የጋዛን ውብ የባሕር ዳርቻ ለመቀራመት ያሰፈሰፉት እስራኤላውያን

ከባሕር ዳርቻ ፊት የተገነባን ቆንጆ ቪላ ማን ይጠላል? ቀኝ ዘመም እስራኤላውያን ውብ በሆነው የጋዛ ባሕር ዳርቻ ፊት ለፊት ቤተ ለመገንባት ወጥነዋል።

የ78 ዓመቷ ዳንኤል ዌይሳ ወደ ጋዛ ለመዘዋወር ዝግጁ የሆኑ የ500 ቤተሰቦች ዝርዝር አለኝ ይላሉ።

የልጅ ልጅ ያዩት አያት ‘ናቻላ’ ወይም ‘የትውልድ አገር’ የሚባል ድርጅትን ይመራሉ።

ይህ ድርጅት ባለፉት አስርት ዓመታት በኃይል በተያዙት ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌም እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በእስራኤል በተያዙ የፍልስጤማውያን መሬት ላይ ሰፋሪዎችን ሲያሰፈር ቆይቷል።

“በቴል አቪቭ ያሉ ጓደኞቼ ‘ከባሕር ዳርቻው ፊት ለፊት መሬት ያዢልኝ። እንዳትረሺኝ’ ይሉኛል። ምክንያቱም የጋዛ የባሕር ጠረፍ በጣም ውብ ነው። አሸዋው ወርቃማ ቀለም ያለው ውብ አሸዋ ነው።”

አዛውንቷ እንደምትለው ለመኖሪያ ቤት ግንባት ይሆናሉ ተብለው የተለዩ ቦታዎች በሙሉ ተይዘዋል።

አዛውንቷ በሚመሩት ድርጅት ውስጥ ያሉ አይሁዳውያን ከአውሮፓውያኑ 2005 በኋላ ወደ ጋዛ ተመልሶ የፍልስጤማውያን መሬትን ለመውረር አሰፍስፈው እየተጠባበቁ ነው።

የጋዛን የባሕር ጠረፍ ለመቀራመት ከሚጠባበቁት መካከል አንዳንዶቹ ሳይወዱ በግድ በራሳቸው ጦር አካባቢውን እንዲለቁ የተደረጉ አይሁዳውያን ይገኙበታል።

እአአ 2005 እስራኤል ከጋዛ ስትወጣት በ21 የሰፈራ ጣቢያዎች ኑሮ መሥርተው የነበሩ 9 ሺህ ዜጎቿን አስወጥታ ነበር።

በወቅቱ ከጋዛ ስትዘግብ የነበረችው ኦርላ ጉሬን ብዙዎች በጦሩ ሳይወዱ በግድ ተጎትተው ሲወጡ አስታውሳለሁ ትላለች።

በርካታ እስራኤላውያን ይህን እርምጃ በአገራቸው ክህደት እንደተፈጸመባቸው አድርገው ያስባሉ።

ከመስከረም 26ቱ ድንገተኛ ጥቃት በኋላ የጋዛን መሬት በኃይል ይዞ የሰፈራ መንደሮችን ማቋቋምን ሐሳብ ከእስራኤል መንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀር ድጋፍ እያገኘ መጥቷል።

የናቻላ ድርጅት መሪዋ ዌይሳ ፍልስጤማውያን አንድ ቀን አገር እንገነባበታለን ብለው በሚያልሙት ዌስት ባንክ በአይሁዳውያን የተያዙትን ቦታዎች በኩራት ያሳያሉ።

ይህንንም በካርታ ላይ በማስፈር የእስራኤል ሰፋሪዎች የያዟቸውን ቦታዎች ያሳያሉ። በዚህ አካባቢ ከ700ሺህ በላይ አይሁዳውያን ሰፋሪዎች አሉ።

ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ እነዚህ ሰፈራዎች ሕገ-ወጥ ናቸው ቢልም በፍልስጤማውያን መሬት ላይ የሚደረገው ወረራ እና የሰፋሪዎች ቁጥር በየዕለቱ ከመጨመር አላገደም።

የ78 ዓመቷ አዛውንት አሁን ላይ 2.3 ሚሊዮን ፍልስጤማውያንን እያኖረ ያለው ጋዛ ሙሉ በሙሉ የእስራኤል ይሆናል ብለው ያምናሉ።

“በጋዛ ሰርጥ አረቦች አይኖሩበትም። ማን ይኖርበታል? አይሁዳውያን” ሲሉ ለራሳቸው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣሉ።

