ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና በኦሮሚያ የዜጋዋን ግድያ ተከትሎ ለዜጎቿ ማስጠንቀቂያ አወጣች
አንድ ቻይናዊ በኦሮሚያ ክልል ገብረ ጉራቻ ከተማ ከተገደለ በኋላ ቻይና በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ዜጎቿ ማስጠንቀቂያ ሰጠች።
ኤአፍፒ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲን ጠቅሶ እንደዘገበው ሰኞ ጥር 22/2015 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ በሰሜን አቅጣጫ ገብረ ጉራቻ ከተማ 9 የቻይና ዜጎች በታጣቂ ቡድኖች ተኩስ ተከፍቶባቸው ነበር።
ተኩስ ከተከፈተባቸው ቻይናውያን መካከል አንዱ ሕይወቱ ማለፉን ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎች በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።
ኤምባሲው የዜጋውን መገደል ይፋ ባደረገበት መግለጫው፤ ጥቃቱን ያደረሰው ታጣቂ ቡድን ማን እንደሆነ እንዲሁም የጥቃቱ ዒላማ የሆኑት ቻይናውያን ማንነትንም አልገለፀም።
የቻይኛ ኤምባሲ መግለጫ አንድ ቻይናዊ መገደሉን ከመጥቀስ ውጪ፣ በሌሎች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም።
ከአዲስ አበባ 163 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ከተማ በቻይናውያኑ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ኤምባሲው ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ላይ፤ “ከፍተኛ የአደጋ ስጋት ባለበት አካባቢ ከሆናችሁ፤ በአስቸኳይ ደኅንነቱ ወደ ተጠበቀ አካባቢ መውጣት አለባችሁ” ብሏል።
ኤምባሲው በኦሮሚያ ክልል እና በአጎራባች ክልሎች በጦር መሳሪያ የታገዘ ጥቃት፣ አፈና እና ዘረፋ የተስፋፋ ነው ብሏል።
ክስተቱን በተመለከተ ኤኤፍፒ የኦሮሚያ ክልል ባስልጣናትን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ለሁለት ዓመታት በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ሲደረግ የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ባለፉት ጥቂት ወራት ቢቆምም፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ግን በመንግሥት ኃይሎች እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ቡድን መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው።
መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው ይህ ታጣቂ ቡድን በመንግሥት ባለስልጣናት እና በዜጎች ግድያ እንዲሁም የውጪ ዜጎችን ጨምሮ ሰዎችን አግቶ ገንዘብ በመጠየቅ ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።
ባለፈው ሳምንትም ታጣቂ ቡድኑ ከ20 ያላሱ የዳንጎቴ ሲሚንቶ የመሃንዲሶች ቡድንን አፍኖ ወስዶ ነበር።
ሮይተርስ እነዚህ ታፍነው የነበሩ የሲሚንቶ ፋብሪካው ሠራተኞች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ተለቀዋል ሲል ዘግቧል።
ከሁለት ወራት በፊት ደግሞ ከ30 ያላሱ የሲሚንቶ ፋብሪካው ሠራተኞች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አደአ በርጋ ወረዳ በታጣቂ ቡድኑ አባላት ታግተው ነበር።
በወቅቱ ምንጮች እገታውን የፈጸመው መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀው እና በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም መንግሥት ‘ሸኔ’ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ነው ብለው ነበር።
ረቡዕ ኅዳር 21/2015 ዓ.ም. ታግተው ከነበሩት መካከል አብዛኛዎቹ በታጣቂ ቡድኑ የተጠየቁትን የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው የወጡ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ታግተው የነበሩት መሃንዲሶች ግን ከእገታ ነጻ የወጡት ማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።