የአል-ቃኢዳ ቅርንጫፍ የሆነው ጂሃዲስት ታጣቂ እንዴት በአፍሪካ አደገኛው ቡድን ሊሆን ቻለ?

የአልቃኢዳ አጋር ጀማአት ኑስራት አል-ኢስላም ዋል-ሙስሊሚን (JNIM) በበርካታ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በተለይም በቡርኪናፋሶ፣ በማሊ እና በኒጀር ላይ እየተስፋፋ ካለው የታጣቂ ጂሃዲስት ጥቃቶች ጀርባ ያለ ዋነኛው ቡድን ነው።

ከአንድ ሳምንት በፊት ሰኔ 24/2017 ዓ.ም. ቡድኑ የሴኔጋል እና የሞሪታንያ ድንበሮች አቅራቢያን ጨምሮ በምዕራብ ማሊ ውስጥ በሰባት ወታደራዊ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የተቀናጀ ጥቃት ማድረሱን ተናግሯል።

ቡድኑ በቀጣናው መረጋጋት ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ተጽዕኖ ስጋት እየጨመረ ነው።

ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር ሁከቱን ለመቆጣጠር ታግለዋል። ይህ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በሦስቱ የሳህል ሀገራት ውስጥ ለበርካታ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አስተዋጽኦ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ነው።

ነገር ግን ከሥልጣን እንዳስወገዷቸው የሲቪል መንግሥታት ሁሉ፣ የአገራቱ ወታደራዊ መሪኦወች (ሁንታ) እያደገ የመጣውን የጂሃዲስት ስጋት በተለይም የጃማኣትን ስጋት ሊገቱት የቻሉ አይመስሉም።

ጀማአት ኑስራት አል-ኢስላም ምንድን ነው?

ጀማአት ኑስራት አል-ኢስላም ዋል-ሙስሊሚን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ አደገኛ የጂሃዲስት ቡድኖች መካከል አንዱ ሆኗል።

በአውሮፓውያኑ 2017 ማሊ ውስጥ የተመሠረተ የአምስት ጂሃዲስት ታጣቂ ቡድኖች ጥምረት ሲሆን ቡድኖቹም፦

  • አንሳር ዲን
  • ካቲባት ማኪና
  • አል-ሙራቢቱን
  • አንሳር አል-ኢስላም
  • በእስላማዊ መግሪብ ውስጥ የአል ቃኢዳ የሰሃራ ቅርንጫፍ ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 2012 የፈረንሳይ ጦር በሰሜናዊ ማሊ ውስጥ ይንቀሳቀሱ የነበሩትን በርካታ የጂሃዲስት እና ተገንጣይ ድርጅቶች ላይ ወታደራዊ ጥቃቶችን ከፈጸመ በኋላ እነዚህ ቡድኖች መተባበር ጀመሩ።

በመጨረሻም የቡድኖቹ መሪዎች ጀማአት ኑስራትን ለመፍጠር ተሰብስበው ነበር ።

በቅርብ ዓመታት ውስጥም ቡድኖቹ የሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች እየተስፋፉ መጥተዋል። በአዲስ የተልዕኮ ቦታዎች ላይም መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

ቡድኑ የሚመራው በቀድሞ የማሊ ዲፕሎማት በነበረው እና የቱዋሬግ ጎሳ አባል በሆነው በኢያድ አግ ጋሊ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2012 በማሊ መንግሥት ላይ በተቀሰቀሰው የቱዋሬግ አመጽ አዛዋድ የተባለ የቱዋሬግ ሕዝብ ነፃ መንግሥት ለመመሥረት ሲጥር ነበር። የጃማአት ኑስራትን ምክትል መሪ አማዱ ኩፋ የፉላኒ ማኅበረሰብ አባል ነው።

ተንታኞች እንደሚያምኑት ማዕከላዊው አመራር በምዕራብ አፍሪካ የሳህል ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የአካባቢ ቅርንጫፎችን ለመምራት ቁልፍ ሚና አለው።

በቡድኑ ውስጥ ምን ያህል ተዋጊዎች እንዳሉ ወይም ምን ያህል በቅርብ ጊዜ እንደተመለመሉ በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት ብዙ ሺዎች ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኞቹ ተዋጊዎቹም የገቢ ምንጭ የሌላቸው ወጣት ወንዶች ናቸው።

ጀማአት ኑስራት አል-ኢስላም ፍላጎቱ ምንድን ነው?

