እስራኤል በጋዛ ላይ በምታካሂደው የእግረኛ ጦር ዘመቻ ምን ማድረግ ትፈልጋለች?

የእስራኤል መሪዎች ሐማስን ከጋዛ ጠራርገው ለማጥፋት ዝተዋል፣ በዚህም ሳቢያ ጋዛ ከዚህ በፊት የነበራት ገጽታ ባለበት የሚቀጥል አይመስልም።

ሐማስ ድንገተኛውን ከባድ ጥቃት በእስራኤል ላይ መፈጸሙን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ “እያንዳንዱ የሐማስ መሪ በሞት ጥላ ነው” በማለት የበቀል በትራቸው በቡድኑ መሪዎች ላይ እንደሚያተኩር ተናግረዋል።

ለዚህ የበቀል እርምጃ “የብረት ጎራዴዎች” (ስዎርድስ ኦፍ አይረን) ብላ እስራኤል በሰየመችው ዘመቻ፣ የጦር ኃይሏ ከዚህ በፊት በጋዛ ላይ ካካሄዳቸው ዘመቻዎች በእጅጉ የሰፋ ግብን ያነገበ ነው። ነገር ግን ይህ ወታደራዊ ተልዕኮ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው? እና የጦሩ መሪዎች እንዴት አድርገው ሊያሳኩት ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ይነሳበታል።

በጋዛ ሰርጥ ውስጥ የሚካሄድ የእግረኛ ወረራ በከተማ ውስጥ ቤት ለቤት የሚካሄድ ውጊያን እና በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ከባድ አደጋን የሚደቅን ነው። ባለፈው አንድ ሳምንት በጋዛ ላይ የተፈጸመው የአየር ድብደባ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችን ሲገድል፣ ከ400,000 በላይ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።

የእስራኤል እግረኛ ሠራዊት ወደ ጋዛ ሲዘምት የሐማስ መሪዎችን እና ተዋጊዎችን ከማደን በተጨማሪ፣ ባልታወቁ የተለያዩ የጋዛ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ቢያንስ 150 ናቸው የተባሉ ታጋቾችንም የማስለቀቅ ተልዕኮን ይዞ ነው።

የእስራኤል ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሄርዚ ሃሌቪ፣ በጋዛ ያሉትን የሐማስ የፖለቲካ አመራሮችን ለይቶ በመምታት ቡድኑን “ለመበታተን” ዝተዋል። ነገር ግን ለ16 ዓመታት በጋዛ ላይ የቆየው የሐማስ የበላይነት ሲወገድ ጋዛ ምን ልትመስል እንደምትችል ምን የታሰበ ነገር አለ? የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።

“እስራኤል የሐማስ አባላትን በመበታተን ቡድኑን ከእንቅስቃሴ ውጪ ታደርጋለች ብዬ አላስብም፤ ምክንያቱም ቡድኑ ያነገበው የጽንፈኛ እስልምና ሃሳብን ነውና” የሚሉት በእስራኤል ጦር ሠራዊት ራዲዮ ውስጥ ወታደራዊ ተንታኙ አሚር ባር ሻሎም “ነገር ግን ጥቃት አስከማይፈጽምበት ደረጃ ድረስ ሊዳከም ይችላል” ይላሉ።

ሐማስን የማዳከም ዓላማ ሊሳካ የሚችል ነው ሊባል ይችላል። ቢሆንም ከዚህ በፊት እስራኤል አራት ጦርነቶችን ከሐማስ ጋር ብትዋጋም የሐማስን የሮኬቶች ጥቃትን ለማስቆም የተደረጉት ሁሉም ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል።

የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ጆናታን ኮንሪሺየስ እንዳሉት፣ በዚህ ዙር ጦርነት ማብቂያ ላይ ከዚህ በኋላ ሐማስ “እስራኤላውያን ሲቪሎችን ለማስጋት ወይም ለመግደል” አቅም እንዳይኖረው ማድረግ ያስፈልጋል።