ዳንኤላ ዌይሳ “የጋዛ አረቦች” ካሻቸው ወደ ተቀረው ዓለም መሰደድ ይችላሉ ይላሉ።

“ዓለም ሰፊ ነች። . . . አፍሪካ ትልቅ ነች። ካናዳ ትልቅ ነች። ዓለም የጋዛ ነዋሪዎችን መቀበል ይችላል። መሄድ ስለሚፈልጉ ብናበረታታቸው ጥሩ የሆኑት የጋዛ ነዋሪዎች ይሄዳሉ” ሲሉም ይደመጣሉ።

በአሁኑ ወቅት የጋዛ ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ጥለው እየተሰደዱ ያሉት ከእስራኤል የቦምብ ድብደባ ሕይወታቸው ለመታደግ እንጂ ዳንኤላ ዌይሳ እንደሚሉት ፍልስጤማውያን ጋዛን ጥለው ለመሰደድ ፍላጎት ኖሯቸው እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ የለም።

የቢቢሲዋ ኦርላ ከዚህ ቃለ መጠይቅ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ዳንኤላ ዌይሳ መኖሪያ ቤት ስትመለስ አዛውንቷ በአካባቢዋ ከሚኖሩ ሰፋሪዎች ጋር ስትወያይ አግኝታቸዋለች።

ዳንኤላ “ወደ ገዛ መመለስ” የሚል ርዕስ ያለበት እና “አዲሷን ጋዛ” የሚያሳይ ካርታ በፕሮጀክተር ላይ በማድረግ ለተሳታፊዎቹ ማብራሪያ ይሰጣሉ።

ሰዎች ወደ ጋዛ የመመለስ ዕቅድ አይሳካም ሲሉኝ “ድሮ ድሮ ዌስት ባንክ ላይ ለመስፈር ሲታቀድ ምን ያህል ይሳከል ብላችሁ ታስቡ ነበር ብዬ እጠይቃቸዋለሁ” ትላለች።

በውይይቱ ተሳታፊ ከሆኑ አንዷ የሆነች ጉሽ ካቲፍ፤ “ወደ ጋዛ መመለስ” በሚለው ሐሳብ ሙሉ በሙሉ የተስማማች ትመስላለች።

“አሁን አካባቢው ባዶ ነው። የሰፈራ ቤቶችን የት ልገንባ ብሎ ማሰብ አያስፈልግም። ወደ ጋዛ ተመልሶ አዲስ የሰፈራ አካባቢን መገንባት ብቻ ነው የሚያስፈልገው” ትላለች።

ምንም እንኳ ባለፉት ስድስት ወራት በማይቋረጠው የእስራኤል ድብደባ ጋዛ እንዳልነበር ብትሆንም ሰው አልባ ባዶ ሆናለች ማለት ግን አይቻልም።

በእስራኤል ጥቃቶች አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ 32ሺህ ሰዎች ተገድለዋል። የጋዛ መሠረተ ልማት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወድሟል። የጋዛ ሕንጻዎች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ካቢኔ አባላት ጨምር ከምንጊዜም በተሻለ ሁኔታ ጋዛ አሁን ላይ ለሰፈራ ምቹ ሆናለች ብለው ያምናሉ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጋቪር ከ1ሺህ በላይ ሰዎች በተሰበሰቡበት መድረክ ላይ ወደ ማይክራፎን ቀረብ ብለው “ወደ መሬታችን የመመለሻው ትክክለኛ ጊዜ አሁን ነው። እንደ መስከረም 26ቱ ዓይነት ጥቃት ካልፈለግን ወደ አገራችን ተመልሰን መሬቱን መቆጣጠር ያለብን ጊዜ አሁን ነው” ሲሉ በደማቅ የድጋፍ ጭብጨባ ታጅበው ነበር።

ከቀኝ አክራሪ አይሁዳውያን ቅስቀሳ በዘለለ ሰፈራዎችን የሚያቋቁሙ ድርጅቶችም ለግንባታ ዝግጅት ነን ቢሉም በትክክል ዕቅዳቸው ይሳካ ይሆን የሚለውን ጊዜ የሚመልሰው ነው።

ይሁን እንጂ አንድ በስም ያልተጠቀሰ እስራኤላዊ ጋዜጠኛ ይህ ተግባራዊ የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው ይላል።

“በጋዛ የመስፈር ጥያቄ ቢኖርም ይህ በመንግሥት ፖሊሲ ይደገፋል የሚል እምነት የለኝም” ይላል።