አሜሪካ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት 200ሺህ ያህል ወታደሮች ሙትና ቁስለኛ ሳይሆኑ አይቀሩም አለች

አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ የጦር መኮንን በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከሁለቱም ወገን በተሰለፉ ወታደሮች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ተናገሩ።

የአሜሪካ ሠራዊት የጋራ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ማርክ ሚሊ እንዳሉት በጦርነቱ ከሩሲያ በኩል 100ሺህ እንዲሁም በዩክሬን ወገን 100ሺህ ወታደሮች ሳይገደሉ ወይም ሳይቆስሉ አይቀሩም ብለዋል።

ጄኔራሉ ጨምረውም በዚህ ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው ተዋጊዎች በተጨማሪ 40ሺህ ያህል ሰላማዊ ሰዎች ሳይገደሉ እንደማይቀር ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ይህ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የሞቱ እና የተጎዱ ሰዎችን በተመለከተ የምዕራባውያን አገራት ባለሥልጣናት እስካሁን ከሰጡት ግምት ከፍተኛው አሃዝ ነው።

ጄኔራሉ ጨምረውም ኪዬቭ ከሞስኮ ጋር ዳግም ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ ማለቷ ለድርድር በር ይከፍታል ብለዋል።

ከቅርብ ቀናት ወዲህ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር ፍላጎት እንዳላት ፍንጭ እያሳየች ነው። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ፣ ፕሬዝዳንት ፑቲን ከሥልጣን ካልተነሱ በቀር ድርድር አናደርግም የሚለውን አቋማቸውን አንስተዋል።

ጄኔራል ሚሊ ለኒው ዮርክ ታይምስ ሲናገሩ ሁለቱ አገራት ሊያደርጉ የሚችሉት ንግግር ስኬታማ የሚሆነው ‘የጦር ድል’ በወታደራዊ እርምጃዎች ሊሳካ እንደማይችል ‘የጋራ ግንዛቤ ወስደው’ ሌሎች አማራጮችን መመልከት ሲችሉ ነው ብለዋል። 

የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከፍተኛ የጦር አማካሪ ሆነው የሚያገለግሉት ጄኔራሉ፤ ጦርነቱ ያደረሰው የውድመት መጠን ሞስኮ እና ኪዬቭ በቀጣይ የክረምት ወራት በበረዶ ምክንያት ውጊያው ሲቀዛቀዝ ድርድር ማድረግ እንዳለባቸው ሊያሳምናቸው ይችላል ብለዋል።

ከ100ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል። ያሉት ጄኔራሉ፤ “ተመሳሳይ ነገር በዩክሬን በኩል ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

ጄኔራሉ የሟች እና ቁስለኛ ቁጥርን በመቶ ሺህ ቤት ያደርሱት እንጂ ሞስኮ እና ኪዬቭ በጦርነቱ ምክንያት የተገደሉባቸውን ወታደሮች ቁጥር አሳንሰው ያቀርባሉ። የተባበሩት መንግሥታትም ከሁለቱ ወገኖች በኩል የሚወጡ የተጎጂዎች ቁጥር ተዓማኒ አይደለም ብሎ ነበር። 

ሞስኮ መስከረም ወር ላይ ጦርነቱ ከተጀመረ በሞት ያጣኋቸው ወታደሮቼ ቁጥር 5ሺህ 937 ነው ብላ ነበር። ዩክሬን እስካሁን የተጎዱ ወታደሮች አሃዝን በይፋ ከመግለጽ ብትቆጠብም ሰኔ 2014 ላይ አንድ የዩክሬን ጦር ከፍተኛ መኮንን የተገደሉት ወታደሮቻቸው ቁጥር 9ሺህ ገደማ መሆኑን ገልጸው ነበር።

ጄኔራል ማርክ ሚሊ ጨምረውም ከተገደሉት እና ከቆሰሉት በተጨማሪ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ በመፈጸሟ ከ15 እስከ 30 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ተፈጥረዋል ብለዋል። 

የተባበሩት መንግሥት በመላው አውሮፓ 7.8 ሚሊዮን ተፈናቃይ ዩክሬናውያንን መዝግቧል። ይህ አሃዝ ግን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው እዚያው ዩክሬን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙትን አይጨምርም።