የእግረኛ ወረራ የሚያስከትለው አደጋ

ወታደራዊውን ዘመቻ ሊያደናቅፉ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታመናሉ።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ኢዘዲን አል-ቃሳም እስራኤል ለምትከፍተው የእግረኛ ጦር ጥቃት ሊዘጋጅ ይችላል። በዚህም ፈንጂዎችን ማጥመድ እና የደፈጣ ጥቃቶችን ማቀዱ አይቀርም። በተጨማሪም አስቸጋሪውን ከመሬት በታች ያሉትን ዋሻዎች በመጠቀም በእስራኤል ኃይሎች ላይ ጥቃት ሊፈጽም ይችላል።

በ2014 (እአአ) በጋዛ ከተማ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ በተካሄደው ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች በተገደሉበት ጊዜ፣ የእስራኤል እግረኛ ሠራዊት በፀረ ታንክ ፈንጂዎች፣ በአልሞ ተኳሾች እና በደፈጣ ጥቃቶች ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።

አሁን አስራኤል ልታካሂደው ካሰበችው የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ በፊት ከጋዛ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙ 1.1 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያቸውን ለቀው እንዲወጡ አዛለች።

እስራኤል ካላት መደበኛ ሠራዊት በተጨማሪ አሁን ልታካሂድ ላሰበችው ዘመቻ 360,000 የተጠባባቂ ሠራዊት አባላትን የጠራች ሲሆን፣ ጦርነቱ ወራት ሊወስድ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ነው።

በዚህ ሁኔታ እስራኤል በጋዛ ውስጥ የምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከጋዛ እንድትወጣ ጫና ሳይፈጠርባት ምን ያህል ጊዜ ልትቆይ ትችላለች የሚል ጥያቆም ይነሳል።

በአንድ ሳምንት ውስጥ በተፈጸመባት የአየር ድብደባ ከባድ ውድመት የገጠማት ጋዛ በፍጥነት “ሲኦል” እየሆነች ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት አስጠንቅቋል።

ጋዛ ውስጥ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሲሆን የውሃ፣ የኤሌክትሪክ እና የነዳጅ አቅርቦት ተቋርጧል። ከሕዝቡም ግማሹ መኖሪያውን ለቆ እንዲወጣ ተነግሮታል።

“የእስራኤል መንግሥት እና ሠራዊት ቢያንስ የምዕራብ አገራት መሪዎች እንዲሁም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ድጋፍ አለን ብለው ያስባሉ። ስለዚህም ያለው እሳቤ ‘ጊዜ ስላለን እርምጃ እንውሰድ’ የሚል ነው” ሲል በእስራኤል ዋነኛ የሚባለው የደኅንነት እና የስለላ ጋዜጠኛ የሆነው ዮሲ ሜልማን ይናገራል።

ነገር ግን በቅርቡ ወይም ቆይቶ የእስራኤል አጋሮች የሰዎች መራብን የሚያሳዩ ምስሎች ከወጡ ጣልቃ ይገባሉ ብሎም ያስባል።

ታጋቾችን ማስለቀቅ

ከታጋቾቹ መካከል ብዙ እስራኤላውያን ቢኖሩበትም፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭ ዜጎች እና ጥምር ዜግነት ያላቸው ሰዎችም ከመካከላቸው ይገኛሉ። በዚህም ሳቢያ አሜሪካን፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ አገራት በእገታው ዙሪያ የሚመለከታቸው ጉዳይ አለ።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን “ፈረንሳይ ልጆቿን ፈጽሞ አትተዋቸውም” በማለት የታገቱ ዜጎቻቸውን በማስለቀቅ ወደ አገራቸው ለመመለስ ቃል ገብተዋል።

የታጋቾቹ ዕጣ ፈንታ ጉዳይ በወታደራዊ ዕቅድ አውጪዎች ላይ ተጽእኖ አሳድሮ ስለመሆኑ ገልጽ የሆነ ነገር የለም፤ በተጨማሪም በእስራኤል መሪዎች ላይ የአገር ውስጥ ተጽእኖም አለ።

