ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወደ ትግራይ ምግብ እና መድኃኒት እየገባ እንዳልሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ
በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ባለፈው ሳምንት ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት ቢደረስም ወደ ትግራይ ክልል ምግብም ሆነ መድኃኒት እየገባ እንዳልሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ይጠቀማል ሲል የሚወቅስ ሲሆን፣ በተጣለው እገዳ ምክንያት 90 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ አደጋ ላይ ወድቋል።
“ምንም ነገር እየገባ አይደለም” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል።
“የግጭት ማቆም ስምምነቱን ተከትሎ ወዲያውኑ ምግብ እና መድኃኒት ወደ ክልሉ ይገባል ብዬ እየጠበቅኩ ነበር። ይህ ሁኔታ ግን እየታየ አይደለም” ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ጨምረውም በትግራይ ክልል ውስጥ ሰዎች በረሃብ እና በህክምና ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች ምክንያት እየሞቱ ነው ብለዋል።
ዶክተር ቴድሮስ በክልሉ የተቋረጡት የቴሌኮም፣ የባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱም ጠይቀዋል።
“ስድስት ሚሊዮን ሕዝቦች በሕይወት የሌሉ ይመስል ለሁለት ዓመታት ያህል ከዓለም ጋር እንዲቆራረጡ ተደርገዋል” ብለዋል።
አንድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣን ግን ዶክተር ቴድሮስ የሰላም ስምምነቱን ለማደፍረስ እየሞከሩ ነው በሚል ወቅሰው ምግብ እና መድኃኒት ወደ ትግራይ እየደረሰ ነው ብለዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎችም የመብራትና የቴሌኮም አገልግሎቶች ወደነበረበት መመለሱን ጨምረው ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መሪዎች መካከል ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ የተደረሰውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነትን ተከትሎ ናይሮቢ ኬንያ ውስጥ ንግግር እየተደረገ ይገኛል።
በዚሁ ንግግር የመክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን የቴሌኮም፣ የመብራት እና የባንክ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መጀመር አለብን ለዚህም ጥረት እየተደረገ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ከዚህ በፊት ግን “ሕዝባችን መጀመሪያ ምግብ እና መድኃኒት ያስፈልገዋል፣ እሱንም ለማድረግ እየሞከርን ነው” ብለዋል።
“ምናልባት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው ሳምንት አጋማሽ ላይ” ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲገባ ይፈቀዳል ሲሉ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለጋዜጠኞች መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።
በትግራይ ያለው ሁኔታ አስከፊ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት እና አጋር ድርጅቶች እየገለጹ ሲሆን መሠረታዊ መድኃኒቶች ማለቃቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
“በአሁኑ ወቅት ያለብን ብቸኛው እንቅፋት፣ ሁኔታውን ለመገምገም የጦር አዛዦቹ እስኪገናኙ ድረስ በረራዎችን መፍቀድ አሁንም አደገኛ ነው” ሲሉ አምባሳደር ሬድዋን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ለውጭ ዲፕሎማቶች እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥቱ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ በጊዜ ገደብ ከተስማሙ የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይን አየር ክልል እና አየር ማረፊያዎች ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ በኋላ “መላው የትግራይ ክልል በመንገድ እና በአየር ለእርዳታ ተደራሽ ይሆናል” በማለት ለዲፕሎማቶቹ አስረድተዋል።