ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወደቦች፣ የኃይል ማመንጫዎች፣ የአየር ማረፊያዎች... ባለቤት የሆነው የእስያው ባለጸጋ አዳኒ
ወቅቱ በአውሮፓውያኑ ኅዳር 26/2008 ነበር።
በወቅቱ በሕንድ በባለጸጋነት በ10ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ጋኡታም አዳኒ በቦምቤይ ቅንጡ ከሆኑት ሬስቶራንቶች አንዱ በሆነው ታጅ ማሃል ሆቴል እየተመገበ ነበር።
ድንገትም ታጣቂዎች ድንገተኛ ተኩስ ከፈቱ። የእጅ ቦምቦችንም ሲወረውሩ ተመለከተ።
ከእስከ አፍንጫቸው የታጠቁ እና ዜግነታቸው ፓኪስታናዊ የሆኑ አስር ግለሰቦች በዚያች ምሽት ነበር፣ በባሕር ላይ ተጉዘው ሆቴሉ የደረሱት።
ሆቴሉም ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ በቡድን ተከፋፍለው ተሽከርካሪዎችን አገቱ፣ ኢላማ ያሏቸውንም አጠቁ፤ ከእነዚህም ውስጥም ሁለት ትልልቅ ሆቴሎች ይገኙበታል።
ታጣቂዎቹ ከተማዋን ለ60 ሰዓታት ያህል የከበቡ ሲሆን፣ በዚህም የ166 ሰዎች ሕይወት ተቀጠፈ እንዲሁም በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል ያለው ግንኙነትም የበለጠ ሻከረ።
በሆቴሉ ውስጥ የነበረው ጋኡታም በኋላ 'ኢንዲያ ቱደይ' ለተሰኘ መጽሄት እንደተናገረው፣ የሆቴሉ ሠራተኞች በፍጥነት የሆቴሉን እንግዶች ወደ ምድር ቤት ወስደው ለሰዓታት ያህል አስቀመጧቸው።
ደም አፋሳሹ ከበባ ከሆቴሉ ውጪ በቀጠለበትም ወቅት የመጨረሻ ፎቅ ላይ ወደ ሚገኘው አዳራሽ ወሰዷቸው።
በአዳራሹ ውስጥ 100 ያህል እንግዶች ታጭቀው ነበር “አንዳንዶች ከሶፋ ስር ተደብቀው ነበር፤ ሌሎች ደግሞ ማምለጫ የሚሆን ቦታን ይዘው ነበር” የሚለው ባለጸጋው በርካቶችም ሕይወታቸውን እንዲያተርፈው ለፈጣሪ ይጸልዩ እንደነበር ያወሳል።
አዳኒ በወቅቱ ሶፋ ላይ ተቀምጦ የነበረ ሲሆን፣ መውጫ ያጡትንም እንግዶች “እምነታቸውን በአምላክ ላይ እንዲጥሉ ነገራቸው።”
እናም 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የትውልድ ስፍራው፣ አህመዳባድ የሚገኙ ቤተሰቦቹ ጋር ደወለ። የጥበቃ ሠራተኛው እና ሹፌሩ ውጭ ሆነው መኪና ውስጥ በጭንቀት እየጠበቁት ነበር።
አዳራሹ ውስጥ ምሽቱን ካሳለፉ በኋላ በነጋታው ማለዳ ኮማንዶዎች ደርሰው አዳኒ እና ሌሎች ታጋቾችን በኋለኛው በር በኩል አስወጧቸው።
“ሞቴን በቅርብ ርቀት አየኋት” በማለት በግል ጄቱ ወደ አህመዳባድ ከተመለሰ በኋላ አዳኒ ለጋዜጠኞች ተናገረ።
ባለጸጋው ከሞት መንጋጋ ካመለጠ አስራ አራት ዓመታትን አስቆጠረ። በአሁኑ ወቅትም ከኤሎን መስክ እና ከጄፍ ቤዞስ ቀጥሎ ሦስተኛው የዓለማችን ቱጃር ነው - የ60 ዓመቱ አዳኒ።
ወደቦች፣ የኃይል ማመንጫ ኩባንያዎችን ጨምሮ በገበያ ካፒታላይዜሽን ላይ የሚሰሩ ትልልቅ ኩባንያዎች ያሉት አዳኒ በስሩ 23 ሺህ ሠራተኞችን ያስተዳድራል።
አንጡራ ሃብቱም 137.6 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።
ከሰሞኑ ባለጸጋው የሚዲያዎች መነገጋገሪያ ሆኗል።
ለዚህም ምክንያቱ በሕንድ ውስጥ ከፍተኛ ዝናና ክብርን ያገኘውን ኤንዲቲቪ የተሰኘውን የዜና አውታር የግሉ ለማድረግ መቃረቡን ተከትሎ ነው።
ትምህርቱን ያቋረጠው ነጋዴ ቢሊየነር ከመሆኑ በፊት ውጣ ውረዶችን በሕይወቱ አልፏል።
በአውሮፓውያኑ 1998 እሱና የሥራ ባልደረባው አህመዳባድ ውስጥ መኪናቸው ውስጥ እያሉ በታጠቁ ሰዎች ታገቱ። ገንዘብ ካልከፈሉም በነጻ እንደማይወጡ ተነገራቸው።
