ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ልዑል አንድሪው የቻይና ሰላይ ነው ተብሎ ከተጠረጠረው ግለሰብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ገለፁ
ልዑል አንድሪው የቻይና ሰላይ ነው ተብሎ ከተወነጀለው ነጋዴ ጋር የመንግሥት ምክርን ተከትሎ "ግንኙነት ማቆማቸውን" ገለፁ ።
ጽህፈት ቤታቸው በመግለጫው ልዑል አንድሪው ግለሰቡን "ይፋዊ በሆኑ መንገዶች" ማግኘታቸውን እና "ምንም ዓይነት ለአደጋ የሚያጋልጥ መረጃ ላይ አለመወያየታቸውን" አስታውቀዋል።
በሰላይነት የተጠረጠረው ቻይናዊ በከፊል ምስጢራዊ በሆነው የብሔራዊ ደህንነት ችሎት ዩኬ እንዳይገባ ተወስኗል።
ኤች6 በሚባል መለያ ብቻ የሚታወቀው ቻይናዊ በፍርድ ቤት "የልዑል አንድሪው የቅርብ ወዳጅ" ተብሎ የተገለፀ ሲሆን፣ ከልዑሉ ጋር "ባልተለመደ መልኩ እምነት የተጣለበት" እንደነበር ተገልጿል።
ዳኞች ነጋዴው የልዑል አንድሪውን ተፅእኖ ለመጠቀም እየሞከረ እንደሆነ ተነግሯቸዋል።
የልዑሉ ፅህፈት ቤት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለቀረበለት ጥያቄ "ከብሔራዊ ደህንነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ አስተያየት መስጠት አልችልም" ብሏል።
ልዑሉ በመግለጫቸው ላይ በስለላ ከተጠረጠረው ግለሰብ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት መቼ እንዳቋረጡም ሆነ ለምን ያህል ጊዜ ይገናኙ እንደነበር አልገለፁም።
ቤኪንግሃም በበኩሉ አሁን ቤተመንግሥቱን ወክለው በሥራ ላይ የሌሉ ግለሰብን በሚመለከት መረጃ መስጠት እንደማይችል በመግለጽ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
እ.ኤ.አ. በ 2023 ኤች6 በመጀመሪያ የተጣለበት እገዳ ላይ ይግባኝ ያለ ቢሆንም፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲጸና ሆኗል።
በእንግሊዝ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ "በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች በቻይና ላይ ያነጣጠረ መሠረተ ቢስ 'የስለላ' ታሪኮችን ለመፈብረክ ሁልጊዜም ዝግጁ ናቸው" በማለት ውንጀላውን አስተባብሏል።
"ዓላማቸው የቻይናን ስም ማጠልሸት እና በቻይና እና በእንግሊዝ መካከል ያለውን መደበኛ ግንኙነት ማደናቀፍ ነው" ሲሉ የኤምባሲው ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የቀድሞዋ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሱኤላ ብራቨርማን ኤች6ን ከዩኬ ያገዱት እንደ አውሮፓውያኑ በ2023 መጋቢት ወር ላይ ነበር።
ግለሰቡ ጉዳዩን፣ በብሔራዊ ደኅንነት ወይም በተዛማጅ ምክንያቶች ግለሰቦችን ከአገሪቱ ለማገድ ወይም ለማስወጣት በተሰጠ ውሳኔ ላይ ይግባኝ ለማየት ለተቋቋመው የኢሚግሬሽን ልዩ ይግባኝ ሰሚ ኮሚሽን አቅርቧል።
ችሎቱም ቀደም ብሎ የተሰጠውን ውሳኔ አጽድቋል።
ፍርድ ቤቱ ኤች6 እ.ኤ.አ. በ 2020 ልዑል አንድሪው የልደት ክብረ በዓል ላይ እንደተጋበዘ እና በቻይና ውስጥ ካሉ ባለሀብቶች ጋር በሚገናኙበት ጊዜ ወክሏቸው መስራት እንዲችል መነጋገራቸውን ጠቅሷል።
ኤች6 ከልዑሉ ጋር እንዴት እንደተቀራረበ ግልጽ ባይሆንም፣ በሕዳር 2021ፖሊስ በዩናይትድ ኪንግደም ድንበር ላይ የሌላ አገር ዜጋ "አጠራጣሪ እንቅስቃሴ" ን ለማጣራት በሚል ተይዞ ጥያቄዎች ቀርበውለት ነበር።
በወቅቱ ኤች 6 ሞባይልን ጨምሮ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ተይዘውበታል።
በድንበር ላይ የነበሩት ፖሊሶች ያገኙት ንብረት የደህንነት መስርያቤቱን MI5ን በማሳሰቡ የአገር ውስጥ መስርያቤቱ ያለውን ልዩ ሥልጣን ተጠቅሞ ወደ አገር እንዳይገባ አግዶታል።
ፍርድ ቤቱ ኤች 6 "በቻይና ከፍተኛ ባለስልጣናት እና በታዋቂ የዩናይትድ ኪንግደም ግለሰቦች መካከል ግንኙነቶችን ለመፍጠር" የተንቀሳቀሰ መሆኑን በመጥቀስ በሂደትም ግንኙነቶቹ "ለፖለቲካዊ ጣልቃገብነት ዓላማዎች" ሊውሉ ይችላሉ ሲል ድምዳሜውን ሰጥቷል።
ዳኞቹ አክለውም ኤች6 "ከሱ ጋር የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ከተዘጋጀው የንጉሣዊው ቤተሰብ ከፍተኛ አባል ያልተለመደ እምነት" አግኝቷል ብለዋል።
ግንኙነቱ የዳበረው ልዑሉ "ከፍተኛ ጫና ውስጥ በነበሩበት ወቅት ነው" ይህም " ያለውን ተጽዕኖውን አላግባብ እንዲጠቀም ሊያደርገው ይችላል" ብለዋል ።
ልዑሉ እ.ኤ.አ. ከ2019 መገባደጃ ጀምሮ ከአሜሪካዊው ባለሀብት ጄፍሪ ኤፕስታይን ጋር በነበረው ወዳጅነት የተነሳ ከፍተኛ ክትትል ይደረግባቸዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ ከሕዳር 2019 ጀምሮም ከንጉሳዊ ኃላፊነት ራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን፣ በወቅቱ ስለወሰኗቸው ውሳኔዎች እና ስለ ገንዘባቸው ምንጭ ጥያቄ ቀርቦባቸው ነበር።