የእስልምና እና የሸሪዓን ጥብቅ አተረጓጎም በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ለመጫን የሚፈልገው ቡድ የሳህል አካባቢ መንግሥታትን ሥልጣን አይቀበልም።

በአንዳንድ አካባቢዎች ቡድኑ ጥብቅ የአለባበስ ሕጎችን በማውጣት፣ ሙዚቃ እና ሲጋራ ማጨስን የሚከለክሉ እርምጃዎችን በመተግበር፣ ወንዶች ፂማቸውን እንዲያሳድጉ እና ሴቶች በሕዝብ ቦታዎች ብቻቸውን እንዳይገኙ በማዘዝ ይታወቃል ይላሉ ተንታኞች።

ይህ የእስልምና አተረጓጎም በአካባቢው ማኅበረሰቦች ከሚተገበረው ሃይማኖት ጋር ሊጣረስ ይችላል ይላሉ የቦን ዓለም አቀፍ የግጭት ጥናት ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ ኢቫን ጊቻውዋ።

"እነዚህ ልማዶች በግልጽ ከተቀመጡት አሠራሮች የላቁ ናቸው፤ እናም በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው የተወደዱ አለመሆናቸውን ነው" ይላሉ።

"ነገር ግን ማራኪም ይሁን አይሁን አገረ መንግሥቱ በሚያስችለው ነገር ላይ የተመሠረተ ነው። እና አገረ መንግሥቱ ላለፉት ዓመታት ሲያደርግ በነበረው ነገር ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ነበር።"

በዓለማዊው የፍትህ ሥርዓት ተስፋ መቁረጥ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን ማስተዋወቅ የአንዳንዶችን ቀልብ ሊስብ ይችላል።

ጀማአት ኑስራት አል-ኢስላም የት ነው የሚንቀሳቀሰው?

እንቅስቃሴው በማዕከላዊ እና በሰሜን ማሊ ከጀመረ በኋላ፣ ጀማአት ኑስራት አል-ኢስላም በፍጥነት ተደራሽነቱን አስፋፍቷል። ጠንካራ ምሽጎቹ በቡርኪናፋሶ፣ በማሊ እና በኒጀር ሲሆኑ፣ ነገር ግን በቤኒን፣ በቶጎ እና በአንድ ወቅት በአይቮሪ ኮስትም ጥቃት ፈጽሟል።

የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሚሠራው እና (ግሎባል ኢንሼቲቭ አጌኒስት ትራንስናሽናል ኦርጋናይዝድ ክራይም) በተሰኘው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሠረት ታጣቂ ቡድኑ በአሁኑ ጊዜ በመላው ማሊ እና ከ13ቱ የቡርኪና ፋሶ ግዛቶች በ11ዱ ይንቀሳቀሳል።

ባለፈው ዓመት ቡርኪናፋሶ በዋነኛነት የሰሜን እና ምሥራቃዊ ድንበር አካባቢዎች የቡድኑ እንቅስቃሴ ማዕከል ሆነዋል።

ይህ የሆነበት ምክንያት በሀገሪቱ ወታደራዊ ክፍል ውስጥ መከፋፈል እና መክዳት እንዲሁም ታጣቂዎቹ በአካባቢው ማኅበረሰቦች ውስጥ ምን ያህል ስር እንደሚሰደዱ የደኅንነት አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተንታኝ ቤቨርሊ ኦቺንግ ተናግራለች።

"ጀማአት ኑስራት በአከባቢው ማኅበረሰቦች ውስጥ ሰርጾ የመግባት ችሎታ ወይም አካባቢያዊ ቅሬታዎችን ለምልመላ እንዲሁም የሰዎችን ልብ ለማሸፈት መጠቀም ይችላል" ቤቨርሊ ለቢቢሲ ገልጻለች።

የጀማአት ኑስራት አል-ኢስላም ጥቃቶች እየጨመሩ ነው?