ይህንን ሁኔታ አሚር ባር ሻሎም በ1972 (እአአ) የፍልስጥኤም ታጣቂዎች እስራኤላውያን አትሌቶችን በማገት 11 ሰዎችን ከገደሉበት የሙኒክ ኦሊምፒክ ጋር ያነጻጽሩታል።

በወቅቱ የእስራኤል መንግሥት በዚህ እገታ ውስጥ የተሳተፉትን እያንዳንዳቸውን ታጣቂዎች አድኖ ለመግደል ዘመቻ አካሂዷል።

አሁን በሐማስ ታጣቂዎች ታግተው በተለያዩ የጋዛ ክፍል ውስጥ ተይዘው የሚገኙ ሰዎችን ፈልጎ ለማስለቀቅ ሳዬሬት ማትካል ከተባለው የእስራኤል ልዩ የኮማንዶ ቡድን አቅም በላይ ሊሆን ይችላል። ሐማስ በበኩሉ እስራኤል በጋዛ ላይ ጥቃት ከከፈተች ታጋቾችን እንደሚገድል አስጠንቅቋል።

ለአምስት ዓመታት በሐማስ ተይዞ የቆየውን ወታደሯን ለማስለቀቅ ስትል እስራኤል በ2011 (እአአ) በልዋጩ ከ1,000 በላይ እስረኞች መልቀቋ ይታወቃል። አሁን ግን እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የእስረኞች ልውውጥ ከማድረጓ በፊት ሁለት ጊዜ ማሰቧ አይቀርም።

ለዚህም ምክንያቱ በቀደመው የእስረኞች ልውውጥ ወቅት ከለቀቀቻቸው ፍልስጥኤማውያን መካከል ያህያ ሲንዋር አንዱ ሲሆን፣ ከእስር ከወጣ በኋላ ጋዛ ውስጥ የሐማስ ፖለቲካዊ መሪ በመሆኑ አሁን ከምትፈልጋቸው የቡድኑ መሪዎች አንዱ ነው።

የጎረቤት አገራት ምላሽ

ሌላው እስራኤል በጋዛ ላይ በምታካሂደው የእግረኛ ጥቃት የጊዜ ርዝመት ላይ ውጤት ሊኖረው የሚችለው በዙሪያዋ ያሉት ጎረቤት አገራት የሚሰጡት ምላሽም አንዱ ነው።

ከእነዚህም መካከል ከጋዛ ሰርጥ ጋር ድንበር ከምትጋራው ከግብፅ በኩል የሚቀርቡ ተደራራቢ ጥያቄዎች ሊኖሩ መቻላቸው ነው። አሁንም ግብፅ ከግዛቷ ወደ ጋዛ ለመግባት በሚያስችለው የራፍህ መተላለፊ በኩል አርዳታ እንዲገባ እየጠየቀች ነው።

“በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ጋዛ ውስጥ ጉዳት እየደረሰ ሲሄድ፣ ግብፅ ለፍልስጥኤማውያን ጀርባዋን የሰጠች ስለሚያስመስላት ጫና ይበረታባታል” ይላሉ ከእስራኤል ብሔራዊ የደኅንነት ጥናት ተቋም የሆኑት ኦፊር ዊንተር።

ነገር ግን ይህ ጫና ግብፅ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ግዛቷ እንዲገቡ እንድትፈቅድ ወይም ወይም በእስራኤል ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንድትወስድ እስከ መፈለግ ይደርሳል ብለው አያምኑም።

በሰሜን በኩል ከሊባኖስ ጋር እስራኤልን የሚያጎራብታት የድንበር አካባቢም በጥንቃቄ የሚታይ ነው።

ባለፉት ቀናትም ሊባኖስ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው እስላማዊው ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችን ቢፈጽምም፣ ይህ በእስራኤል ላይ የተከፈተ ሌላ የጦርነት ግንባር ነው ብለው የሚያዩት አይደለም።

