የኢትዮጵያ መንግሥት የተመድ ሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ሪፖርትን ውድቅ አደረገ

የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ የተከሰቱ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ያወጣውን ሪፖርት እንደማይቀበለው እስታወቀ።

ሪፖርቱ “ያልተሟላ፣ ተያያዥነት የሌለው እና በመረጃ ያልተደገፈ” በማለት አገሪቱን በመጥፎ መልኩ ለማቅረብ የታለመ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት አጣጥሎታል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አጣሪ ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት ላይ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎችን ማግኘቱን አስታውቋል።

ሦስት አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚሽን የመብት ጥሰቶቹ “የጦር ወንጀል” እና “በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች” ናቸው ሊባሉ የሚያስችሉ ስለመሆናቸው አሳማኝ ምክንያቶች ማግኘቱን በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።

ቀደም ሲል በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አማካኝነት የተደረገውን ምርመራ የሚቃረን ነው በሚል የኢትዮጵያ መንግሥት የአጣሪ ኮሚሽኑን መቋቋም ተቃውሞ ነበር።

የአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን ያመለከተ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን የሚያመለክቱ አሳማኝ መረጃዎች ማግኘቱን ገልጿል።

ሪፖርቱ “በጥድፊያ የተዘጋጀ፣ ከደረጃው የወረደ” መሆኑን በመግለጽ የተሰማውን ቅሬታ ያመለከተው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ጨምሮም አጣሪ ኮሚሽኑ አጀንዳን ለማሳካት በመረጠ መንገድ ሥራውን አከናውኗል ሲል ወቅሷል።

በቀረበው ሪፖርት ላይ ጠንካራ ትችት የሰነዘረው የኢትዮጵያ መንግሥት የምርመራው ውጤት “በምርመራ ሪፖርት ስም ፖለቲካዊ መግለጫ ነው” ብሎታል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የባለሙያዎች አጣሪ ቡድን በሪፖርቱ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ግድያዎች፣ አካላዊ ጥቃቶች፣ መድፈር እና ወሲባዊ ጥቃቶችን በመጥቀስ በሪፖርቱ ላይ ያቀረበ ሲሆን፣ ፀጥታው ምክር ቤት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን አጀንዳ አድርጎ እንዲነጋገር ጠይቋል።

ሪፖርቱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ተቃውሞና ትችት የቀረበበት ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ቀድሞ የታሰበውን “ኢትዮጵያን የመወንጀል እና ዝቅ አድርጎ የማቅረብ” ፖለቲካዊ ውጤት ነው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ሬድዋን ሪፖርቱን፣ "የተምታታና ተጨባጭነት የሌለው" ብለውታል።

በጀኔቭ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደም፣ ኮሚሽኑ መንግሥት ርሃብን በጦር መሳሪያነት ስለመጠቀሙ አንድም ማስረጃ አላቀረበም" ሲሉ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

ዘነበ ጨምረውም፣ "የሪፖርቱ ድምዳሜዎች ርስበርስ የሚጋጩና አድሏዊ ናቸው" ብለዋል።

የመርማሪ ቡድኑ ሰብሳቢ የሆኑት ኬንያዊቷ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ እንደተናገሩት፣ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ሌሎች መሠረታዊ አገለግሎትች አቅርቦትን መከልከል መፈጸሙን ጠቅሰው “መንግሥት ማስራብን የጦርነቱ አንድ ዘዴ አደርጎ እንደተጠቀመበት ሊያሳምን የሚችል መረጃ” መግኘታቸውን ገልጸዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መቀመጫ በሆነችው ጄኔቭ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ዘነበ ከበደ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እንደተናገሩት መርማሪ ቡድኑ “ፖለቲካዊ አላማን የያዘ” እና ሪፖርታቸውም “ወገንተኛ እና እርስ በርሱ የሚቃረን” ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

“የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብአዊ እርዳታን እንደ ጦርነት መሳሪያ መጠቀሙን የሚያሳይ አንድም ማስረጃ አላቀረቡም” ያሉት አምባሳደሩ፣ በህወሓት የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን ችላ ያለ ነው ያሉትን ሪፖርት “የማይረባ” በማለት “ውድቅ ከማድረግ ውጪ ምንም አማራጭ የለንም” ብለዋል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውደመትን ከማስከተሉ ባሻገር፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሰብአዊ እርዳታ ጠባቂ አድርጓቸዋል።

ቀደም ሲል በተደረጉ ምርመራዎች እና የሰብአዊ መብት ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊቶች እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን በተደጋጋሚ ማሳወቃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም በመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ምርመራ የሚያካሂድ ቡድን አቋቁሞ እየሰራ መሆኑንና በደሎችን ፈጽመዋል የተባሉ የሠራዊቱን አባላት ለፍርድ ማቅረቡን በመጥቀስ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ይገልጻል።