ከቅርብ ወራት ወዲህ በቡርኪናፋሶ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሁከት እና ብጥብጥ ድርጊቶች ጨምረዋል ሲል የቢቢሲ ሞኒተሪንግ የጂሃዲስት ሚዲያ ቡድን ትንታኔ አመልክቷል። በቅርቡም በማሊ፣ በኒጀር እና በቤኒን ከፍተኛ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

በዚህ ዓመት አጋማሽ ጂሃዲስት ቡድኑ በቡርኪናፋሶ ከ280 በላይ ጥቃቶችን ፈጽሟል። እነዚህ ጥቃቶች በ2024 ለተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸሩ ቁጥሩ በእጥፍ ማደጉን በቢቢሲ የተረጋገጠ መረጃ ያሳያል ።

ቡድኑ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በሳህል ዙሪያ ወደ 1,000 የሚጠጉ ሰዎችን መግደሉን ተናግሯል፣ አብዛኞቹ የደኅንነት አባላት ወይም ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የሚዋጉ ሚሊሻዎች መሆናቸውን የቢቢሲ ሞኒተሪንግ መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህ ውስጥ ወደ 800 የሚጠጉት በቡርኪናፋሶ ብቻ ናቸው። ሁለተኛው ከፍተኛ የግድያ ቁጥር የተመዘገበው በማሊ ሲሆን 117 ሰዎች ተገድለዋል፤ በቤኒን የተገደሉት ሰዎች ደግሞ 74 ናቸው።

"በሰኔ ወር የደረሰው የጥቃት ድግግሞሽ እስካሁን ተሰምቶ አይታወቅም" የሚሉት ጊቻውዋ፤ "በእርግጥ ባለፉት ሳምንታት ተግባራቸውን አጠናክረዋል" ብለዋል።

ታጣቂዎቹ ከፍተኛ የሆነውን ጉዳት ለማድረስ እንዲረዳቸው የተነደፉ የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማሉ ስትል ቤቨርሊ ኦቺንግ ታስረዳለች።

"በወሳኝ መንገዶች ላይ የረዥም ርቀት አቅም ያላቸው ፈንጂዎችን ይቀብራሉ። [በተጨማሪም] በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ የፀጥታ ኃይሎችን ዒላማ ያደርጋሉ። ስለዚህ ብዙ መሳሪያቸውን የሚያገኙት ከዚያ ነው። ማኅበረሰቦች ከመንግስት ጋር የተባበራሉ ተብሎ በሚታሰብባቸው አጋጣሚዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይም ጥቃት ፈጽመዋል።"

ድንበር ዘለል የተደራጁ ወንጀሎችን ላይ የሚሰራው ጂ-ቶክ የተሰኘው ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በቢሊየነሩ ኢሎን መስክ የሚተዳደረው እና ኢንትርኔት በሳተላይት የሚያቀርበው ስታርሊንክ እንዲሁም አቅማቸውን ለማሳደግ እንደ ጃማት ኑስራት ባሉ ቡድኖች ጥቅም ማግኛ መሆኑን አመልክቷል።

ኩባንያው መደበኛ የሞባይል ኔትወርኮች የማይገኙበት ወይም የማይታመኑበት ባለከፍተኛ ፍጥነት ኢንተርኔት ያቀርባል።

ታጣቂ ቡድኖች የስታርሊንክ መሳሪያዎችን በኮንትሮባንድ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያስገቡ ጂ-ቶክ ተናግሯል።

የጂ-ቶክ ተንታኝ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ፖድካስት እንደተናገረው "ስታርሊንክ [ለታጣቂ ቡድኖች] ጥቃቶችን ለማቀድ እና ለማስፈጸም፣ መረጃን ለመለዋወጥ፣ አባላትን ለመመልመል፣ የገንዘብ ልውውጥ ለማድረግ እና ከአዛዦቻቸው ጋር ግንኙነት ለመፍጠር በጣም ቀላል አድርጓል።"

ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጥ ስታርሊንክን ለማነጋገር ሞክሮ ነበር።

የጀማአት ኑስራት አል-ኢስላም ገንዘብ ከየት ያገኛል?

