ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራናውያን በዋጋ ንረት የተነሳ ለሦስተኛ ቀን ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል
በኢራን የዋጋ ግሽበትና የገንዘብ የመግዛት ዋጋ መቀነስን ተከትሎ የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች እና የሥራ ማቆም አድማዎች ከዋና ከተማዋ ቴህራን ወደ ሌሎች በርካታ ከተሞች ተዛምተው ለሦስተኛው ቀን ቀጥለዋል።
ተቃውሞው የተቀሰቀሰው እሁድ ዕለት የኢራን ሪአል ከአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ደረጃ በማሽቆልቆሉ በቴህራን የሚገኘው ግራንድ ባዛር ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ካደረጉ በኋላ ነው።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቢቢሲ ፐርሺያ የተረጋገጡ ቪዲዮዎች በካራጅ፣ በሃሜዳን፣ ቄሽም፣ ማላርድ፣ ኢስፋሃን፣ ኬርማንሻህ፣ ሺራዝ እና ያዝድ ከተሞች የተቃውሞ ሠልፎች መካሄዳቸውን ያሳያሉ።
ፖሊስም ሠልፈኞቹን ለመበተን የአስለቃሽ ጋዝ ተጠቅሟል።
የኢራን መንግሥት "የተቃውሞ ሠልፎቹን እንደሚረዳ" እና "ጠንካራ ተቃውሞዎች ቢቀርቡም እንኳ በትዕግስት እንደሚያዳምጥ" ተናግሯል።
ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ሰኞ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ እንደጻፉት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተቃዋሚዎቹ "ተወካዮች" ጋር ውይይት እንዲያደርጉ እንዲሁም "ችግሮቹን ለመፍታት እና በኃላፊነት ስሜት ለመንቀሳቀስ" እርምጃዎች እንዲወሰዱ መመሪያ ሰጥተዋል።
የኢራን ማዕከላዊ ባንክ ገዥ የነበሩትን መሐመድሬዛ ፋርዚን ያስገቡትን የሥራ መልቀቂያ ተቀብለው በምትካቸው የቀድሞ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሚኒስትር አብዶልናሰር ሄማቲን ሾመዋል።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች "ሞት ለአምባገነኖች" የሚሉ መፈክሮችን በማሰማት ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል።
ይህም በኢራን ውስጥ የመጨረሻውን ሥልጣን የያዙትን የጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኒ የሚያመለክት ነው ተብሏል።
አንዳንድ ተቃዋሚዎች እአአ በ1979 የእስልምና አብዮት ከሥልጣን የተወገዱትን የሟቹን የሻህ መሐመድ ሬዛ ፓህላቪን ልጅ በመደገፍ "ሻህ ለዘላለም ይኑር" የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙም ተሰምተዋል።
በምላሹም፣ በዩናይትድ ስቴትስ በስደት የሚኖሩት ሬዛ ፓህላቪ በኤክስ ገጻቸው ላይ "ከእናንተ ጋር ነኝ። ዓላማችን ፍትሃዊ ስለሆነ እና አንድ ስለሆንን ድል የእኛ ነው" ብለዋል።
"ይህ አገዛዝ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ መንኮታኮቱ ይቀጥላል" ሲሉ አክለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ ገፁ ላይ በፋርስ ቋንቋ ለተቃውሞ ሠልፈኞቹ ድጋፍ ሰጥቷል።
አሜሪካ "ጥንካሬያቸውን እንደምታደንቅ" እና ለዓመታት በማይሰሩ ፖሊሲዎች እና ብልሹ የኢኮኖሚ አስተዳደር በኋላ "ክብር እና የተሻለ መጻዒ ዕድል" ከሚፈልጉ ጎን እንደምትቆም አስታውቋል።
ሰኞ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በፍሎሪዳ በተደረገው ስብሰባ ኢራን ዋነኛ አጀንዳ ሆና እንደነበር ተዘግቧል።
ከውይይቱ በኋላ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ትራምፕ በኢራን የሥርዓት ለውጥ እንዲደረግ ይደግፉ እንደሆን ተጠይቀው ከመመለስ ተቆጥበዋል።
ነገር ግን "ብዙ ችግሮች አሉባቸው፤ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ ኢኮኖሚያቸው ወድቋል፣ ኢኮኖሚያቸው ጥሩ አቋም ላይ አይደለም፣ እና ሰዎች ብዙም ደስተኛ እንዳልሆኑ አውቃለሁ" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አገሪቱ የባለስቲክ ሚሳኤል ወይም የኒውክሌር ፕሮግራሞቿን የምትቀጥል ከሆነ እስራኤል ዳግም የምትፈጽመውን የአየር ጥቃት ሊደግፉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በእስራኤል እና በኢራን መካከል ለ12 ቀናት በዘለቀው ጦርነት ወቅት፣ አሜሪካ ቁልፍ በሆኑ የኢራን የዩራኒየም ማበልጸጊያ ተቋማት ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።
ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ መሆኑን ትናገራለች።
ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን ማክሰኞ ዕለት ኢራን "ለማንኛውም የጭቆና ጥቃት" የምትሰጠው ምላሽ "ከባድ እና ጸጸት የሚያስከትል" እንደሚሆን ቃል ገብተዋል።
የኢራን ጠቅላይ መሪ በጦርነቱ ወቅት የእስራኤል መንግሥት በኢራን ውስጥ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች እንደሚቀሰቀሱና አገዛዙን እንደሚገለብጡ ተስፋ አድርገው እንደነበር በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ኻሜኒ በመስከረም ወር "በጎዳናዎች ላይ ዓመፅ መፍጠር ፈልገው ነበር... ነገር ግን ሰዎች ጠላት በሚፈልገው መንገድ ፈጽሞ አልተጓዙም" ሲሉ ተናግረው ነበር።