ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከቱርኩ ርዕደ መሬት ተርፈው “ያለ ስም” ብቻቸውን የቀሩ ሕጻናት
ቱርክ እና ሶሪያን ክፉኛ በመታው ርዕደ መሬት ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩም ለጉዳት መዳረጋቸው ተገልጿል። አሁንም የፍለጋ ሥራው በመቀጠሉ በፍርስራሽ ሥር ተቀብረው የሚገኙ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ይታመናል።
ከአደጋው የተረፉ ቤተሰቦች ድምጻቸው የጠፋባቸውን ልጆቻቸውን፣ ባለቤታቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን ለመፈለግ አንስተው የማይጨርሱትን የፍረስራሽ ክምር ለማንሳት ሲሞክሩ ተስተውሏል።
አደጋው ከደረሰ ቀናት ቢቆጠሩም በሕይወት የተረፉ ቤተሰቦቻቸውን የማግኘት ተስፋቸው ያልተሟጠጠ በርካቶች ናቸው።
እስካሁንም በአስደናቂ ሁኔታ አዲስ የተወለዱትን ጨምሮ በርካታ ሕጻናት በሕይወት ከተቀበሩበት መውጣት ችለዋል።
በቱርክ አዳና ከተማ በሚገኘው ሆስፒታል ከአደጋው በሕይወት የተረፉ በርካታ ሕጻናት ይገኛሉ።
ብዙዎቹ ስማቸውን መናገር አይችሉም። የተኙበት አልጋ ላይ “ስማቸው የማይታወቅ” ተብሎ ነው የተጻፈው።
ርዕደ መሬቱ ወላጆቻቸውን እና ዘመዶቻቸውን አሊያም ቤታቸውን ብቻ አይደለም የነጠቃቸው። መጠሪያ ስማቸውንም ጭምር ነው።
አሁን እነዚህ ልጆች ስም የላቸውም። የማን ልጆች እንደሆኑም አይታወቅም። ፈላጊ እስከሚመጣ ከመጠባበቅ ውጪ ምርጫ የለም።
በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ዶክተሮች በርዕደ መሬቱ ጉዳት ያጋጠማትን የ6 ወር ጨቅላ ሕጻን ጡጦ ያጠባሉ። የዚህች ሕጻን ቤተሰቦች ሊገኙ አልቻሉም።
በእርግጥ ማንነቷ ያልታወቀው የእርሷ ብቻ አይደለም።
ቤተሰቦቻቸው በሕይወት ይኑሩ፣ ይሙቱ የማይታወቅ እና ማንነታቸው ያልተለየ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት አሉ።
የሆስፒታሉ ዳይሬክተር እና የሕጻናት ሐኪሟ ዶክተር ኑርሳህ ኬስኪን፣ በአልጋዋ ላይ በተለጠፈው ‘ስሟ የማይታወቅ’ የሚል መለያ ብቻ የምትታወቀውን እና በጽኑ ህሙማን ክፍል ያለችውን ሕጻን እጅ ይዛ ቆማለች።
ሕጻኗ ከባድ ጉዳት ነው ያጋጠማት። አጥንቶቿ ተሰነጣጥቀዋል። ዓይኖቿ ጠቁረዋል። ፊቷ ክፉኛ ተጎድቷል። ግን በስብራት ውስጥ የሚታይን ፈገግታ ትሰጣለች።
ዶክተር ኬስኪን ስለ ሕጻኗ ሲናገሩ “የት እንደተገኘች እና ወደዚህ እንዴት እንደመጣች እናውቃለን። አድራሻዋን ለማወቅ እየሞከርን ነው። እስካሁን ፍለጋው እንደቀጠለ ነው” ብለዋል።
እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ከገጠማቸው ሕጻናት መካከል አብዛኞቹ በሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ ሕንጻዎች ወድቀው የተረፉ ናቸው።
ወደ አዳና ሆስፒታል ያመጧቸውም ሆስፒታሉ አሁንም አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ ነው።
ርዕደ መሬቱ ባጋጠመበት አካባቢ ያሉ በርካታ የጤና ተቋማት ፈራርሰዋል አሊያም ጉዳት ደርሶባቸዋል። በመሆኑም አዳና ሆስፒታል በአደጋው ጉዳት ላጋጠማቸው የሕክምና ማዕከል ሆኗል።