ሁለት ተጠርጣሪዎች ቢያዙም አዳኒ እና አጋሩ ፍርድ ቤት ተደጋጋሚ መጥሪያ ቢያደርግላቸው ክስ ለመመስረት ባለመምጣታቸው ተጠርጣሪዎቹ በአውሮፓውኑ 2018 በነጻ ተለቀቁ።
ትህትና የተሞላውና ራሱን ከፍ የማያደርገው አዳኒ ስለእነዚህ ክስተቶች ብዙም አያወራም። የሆነ ወቅት ለአንድ ጋዜጠኛ “በሕይወቴ ውስጥ ሁለት፣ ሦስት በጣም አሳዛኝ ክስተቶች ገጥመውኛል” ከማለት ውጪ ምንም ከማለት ተቆጥቧል።
በ16 ዓመቱ ትምህርቱን ያቋረጠው አዳኒ የሕንድ የንግድ ማዕከል ወደሆነችው ቦምቤይ የአልማዝ ሥራን ለመሞከር መጣ። ሆኖም ይህ ብዙ አላስቀጠለውም፣ አላዋጣውም። ከሁለት ዓመት በኋላም በወንድሙ የሚተዳደረውን የማሸጊያ ፋብሪካ ለማንቀሳቀስ ወደ ትውልድ ስፈራው ጉጅራት ተመለሰ።
የአዳኒ ቤተሰቦች መካከለኛ ገቢ ያላቸው ናቸው። ቤተሰቦቹ በጨርቃ ጨርቅ ንግድ ይተዳደሩ የነበረ ሲሆን፣ እሱም የመጀመሪያ ድርጅቱን በአውሮፓውያኑ 1998 በሸቀጦች ንግድ ነበር የጀመረው።
በሚቀጥሉት 24 ዓመታት ውስጥም በወደብ፣ በማዕድን፣ በባቡር፣ በመሠረ ልማት፣ ኃይል እና ሪል ስቴትን ጨምሮ ያልገባበት የንግድ ዘርፍ የለም።
በአሁኑ ወቅት አዳኒ የሕንድ የመሠረተ ልማት ባለጸጋ ነው ቢባል ድፍረት አይሆንም። በሕንድ ሁለተኛው ትልቁ የሲሚንቶ ኩባንያ፣ የአገሪቱን ትልቁን ምዕራባዊ የባሕር ጠረፍ ከተማ ሙንድራን ጨምሮ 13 ወደቦችን እንዲሁም ሰባት አየር ማረፊያዎችን ያስተዳድራል።
ዋና መዲናዋን ዴልሂን እና የንግድ ማዕከል የሆነችውን ቦምቤይን የሚያገናኘውን ረጅሙን የፈጣን መንገድንም [ኤክስፕረስ] እየገነባ ነው።
ስድስት ያህል የድንጋይ ከሰል የኃይል ማመንጫዎች ያሉት አዳኒ የሕንድ ከፍተኛው የኃይል አመንጪ ነው። በአረንጓዴ ሃይድሮጂን 50 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ገብቷል፤ እንዲሁም ስምንት ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የተፈጥሮ ጋዝ የቧምቧ መስመርም አለው።
በኢንዶኔዢያ እና በአውስትራሊያ የድንጋይ ከሰል ማምረቻዎችን ገዝቷል። በአውሮፓውያኑ 2030 የዓለማችን ቁንጮ የታዳሽ ኃይል አመንጪ ለመሆንም አቅዷል።
የፖሊሲ ተንታኝ የሆኑት ጄምስ ክራብትሪ “ዘ ቢሊዮነር ራጅ፣ ጆርኒ ስሩው ኢንዲያስ ኒው ጊልድድ ኤጅ’ በተሰኘ መጽሃፋቸው፣ አዳኒ ቢዝነሱን ያስፋፋበት ፍጥነት ከዚህ ቀደም ከነበረው የኢንዱስትሪ አብዮት ጋር ያወዳድሩታል።
“በሕንድ ያረጁ መሠረተ ልማቶች ላይ መተማመን ባለመቻሉ የራሱን የግል የባቡር ሀዲዶች እና የኤሌክትሪክ ኃይል መስመሮችን ገነባ። ከአገር ውስጥም የድንጋይ ከሰል በቀላሉ ማግኘት ባለመቻሉ በኢንዶኔዢያ እና በአውስትራሊያ የማዕድን ማውጫዎችን ገዛ። እነሱንም ራሱ በሚቆጣጠረው ወደብ በኩል ወደ ሕንድ ወሰደ” ብሏል ክራብትሪ።
አዳኒ በውዝግቦች የተከበበ ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የነበረው የጠበቀ ግንኙነት ዘመንን ተሻግሯል።
የጉጅራት ግዛት አስተዳዳሪ በነበሩበት ጊዜ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑም በኋላ ያላቸው ሽርክና፣ ተቺዎች የአዳኒ የንግድ ኢምፓየርን ክሮኒ ካፒታሊዝም ተብሎ የሚጠራውን የባለጸጎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥብቅ ወዳጅነት ዋነኛ ተምሳሌት ነው ይሉታል።
“ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲና አዳኒ በግንኙነታቸው ሁለቱም ተጠቃሚ ሆነዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢዝነስ ላይ ያላቸው ፖሊሲዎች አዳኒ ንግዱን መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ እንዲያስፋፋ ረድቶታል። የአዳኒ ኩባንያዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉጅራት ሞዴል ተብሎ በሚጠራውና መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ላይ በማተኮር የውጭ ካፒታል እና የወጭ ንግድ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት በሚልም መርኅ ላይ የተመረኮዘ ነው” ይላል ክራብትሪ።
በአውስትራሊያ ኩዊንስላንድ የሚገኘው የአዳኒ የድንጋይ ከሰል ማምረቻም ለዓመታት ያህል ከሰል ምርትን በሚቃወሙ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች መካከል ከፍተኛ ውዝግብን የፈጠረ ነው።
በመጨረሻም ከብዙ ክርክር በኋላ በአውሮፓውያኑ 2019 ግንባታው ተጀምሯል። በአውስትራሊያ ተቀማጭነቱን ያደረገውና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት የሆነው 'አዳኒ ዋች' የተሰኘ ድረ ገጽ “በፕላኔታችን ላይ አዳኒ እና ኩባንያዎቹ የሚፈጽሟቸውን ጥፋቶች” ዘርዝሯል። የአዳኒ ኩባንያዎች በበኩላቸው በአውስትራሊያ ውስጥ ምንም አይነት ሕግ አልጣስንም ብለዋል።
ከአስር ዓመት በፊት የሕንድ መንግሥት ጠቅላይ ኦዲተር በወቅቱ የጉጅራት አስተዳዳሪ የነበሩት ናሬንድራ ሞዲ፣ ከመንግሥት ከሚተዳደረው የጋዝ ኩባንያ ለአዳኒ እና ለሌሎች ነጋዴዎች ባልተገባ መልኩ ርካሽ ነዳጅ አቅርበዋል ሲል ከሷል።
እንዲሁም ከአምስት ዓመታት በፊትም አንድ ጋዜጠኛ የአዳኒ ኩባንያዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የተለየ ጥቅም እንዲያገኙ ተደርገዋል ሲል ተከታታይ ጽሁፎችን አውጥቷል።
የአዳኒ ኩባንያዎችም ሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ መንግሥት እንዲህ ያለውን የአድሏዊ አሰራር ውንጀላን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል።
የአዳኒ የሕይወት ታሪክን የጻፈው ደራሲ አርኤን ብሃስካር በበኩሉ “ግንኙነቱን የማጠንከር እና የመቀጠል ችሎታው” ለንግድ ሥራዎቹ እድገት እንደረዳው ተናግሯል።
ከአብዛኞቹ “የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መሪዎች” ጋር በተለያየ ሁኔታ ወዳጅነትን መመስረት ችሏል። በኬረላ የሚገኘው የአዳኒ የወደብ ፕሮጀክት የፀደቀው ዋናው ተቃዋሚ ኮንግረስ ፓርቲ በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግዛቲቱን የሚመሩት ኮሚኒስቶች ደግፈውታል።
ብሃስካር እንደሚለው አዳኒ ከንግድ አጋሮቸቻው ጎልተው እንዲወጡ ካደረጓቸው ጉዳዮች መካከል የቢዝነስ አካሄዱ ነው ይላል።
“ንግዱ ገንዘብ ማትረፍ እስኪጀምር ድረስ ከኢንቨስትመንቱ ምንም አይነት ገንዘብ ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆኑ ነው” ሲልም ይናገራል።
አክሎም አዳኒ እድገቱ የሚረጋገጠው የንግድ ፍላጎቶች “ከአገራዊ ጥቅሞች ጋር እጅና ጓንት ሆነው” ሲሰሩ ነው ብሎ ያምናል።
በድረ-ገጹ ላይ እንደተገለጸው የቢዝነሱ ፍልስፍናም “በጥሩነት እድገት” የሚመራ “የአገር ግንባታ” የሚል ነው።