የሄዝቦላህ ዋነኛ ደጋፊ የሆነችው ኢራን በእስራኤል ላይ “አዲስ ግንባር” እንደምትከፍት መዛቷን ተከትሎ፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት “ይህንን ሁኔታ ለራሱ ለመጠቀም ለሚያስብ የትኛውም አገርም ሆነ ድርጅት አንድ ቃል ብቻ ነው ያለኝ፤ ይህም ‘አታድርጉት!’ የሚል ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል።

ይህንን የፕሬዝዳንቱን ማስጠንቀቂያ የበለጠ ለማጠናከር እና ለእስራኤል ድጋፏን ለማሳየት የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧን ወደ ምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን ባሕር ክፍል ልካለች።

የጋዛ ዕጣ ፈንታ

ሐማስ በከፍተኛ ደረጃ የሚዳከም ከሆነ፣ ቦታውን ማን ሊይዝ ይቻላል የሚለው ጥያቄ ይነሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ የነበራትን ሠራዊት እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰፋሪዎቿን በ2005 (እአአ) ስላስወጣች ወደ ግዛቲቱ በወራሪ ኃይልነት ተመልሳ የመግባት ፍላጎት አይኖራትም።

በጋዛ ውስጥ የበላይነት ያለው ሐማስ ከተዳከመ በ2007 (እአአ) ከጋዛ በሐማስ የተባረረው ታጣቂ ቡድን ያልሆነው እና በከፊል ዌስት ባንክን የሚያስተዳድረው የፍልስጥኤም ባለሥልጣን ቀስ በቀስ ወደ ጋዛ የሚመለስበት በር ይከፈታል ብለው ኦፊር ዊንተር ያምናሉ።

ጨምሮም ግብፅ በፋታህ የሚመራው የፍልስጥኤም ባለሥልጣን ከሁኔታዎች ጋር እራሱን እያስማማ የሚሄድ የጋዛ አስተዳደር መኖሩን ትደግፈዋለች ብሎ ይጠቅሳል።

ሌላው ደግሞ በጋዛ ውስጥ ቀደም ሲል በተካሄዱ ጦርነቶች ጭምር የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።

ሐማስ እስራኤል ላይ ከፈጸመው የአሁኑ ጥቃት ቀደም ብሎ ጀምሮ እስራኤል በተመሳሳይ ለሰላማዊ እና ለወታደራዊ አገልግሎቶች ሊውሉ የሚችሉ ሸቀጦች ወደ ጋዛ እንዳይገቡ በጥብቅ ስትቆጣጠር ቆይታለች። ከዚህ በኋላ ደግሞ የበለጠ ዕቀባውን በጋዛ ላይ ለመጣል ፍላጎት ይኖራታል።

በተጨማሪም ለእስራኤላውያን ማኅበረሰቦች የበለጠ ጥበቃ ለማድረግ በጋዛ ድንበር ላይ ካለው አጥር ዙሪያ ሰፋ ያለ የመከላከያ ቀጠና ጋዛ ውስጥ እንዲኖር ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል።

የእስራኤል የአገር ውስጥ ደኅንነት አገልግሎት ሺን ቤት የቀድሞው ኃላፊ ዮራም ኮኸን፣ አሁን ያለውን የደኅንነት ቀጠና የሚተካ አልፎ የገባን “ተኩሶ ለመግደል” የሚያስችል ሁለት ኪሎ ሜትር ወደ ጋዛ ውስጥ የሚሆን ቀጠና መኖር አለበት ብለው ያምናሉ።

አሁን እስራኤል በጋዛ ውስጥ ልታካሂድ እየተዘጋጀችበት ያለው በጋዛ ላይ የምታካሂደው የእግረኛ ሠራዊት ወታደራዊ ዘመቻ የሚያመጣው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ እስራኤል ተመሳሳይ ጥቃት በድጋሚ እንዳይፈጸምባት የማድረግ ፍላጎት አላት።