ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኒው ዮርክ እና ሴንጋፖር የዓለማችን ውድ ከተሞች ተባሉ
ዓመታዊው የኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት የዳስሳ ጥናት ኒው ዮርክ እና ሴንጋፖር የዓለማችን ውድ ከተሞች መሆናቸውን አሳየ።
የእስራኤሏ ቴል አቪቭ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ሆንግ ኮንግ እና ሎስ አንጀለስ ደግሞ በእኩል ደረጃ አራተኛ ላይ ተቀምጠዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ የሊቢያዋ ትሪፖሊ እና የሶሪያዋ ደማስቆ ኑሮ ርካሽ ከሆኑባቸው ከተሞች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው ብሏል። እነዚህ ከተሞች በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚገኙ አገራት መዲናዎች ናቸው።
የዳስሳ ጥናቱ በዚህ ዓመት በአጠቃላይ በዓለማችን ግዙፍ ከተሞች የኑሮ ውድነት በአማካይ በ8.1 በመቶ ጨምሯል ብሏል።
ለጭማሪው ደግሞ በዩክሬን ያለው ጦርነት እና የኮቪድ-19 ወረርሽን በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ያሳደርው ጫና እንደምክንያት ተጠቅሰዋል።
የዋጋ ግሽበት በተለይ በቱርክ ኢስታንቡል (86 በመቶ)፣ በአርጀንቲናዋ ቦነስ አይረስ (64 በመቶ) እንዲሁም በኢራኗ መዲና ቴህራን 57 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል።
በዚህ የዳሰሳ ጥናት ላይ ሦስት የአሜሪካ ከተሞችም በቀዳሚዎቹ ውድ የዓለማችን 10 ከተሞች ውስጥ ተካተዋል።
ኒው ዮርክ፣ ሎስ አንጀለስ እና ሳንፍራንሲስኮ ውድ የሆኑበት ምክንያትም በተመሳሳይ የዋጋ ንረት በከተሞቹ በማጋጠሙ ነው።
አሜሪካ አሁን ላይ ያጋጠማት ከፍተኛ የዋጋ ንረት በ40 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ነው።
በሩሲዋ መዲና ሞስኮም ኑሮ ከብዷል፤ በኑሮ ውድነት ሞስኮ ከ88ኛ ደረጃ ወደ 37ኛ ደረጃ ከፍ ብላለች። ለዚህ ደግሞ የሩሲያን ወረራ ተከትሎ ምዕራባውያን በአገሪቱ ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች ምክንያት ናቸው ተብሏል።
ይህ የዳሰሳ ጥናት በ173 ከተሞች የምርት እና አገልግሎት ዋጋዎችን በአሜሪካ ዶላር አነጻጽሯል።
ጥናቱን ያካሄደው ቡድን መሪ የሆኑት አፕሳና ደት እንደሚሉት በዩክሬን ያለው ጦርነት፣ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ እና ቻይና ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የወሰደችው የዜሮ-ኮቪድ ፖሊሲ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ችግር ፈጥረዋል።
ይህ ከወለድ መጠን ከፍ ማለት ጋር እና ከውጭ ምንዛሬ መዋዠቅ ጋር ተያይዞ በመላው ዓለም በሚገኙ ከተሞች ሕይወት ከባድ እንዲሆን አድርገዋል ይላሉ።
በዳሰሳ ጥናቱ መሠረት ውድ የተባሉት ቀዳሚዎቹ አስር ከተሞች ኒው ዮርክ እና ሴንጋፖር በቀዳሚነት ሲጠቀሱ፣ ቴላቪቭ 3ኛ፣ ሆንግ ኮንግ እና ሎስ አንጀለስ ደግሞ በእኩል ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ዙሪክ፣ ጄኔቭ፣ ሳን ፍራንሲስኮ እና ፓሪስ ከ6ኛ እስከ 9ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ፤ ሲድኒ እና ኮፐንሃገን ደግሞ በእኩል ደረጃ 10ኛ ላይ ተቀምጠዋል።