፈራው አብራርታለች።

አሁን በቻይና ትልልቅ ከተሞች ሰዎች ገበያ ማዕከሎችን እያጨናነቁ ነው።

ሬስቶራንቶች ሙሉ ናቸው።

ፓርኮች አካባቢ በሕዝብ ተሞልቷል።

ይህ ሁሉ የሆነው የእንቅስቃሴ ገደብ ሙሉ በሙሉ በመነሳቱ ነው።

መዝነኛዎች ሙሉ እንደሆኑት ሁሉ ሆስፒታሎችም ሞልተዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ነው በተህዋሲው እየተያዘ ያለው።

የበሽታው ስርጭት ይባባስ ይሆን?

የቻይና ፖሊሲ “ዜሮ ኮቪድ” በነበረ ጊዜ የቻይና ሐኪሞች በተህዋሲው መያዝ አደገኛ እንደሆነ ነው ነጋ ጠባ ሲሰብኩ የቆዩት።

አሁን ደግሞ ፖሊሲው ሲቀየር ተህዋሲው ያን ያህልም አሳሳቢ እንዳልሆነ መናገር ጀምረዋል።

ሕዝቡም በዚህ ግራ ተጋብቷል።

ሚስ ዋንግ የተባለች የቤይጂንግ ነዋሪ ይህ ፖሊሲ ከመምጣቱ በፊት ቀደም ብላ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ገዛታለች።

ለመተንፈሻ የሚያገለግሉትን ኦክሲጂኔተር፣ ኦክሲሜተር እና ሌሎችንም የገዛችው ለአያቷ ነው።

አያቷ ዕድሜያቸው ከ90 በላይ ነው።

ከዚህ በኋላ በወረርሽኙ ከተያዙ ላይመለሱ ይችላሉ የሚል ስጋት አላት።

የኮቪድ ወረርኙ ዳግም ከመስፋፋቱ በፊት ወሳኝ የጤና ዕቃዎችን መግዛቷም ብልህነት እንደነበር አሁን ተረድታለች።

እርሷ እንደምታምነው አሁን መንግሥት ገደቦችን ማንሳቱ ለኢኮኖሚው በጣም ጥሩ ነው።

ቢዝነስ በአንድ ጊዜ ነው መነቃቃት ያሳየው።

ሊ የ52 ዓመት ወይዘሮ ናቸው።

መንግሥት ቀደም ሲል “ኮቪድ ዜሮ” ፖሊሲ ብሎ የወሰደው እርምጃ ትክክል ነው ብለው ይከራከራሉ።

ነገር ግን አሁን በድንገት ያን ገደብ ማንሳት አልነበረበትም ብለው ያስባሉ።

ምክንያቱም አንደኛ ይህ ቀዝቃዛው ወቅት ለተህዋሲው ሥርጭት የተመቸ ነው።

 ሁለተኛ ቀስ በቀስ ነበር ገደቡ መነሳት የነበረበት።

ሁሉም ነገር ድንገት ሆነና ነው ችግሩ የተፈጠረው ባይ ናቸው።

“2022 አስቀያሚ ዓመት ነበር ለእኛ ቻይናውያን፤ 2023 የከፋ እንዳይሆን ተግተን እንጸልያለን” ይላሉ።

አንዳንድ የቻይና ወጣቶች ግን ከዚህ ሁሉ ጭንቅ ተህዋሲውን በገዛ ፈቃድ ተቀብሎ ሁሉንም ነገር መሻገርና የቻይናን አዲስ ዓመት “በሰላም እና በጤና መቀበልን” መርጠዋል።

ምንም እንኳን በበሽታው ሰበብ ሰላም እና ጤና ሊርቃቸው እንደሚችል እያወቁም ያልተጠበቀውን እርምጃ እንደ አማራጭ ወስደውታል።