ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ከቻይና በዶላር ከተሰጣት ብድር የተወሰነውን ወደ ዩዋን ለመቀየር ንግግር መጀመሩ ተገለጸ
ኢትዮጵያ ከቻይና ካለባት የ5.38 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ የተወሰነውን የቤጂንግ መገበያያ ገንዘብ ወደሆነው ዩዋን ለመቀየር ንግግር መጀመሩ ተገለጸ።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ፤ ባለፈው ወር በቻይና፣ ቤጂንግ ጉብኝት ላይ ሳሉ ከቻይና ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ እንዲሁም ከቻይና ብሔራዊ ባንክ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ዶ/ር ኢዮብ ጥቅምት 07/2018 ዓ. ም. በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ የኢትዮጵያን ዕዳ ወደ ዩዋን ለመለወጥ ውይይት መጀመሩን ተናግረዋል።
ዶ/ር ኢዮብ "ቻይና እጅግ ጠቃሚ አጋራችን ናት፤ የንግድና ኢንቨስትመንት መጠን ጨምሯል፤ ስለዚህም የተወሰነ የመገበያያ ገንዘብ ለውጥ (currency swap) ማድረጉ ትርጉም ይሰጣል" ማለታቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።
ብሉምበርግ እንደዘገበው፤ የዶላር ዕዳውን ወደ ዩዋን ለመለወጥ "በይፋ ጥያቄያችንን አቅርበናል" ሲሉም ዶ/ር ኢዮብ ተናግረዋል።
ዶ/ር ኢዮብ ከኢትዮጵያ ብድር ውስጥ ምን ያህሉ ወደ ዩዋን እንደሚለወጥ በግልጽ ባይናገሩም "በዚህ መንገድ ገንዘብ ማትረፍ ይቻላል። ገና ጅማሮ ላይ ያለ ጉዳይ ቢሆንም በጣም በጉጉት የምንጠብቀው ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሰኔ 2024 አንስቶ ከቻይና ያለባት የዕዳ መጠን 5.38 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ አይኤምኤፍ ያሳለፍነው ነሐሴ ያወጣው መረጃ ይጠቁማል።
ኢትዮጵያ በጊዜው ያልከፈለችውን የ15 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ሽግሽግ በተመለከተ ከአበዳሪዎቿ ጋር ድርድር ስታደርግ ቆይታለች።
አገሪቱ በጊዜው ያልከፈለችውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዩሮ ቦንድ በተመለከተ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በግል አበዳሪዎች ኮሚቴ መካከል ሲደርግ የነበረው ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ባለፈው ሳምንት ተዘግቧል።
ገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ለቀናት በቆየው ንግግር "ጉልህ መሻሻል" መታየቱን ቢገልጽም፤ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ግን ድርድሩ "ፍሬ አልባ" ደረጃ ላይ በመድረሱ "ሕጋዊ አማራጭ" ሊከተል እንደሚችል አስታውቋል።
ዶ/ር ኢዮብ ድርድሩን በተመለከተ "በጣም ከባድ ንግግር አድርገናል፤ ግን የማይታለፍ ነጥብ ብዬ አልገልጸውም፤ መሻሻል አለ" ብለዋል።
ኢትዮጵያ 6.625 በመቶ ዓመታዊ ወለድ የሚከፈልበት እና በ10 ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የሚመለስ የአንድ ቢሊዮን ብር ቦንድ ለሽያጭ ያቀረበችው በ2007 ዓ. ም. ነበር።
መንግሥት በዓመት ሁለት ጊዜ በሐምሌ እና ታኅሣሥ ወራት እንዲከፍል የሚጠበቅበትን ወለድ እስከ 2015 ዓ. ም. ድረስ ሲፈጽም የቆየ ቢሆንም ከታኅሣሥ 2016 ዓ. ም. አንስቶ ይህንን ግዴታውን አልተወጣም።
በተጨማሪም ቦንዱ በታኅሣሥ 2017 ዓ. ም. ሙሉ በሙሉ መመለስ የነበረበት ቢሆንም ይህም አልተፈጸመም። ኢትዮጵያ ቦንዱ የሚመለስበት ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ከአበዳሪዎች ጋር ተደጋጋሚ ንግግሮችን አድርጋለች።
በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ አማካይነት እንደ ቻይና ካሉ አበዳሪ አገራት የዕዳ ሽግሽግ ለማግኘት ንግግር ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ከሁሉም አበዳሪዎች ጋር በሚኖር ግንኙነት ላይ "ወጥነት እና እኩልነትን ማረጋገጥ" እንደሚፈልግ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለቦንድ አበዳሪዎቹ መከፈል የነበረበትን ወለድ ለማዘግየት የወሰነው፤ ይህንን ውል በመደበኛ አካሄዱ ማስቀጠል እፎይታ እንዲሰጡት ከጠየቃቸው "ሌሎች የውጭ አበዳሪዎች ጋር የሚደረገውን ውይይት አደጋ ላይ ይጥለዋል" በሚል ነው።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እንደ ቻይናው ኤግዚም ባንክ ካሉ አበዳሪዎች ጋር በዚህ ዓመት መጨረሻ የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ የምትደርስ ሲሆን፤ የስምምነት ረቂቅ የተላከላቸው አበዳሪዎችም አሉ።
እንደ ባንኮችን ካሉ የግል አበዳሪዎች (non-bond commercial creditors) ጋር እንዲደረስ የሚጠበቀውን የሁለትዮሽ ስምምነት ደግሞ እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን ዶ/ር ኢዮብ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ኬንያ ከቻይና ያለባትን ዕዳ ወደ ዩዋን ለመለወጥ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል። ከኬንያ በተጨማሪ ሲሪላንካ እና ሀንጋሪም ተመሳሳይ ውሳኔ ማሳለፋቸው ተዘግቧል።
ኬንያ የዶላር ዕዳዋን ወደ ዩዋን በመለወጥ 215 ሚሊዮን ዶላር እንደምታተርፍ የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።
የቻይና መንግሥት የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ዩዋን በዓለም አቀፍ ገበያ ጠንካራ መገበያያ እንዲሆን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሯል።
ኢትዮጵያ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ 10 አባል አገራት ያሉት ብሪክስ፤ ዶላር በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ዋጋ ለመገዳደር (de-dollarization) ውይይቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የብሪክስ ጥምረት ፖሊሲዎችን ወግነው ከአሜሪካ ጥቅም የሚጻረሩ አገራት ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው መናገራቸው አይዘነጋም።
ቻይና በዶላር የተወሰደን ብድር አነስተኛ ወለድ ባለው ዩዌን እንዲመለስ የዘረጋችው አሠራር "ዩዋንን በዓለም አቀፍ መገበያያ ጠንካራ የማድረግ" አካል መሆኑን የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ሌሴትጃ ካግኛጎ መናገራቸውን የብሉምበርግ ዘገባ ያትታል።
የቻይና የአንድ ዓመት የወለድ መጠን 3% የአሜሪካ ደግሞ 7.25% ነው።
ከቻይና በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ዕዳ ያለባት ዛምቢያም ብድሯን ወደ ዩዋን ለመለወጥ "የኬንያን መንገድ በንቃት እየተከታተች" እንደምትገኝ የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ሲቱምባኮ ሙሶኮታዌን ባለፈው ሳምንት ገልጸዋል።
አይኤምኤፍ እንዲህ ያሉ የመገበያያ ገንዘብ ልውውጥ ስምምነቶች "አዎንታዊ ሚና አላቸው" ብሏል።
የአይኤምኤፍ የአፍሪካ ዳይሬክተር አበበ አእምሮሥላሴ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደ ኬንያ ላሉ አገራት "ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያድን አምናለሁ" ማለታቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።