ቡድኑ በርካታ የገቢ ምንጮች አሉት።

በአንድ ወቅት ማሊ ውስጥ የውጭ ዜጎችን በማገት እና ማስለቀቂያ ገንዘብ በመተጠየቅ ገንዘብ ተሰብስቦ ነበር። ነገር ግን የፀጥታው ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ በሀገሪቱ ውስጥ የቀሩት የውጭ ዜጎች ጥቂቶች ናቸው።

በማሊ ደኅንነታቸውን አደጋ ላይ ሊጥል ስለሚችል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የጂ-ቶክ ተንታኝ እንደሚሉት የቀንድ ከብት መዝረፍ ከፍተኛ የቡድኑ የገቢ ምንጭ ሆኗል።

"ማሊ ትልቅ ከብቶችን ላኪ በመሆኗ እንስሳትን ዘርፈው መሸጥ ቀላል ይሆንላቸዋል" ብለዋል ተንታኙ።

በጂ-ቶክ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በአንድ ዓመት ውስጥ በአንድ የማሊ አውራጃ ታጣቂ ቡድኑ ከቁም እንስሳት 770,000 ዶላር አግኝቷል። በዚህ አሃዝ መሠረት፣ ጀማአት ኑስራት ከከብቶች ዝርፊያ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እያገኘ ሊሆን ይችላል።

በተጨማሪም እንደ ባለሙያዎች ገለጻ ታጣቂ ቡድኑ የተለያዩ ግብሮችን ይጥላል።

"ወርቅን ታክስ ያደርጋሉ፤ ነገር ግን በግዛታቸው ውስጥ የሚያልፍ ማንኛውንም ነገር፣ የተዘረዘሩ እቃዎችም ይሁኑ ሕገወጥ እቃዎች ግብር ያስከፍላሉ" ይላል ጂ-ቶክ።

"ጀማአት ኑስራት ለዜጎች ለጥበቃ ሲባል መክፈል እንዳለባቸው የሚነግራቸው ከዝርፊያ የማይተናነስ የታክስ ዓይነት ሊኖር ይችላል።"

ታጣቂዎቹ እገዳዎችን በማዘጋጀት ሰዎች ወደ አንድ አካባቢ ለመግባት ወይም ለመውጣት ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅ ይታወቃሉ ትላለች ቤቨርሊ ኦቺንግ።

ቡድኑን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረት ምን ይመስላል?

የፈረንሳይ ጦር በማሊ የሚገኘውን መንግሥት እየደገፈ ለአስር ዓመታት ያህል በአገሪቱ ውስጥ ነበረ። ከ4,000 በላይ የፈረንሳይ ወታደሮች በሳህል ቀጠና ሰፍረው ጀማአት ኑስራትን የመሠረቱትን ታጣቂ ቡድኖች ሲዋጉ ነበር።

እ.ኤ.አ. በ2013 እና 2014 ከታጣቂዎች ግዛትን ማስለቀቅ እና በርካታ ከፍተኛ አዛዦችን መግደል ጨምሮ አንዳንድ ወታደራዊ ስኬቶች መታየት ቢጀምሩም፤ ይህ ግን ጀማአት ኑስራት አል-ኢስላም ዋል-ሙስሊሚን ከተቋቋመ በኋላ ያሳየውን መስፋፋት ግን መግታት አልቻለም።

የጂ-ቶክ ተንታኝ "ጀማአት ኑስራትን በወታደራዊ ጥቃት መርታት ይቻላል በሚለው ሃሳብ ምክንያት የፀረ-ሽምቅ ጥረቶች እስካሁን አልተሳኩም፤ ነገር ግን በድርድር ብቻ ነው ቡድኑ የሚያበቃው" ሲሉ ጠቁመዋል።

