በማሊ መፈንቅለ መንግሥት በማሴር የፈረንሳይ ሰላይ መታሰሩ ተገለጸ

ማሊን ለማወክ በሚል ለፈረንሳይ ሲሰልል ነበር ተብሎ የተጠረጠረ ፈረንሳዊ ዜጋን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የማሊ ወታደራዊ አስተዳደር አስታወቀ።

በማሊ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ወታደራዊ አገዛዙ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ያን ቨዚለር የተባለው ግለሰብ "ለፈረንሳይ ብሔራዊ ደኅንነት ተቋም" ተቀጥሮ ይሠራ ነበር።

ተጠርጣሪው እስካሁን ድረስ በክሱ ላይ ምላሽ አልሰጠም።

የግለሰቡ ምሥል እንዲሁም ወታደራዊ መንግሥቱን ለመገልበጥ ሲያሴሩ ነበር የተባሉ የጦር ጀነራሎችም ምሥል ይፋ ተደርጓል።

የማሊ የደኅንነት ሚኒስቴር ጀነራል ዳውድ አሊ መሐመዲን "እነዚህ ሰዎች በመታሰራቸው ሴራው ከሽፏል" ብለዋል።

የቀድሞዋ የማሊ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ ስለ ግለሰቡ መታሰር ጉዳይና ማሊን ለማወክ እየተንቀሳቀሰች ነው ስለመባሉ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

ከ2012 ጀምሮ በኢስላሚስት ታጣቂዎች የደኅንነት ስጋት የበረታባት ማሊ በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ናት። ሆኖም ግን ወታደራዊ አገዛዝ ሥልጣን ሲቆጣጠር የጂሀዲስቶች ቁጥር የበለጠ ጨምሯል።

ላለፉት ቀናት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራን የተመለከቱ ጭምጭምታዎች ሲሰሙ ነበር።

ጀነራል ዳውድ አሊ መሐመዲን "የተገለሉ የማሊ ደኅንነት መዋቅር አባላት ማሊን ለማመሳቀል ሲሞክሩ ተይዘዋል" ብለዋል።

"እነዚህ ወታደሮችና ሲቪሎች የውጭ መንግሥት ድጋፍ ሲደረግላቸው ነበር" ሲሉም አክለዋል።

የፈረንሳዩ ዜጋ እየሠራ የነበረው ለፈረንሳይ ብሔራዊ ደኅንነት ተቋም እንደሆነ ጠቅሰው የፖለቲካ መሪዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰቦችና ወታደራዊ አመራሮችን ማስተባበሩን ተናግረዋል።

ሁለት ወታደራዊ ጀነራሎች እንደታሰሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የቀድሞው የሞፓቲ ግዛት አገረ ገዢ ጀነራል አባስ ዴምቤሌን ይጨምራል።

ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር በተያያዘ ቢያንስ 55 ወታደሮች እንደታሰሩ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ጀነራል ዳውድ አሊ መሐመዲን ሌሎችም "ተባባሪዎችን" ለመያዝ እየተሠራ እንደሆነ ጠቅሰው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው እንደከሸፈና ወታደራዊ ሥርዓቱ "በቁጥጥራቸው ሥር" መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ሳምንታት የማሊ ፖለቲካዊ ውጥረት ተባብሷል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሙሳ ማራ እና ቾገል ማይጋ የአገሪቱን ስም በማጥፋትና በገንዘብ ብዝበዛ ክሶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ሙሳ ማራ ወታደራዊ አገዛዙን አጥብቀው የሚተቹ ሲሆን ከነሐሴ አንድ ጀምሮ ታስረዋል። ቾገል ማይታ ደግሞ በፍርድ ቤት ዕግድ ተጥሎባቸዋል።

ያለፈው ግንቦት ወታደራዊ አገዛዙ ሁሉንም ፖለቲካዊ ፓርቲዎች እንዲሁም ፀረ መንግሥት ተቃውሞዎች አግዷል።

ጀነራል አሲሚ ጎይታ በ2020 እንዲሁም በ2021 ሥልጣን ተቆናጠዋል። አምና ምርጫ እንደሚደረግ ቃል ቢገቡም አልተተገበረም።

ሐምሌ ላይ የሽግግር ጊዜው ወደ አምስት ዓመት እንዲራዘም ተወስኗል። ስለዚህም እስከ 2030 በሥልጣን ይቆያሉ።

ማሊ እና ጎረቤቶቿ ኒጀርና ቡርኪና ፋሶ የጂሀዲስቶችን ጥቃት ለመመከት የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን ድጋፍ መጠየቃቸው አይዘነጋም። ሆኖም የፀጥታው ሁኔታ እስካሁን መሻሻል አላሳየም።