በኢስከንድረን ከተማ በርዕደ መሬቱ ክፉኛ ከተመታ ሆስፒታል የእናቶችና ሕጻናት ክፍል አዲስ የተወለዱ ሕጻናት ወደዚህ ሆስፒታል ተልከዋል።
እንደ አገሪቷ ጤና ሚኒስቴር ከሆነ በርዕደ መሬቱ ከተመቱ አካባቢዎች ውስጥ ከ260 በላይ ጉዳት ያጋጠማቸው እና ማንነታቸው ያልታወቀ ሕጻናት አሉ።
የተለያዩ አካባቢዎችን መድረስ እየተቻለ በመሆኑም ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።
የአዳና ሆስፒታል መተላለፊያዎች በተጎዱ ሰዎች ተጨናንቋል። ከአደጋው የተረፉት በአልጋዎች ላይ ተኝተዋል። ሌሎች ደግሞ በፍራሽ ላይ በብርድ ልብስ ተጠቅልለው በድንገተኛ ክፍል ላይ ይታያሉ። የቀዶ ሕክምና ክፍሉም በበርካታ ጉዳት ባጋጠማቸው ሕጻናት ተሞልቷል።
አምስት አሊያም ስድስት ዓመት የሚሆናት ሕጻን ጉሉኮስ ተተክሎላት ተኝታለች። ባለሙያዎች እንደሚሉት የጭንቅላት ጉዳት እና በርካታ መሰነጣጠቅ አጋጥሟታል።
የሕጻናት ቀዶ ሕክምና ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ኢልክኑር ባነሊሴሰር “ይህችም ሕጻን ስሟን መናገር አልቻለችም። ስሟን አልነገረችንም። በዐይና እና በምልክት ብቻ ነው የምንግባባው።
“ከፍተኛ በሆነው የርዕደ መሬቱ ነውጥ ሳቢያ ሕጻናቱ ማውራት አይችሉም። ስማቸውን ግን ያውቃሉ። ወደ መረጋጋት ሲመለሱ ከሁለት ቀናት በኋላ ለማውራት እንሞክራለን” ብለዋል ሕጻናቱ ስላሉበት ሁኔታ ሲገልጹ።
የጤና ባለሥልጣናት ማንነታቸው ያልታወቁ ሕጻናትን አድራሻ ለመፈለግ ጥረት እያደረጉ ነው፤ ነገር ግን አድራሻቸው ከፍርስራሽ ያለፈ አይደለም።
የቱርክ ማኅበራዊ ሚዲያ በጠፉ ሕጻናት ምስሎች ተጨናንቋል። ከፎቷቸው ጋር የልጆቹን የመኖሪያ ሕንጻ፣ ስንተኛው ወለል ላይ ይኖሩ እንደነበር በመግለጽ ዝርዝር መረጃ አጋርተዋል። ሕጻናቱ ሕይወታቸው ተርፎ ሊሆን እንደሚችልም ተስፋ አድርገዋል።
እነርሱን ለመፈለግ በሕይወት የተረፉ ቤተሰቦች እና የጤና ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ወደ ጤና ተቋማት ይሄዳሉ።
በአዳና ሆስፒታል፣ የተጎዱ ሕጻናት አሁንም እየመጡ ነው።
ስሜታቸው አሳዛኝ ነው። ደንግጠዋል፤ ተዳክመዋል። ሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኙት በሙሉ ከአደጋው የተረፉ ናቸው።
በእርግጥ ታማሚዎችም የጤና ሠራተኞችም በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ነው ያሉት።
ዶ/ር ኬስኪን በአደጋው ዘመዶቿን አጥታለች። ከልጆቿ ሆስፒታል ውስጥ ነው ተጠልላ ያለችው።
ስላለችበት ሁኔታ የተጠየቀችው ኬስኪን “ደህና ነኝ ። ደህና ለመሆን እየሞከርኩ ነው። ምክንያቱም ሕጻናቱ ይፈልጉናል። ልጆቼ ስለተረፉልኝ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ። ለእናት ልጆቿን ከማጣት በላይ ሌላ ህመም ያለ አይመስለኝም” ብላለች።
በሆስፒታሉ ከሚገኙ ታካሚዎች ጥቂቶቹ ከቤተሰባቸው ጋር ተገናኝተዋል። ቀሪዎቹ ርዕደ መሬቱ ስማቸውን ከእነ ማንነታቸው ጠራርጎ የወሰደባቸው ማንነታቸው ያልታወቁ ሕጻናት ናቸው።