እ.ኤ.አ. በ2014 የሳህል ሀገራት በአንድነት 5,000 ጠንካራ የዓለም አቀፍ ወታደሮች ያሉትን ጂ 5 የሳህል ግብረ ኃይል ቡድን መሥርተዋል። ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት ዓመታት ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር ቡድኑን ጥለው መውጣታቸው የግብረ ኃይሉ አማፂያንን ለመመከት ያለውን አቅም አሳጥቷል።

ሚኑስማ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል የፀረ-ሽምቅ ጥረት ባይሆንም ጥረቶችን ለመደገፍ ለአስር ዓመታት በማሊ ውስጥ የነበረ ቢሆንም በ2024 መጨረሻ ላይ ሀገሪቱን ለቅቆ ወጥቷል።

ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች በቡድኑ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድረዋል?

በ2020 እና 2021 በማሊ፣ በ2022 በቡርኪናፋሶ እንዲሁም በ2023 ኒጀር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥታት ተካሂደዋል።

በቡርኪናፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር በወታደራዊ አስተዳደር ስር ያለው ደካማ አስተዳደር በመቀጠል እንደ ጀመአት ኑስራት ያሉ ታጣቂ ቡድኖች እንዲያብቡ አስችሏቸዋል ሲሉ ተንታኞች ገልጸዋል።

እነዚህ ጁንታዎች የፈረንሳይ ወታደሮችን ከአገራቸው ለቀው እንዲወጡ ለመንገር በሩሲያ ድጋፍ እና በሦስቱ የሳህል ሀገራት የተቋቋመው ጥምር ጦር ለመተካት አፍታም አልወሰደባቸውም።

ምንም እንኳን የሩሲያው ቅጥረኛ ቡድን ቫግነር ወታደሮቹን ከማሊ ሙሉ በሙሉ ቢያስወጣም በክሬምሊን ቁጥጥር ስር ያለዉ አፍሪካ ኮርፕስ አሁንም እንዳለ ይቆያል።

በቡርኪናፋሶ፣ ወታደራዊ ወረራ ከመጀመሩ በፊት በ2020 የጀመረው "ፍቃደኛ" እየተባለ የሚጠራው ጦር ታጣቂዎችን ለመዋጋት አንዱ ስትራቴጂ ነው። የሁንታ መሪው ኢብራሂም ትራኦሬ 50,000 ተዋጊዎችን ለመመልመል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ።

ነገር ግን ብዙዎቹ እነዚህ በጎ ፈቃደኞች በግዳጅ ለውትድር እና አገልግሎት እንደሚመለመሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በቂ ያልሆነ ሥልጠና በማግኘታቸውብዙ ጊዜ ከባድ ጉዳት ይደርስባቸዋል። እንዲሁም ብዙውን ጊዜ የጀማአት ኑስራት ጥቃቶች ዒላማ ናቸው።

በቡርኪናፋሶ እና በማሊ የሚገኙ ወታደራዊ ጁንታዎች በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተለይም በፉላኒዎች ላይ አሰቃቂ ግፍ ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ብዙ ጊዜ መንግሥት የፉላኒ ማኅበረሰብን ከእስልምና ሃይማኖት ታጣቂ ቡድኖች ጋር ያምታታቸዋል፤ ይህም የሰላም ጥረቶችን የበለጠ እንዳደናቀፈ ገልጿል።

ከጥር 2024 እስከ መጋቢት 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ወታደራዊው መንግሥት እና የሩሲያ አጋሮቻቸው በማሊ ውስጥ ለ1,486 ሲቪሎች ጉዳት ተጠያቂ ናቸው ሲል ጂ-ቶክ ሪፖርት አድርጓል።

ይህ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ከፍተኛ ጥቃት በመንግሥት ላይ ቁጣን ቀስቅሷል፣ ይህም ለጀማአት ኑስራት ተጨማሪ ምልመላ እንዲጨምር አድርጓል።