ሩሲያ በኒውክሌር ኃላፊዋ ጄነራል ግድያ ተጠርጣሪ ያዘች

ሩሲያ በኒውክሌር ኃላፊዋ ጄነራል ኢጎር ኪርሎቭ እና በረዳታቸው ግድያ የኡዝቤኪስታን ዜግነት ያለው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች።

የአገሪቱ የኒውክሌር፣ ኬሚካል እና ባዮሎጂካል መከላከያ የሆኑት ጄኔራሉ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ነው ከመኖሪያ ቤታቸው ቤታቸው ህንጻ ሲወጡ በዩክሬን በተቀነባበረ ጥቃት የተገደሉት።

ጄነራሉ እና ረዳታቸው አሊያ ፖሊካርፖብ ብስክሌት መሳይ በሆነ (የኤሌክስትሪክ ስኩተር) ውስጥ በተደበቀ እና ከርቀት በሚቆጣጠሩት ቦምብ ነው ህይወታቸውን ያጡት።

ስሙ ይፋ ያልተደረገው ተጠርጣሪ በዩክሬን ልዩ አገልግሎት መመልመሉን ማመኑን የሩሲያ የምርመራ ኮሚቴ (ኤስኬ) አስታውቋል። ኮሚቴው ክሱን የሚያጠናክር ተጨማሪ መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥቧል።

የዩክሬን የጸጥታ አገልግሎት ከግድያው ጀርባ አለሁበት ሲል ኃላፊነት መውሰዱን አንድ ምንጭ ማክሰኞ ዕለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እኚህ የዩክሬን ምንጭ እንደተናገሩት የ54 ዓመቱ ጄነራል ኢጎር የጦር ወንጀል በመፈጸማቸው "ኢላማ ተደርገዋል" ብለዋል።

ግድያው ከመፈጸሙ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ዩክሬን ይህንኑ የሩሲያ ጄነራል "የተከለከሉ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች በገፍ በመጠቀም ተጠያቂ" ናቸው ስትል ክስ በሌሉበት መስርታ ነበር። ሩሲያ ይህንን ውንጀላ አትቀበለውም።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጄነራሉ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን መግለጻቸውን የሩሲያ መንግሥታዊ የዜና ወኪል ታስ የክሬምሊን ቃል አቀባይን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በጄነራሉ ግድያ ተጠርጥሮ የታሰረው ግለሰብ በአውሮፓውያኑ 1955 የተወለደ የኡዝቤኪስታን ዜጋ መሆኑን ኮሚቴው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

"የሽብር ተግባር በመፈጸም ተጠርጥሯል" እንዲሁም በምርመራ ወቅት "በዩክሬን ልዩ አገልግሎት እንደተመለመለ አምኗል" ሲል ኮሚቴው አትቷል።

ፈንጂው ጄኔራሉ በሚኖሩበት ህንጻ መግቢያ አጠገብ በቆመ ስኩተር ላይ በድብቅ መገጠሙን ኤስኬ አስታውቋል።

ቦምቡን ለመከታተል ተጠርጣሪው መኪና ተከራይቶ እንደነበር፣ በተጨማሪም በዩክሬን ዲኒፕሮ ከተማ ለጥቃቱ አስተባባሪዎች በቀጥታ እንዲተላለፍ የቪዲዮ ካሜራ ጭኖ እንደነበር መርማሪ ኮሚቴው አክሎ ገልጿል።

ጄነራሉ ረዳታቸው የመኖሪያ ህንጻውን ለቀው ሲወጡ ፈንጂው በርቀት መቆጣጠሪያ ፈንድቷል ይላል መግለጫው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ የፌደራል ደህንነት አገልግሎት (ኤፍኤስቢ) ተጠርጣሪው ምርመራ ሲደረግለት የሚያሳይ ቪዲዮ ይፋ አድርጓል። በቪዲዮው ላይ አንድ ጠቆር ያለ ጸጉር ያለው በካቴና የታሰረ ግለሰብ ካሜራውን እያየ ሲናገር ይታያል።

ጄነራሉን ለመግደል የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት እንዲሁም የአውሮፓ ፓስፖርት ሊሰጠው እንደሆነ በሩስኪ ቋንቋ ሲናገር ተደምጧል።

በዩክሬን መመሪያ መሰረት ወደ ሞስኮ እንደደረሰ እና በቤት ውስጥ የሚሰራ ተቀጣጣይ ፈንጂ ተቀብሏል ተብሏል። የተጠርጣሪው የእምነት ክህደት ቃል በግዳጅ የተገኘ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።