ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በናይሮቢው ውይይት ቀዳሚው ጉዳይ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ እንደሆነ አሜሪካ ገለጸች
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መሪዎች መካከል በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ግጭትን በዘላቂነት ማቆም ስምምነትን ተከትሎ በናይሮቢ የተጀመረው ንግግር አንዱ አጀንዳ በትግራይ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ እንደሆነ አሜሪካ አስታወቀች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃለ አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሰኞ ዕለት ይህንን ያሉት፣ የፌደራል መንግሥቱ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ንግግር መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።
በናይሮቢ፣ ካረን ሞራን ማዕከል እየተደረገ ስላለው ውይይት አስተያየታቸውን የሰጡት ኔድ ፕራይስ በስምምነቱ መሠረት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ማፋጠን እንዲሁም በትግራይና በአጎራባቾቹ የአፋር እና የአማራ ክልሎች ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ አንደኛው አጀንዳ እንደሆነ ተረድተናል ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት በተደረሰው ስምምነት መሰረት “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም እና የትግራይ ኃይሎች ኃላፊ በአምስት ቀናት ውስጥ ተገናኝተው አፈጻጸሙን በተመለከተ ውይይት እያደረጉ” ነው ብለዋል።
ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸውን ያስታወቁት ኔድ ፕራይስ “እነዚህ ተጨባጭ እርምጃዎች ሁለቱም ወገኖች ጠመንጃን ጸጥ ለማሰኘት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያንጸባርቃል” በማለት አስረድተተዋል።
ለሁለት ዓመታት ያህል የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ከማስቀጠል በተጨማሪ የዚህ ውይይት አጀንዳዎች ስምምነቱን የመቆጣጠሪያ መንገዶችንና የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት የሚሉ ይገኙበታል።
በውይይቱ ላይ ምን ተባለ?
በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት በጦር አዛዦቹ መካከል የሚደረገው ውይይት ደኅንነትን የሚያረጋግጥ እና እስካሁን ተደራሽ ወዳልሆኑ አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታዎችን ያፋጥናል በማለት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
አምባሳደር ሬድዋን የቴሌኮም፣ የመብራት እና የባንክ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መጀመር አለብን ሲሉም በውይይቱ መክፈቻ ላይ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ግን “ሕዝባችን መጀመሪያ ምግብ እና መድኃኒት ያስፈልገዋል፣ እሱንም ለማድረግ እየሞከርን ነው” ብለዋል።
“ምናልባት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው ሳምንት አጋማሽ ላይ” ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲገባ ይፈቀዳል ሲሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ተደራዳሪ ሬድዋን ሁሴን ለጋዜጠኞች መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።
በዚሁ ፕሮግራም ላይ የህወሓት ተደራዳሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ስምምነቱ በደነገገው መሠረት በርካታ መሰራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ጠቅሰው፣ መሠረታዊ አገልግሎት መቀጠል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል። አገልግሎቶች በመቀጠላቸውም በስምምነቱ መተማመን፣ ተስፋ በሕዝቡ ላይ እንደሚያሰርጽ አስረድተው ይህም ሊመጣ ያሰበውን ሰላም ያጠናክረዋል ብለዋል።
“የትግራይን ሕዝብ ፍላጎት አሳልፎ የሰጠ ነው” በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ከትግራይ ዲያስፖራ እየቀረበ ሲሆን አቶ ጌታቸው ከድርድሩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለስምምነቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
“እኛ የምንዋጋው ደስተኛ ሕዝብ በመሆናችን ሳይሆን፣ እንደ ሕዝብ ህልውናችን አደጋ ላይ ስለወደቀ ነው፤ የሰላም ስምምነት ህልውናችንን የሚያረጋግጥ ከሆነ ለምን አንሞክረውም?” ሲሉም በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ለውይይቱ ቅርበት ያላቸውን ባሥልጣንን ዋቢ አድርጎ ኤፒ እንደዘገበው በልዑካኑ መካከል የሚደረገው ውይይት እስከ ረቡዕ ጥቅምት 30/2015 ዓ.ም. እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በሁለቱም የጦር አዛዦች መካከል የሚከሰቱ ማንኛውንም ችግሮች ለመፍታት የግንኙነት መስመር የተቋቋመ መሆኑን፣ እኚሁ በስም ያልተጠቀሱ ባለሥልጣን እንደተናገሩና “ውጊያ ለማቆም ከሁሉም ጦር ክፍሎቻቸው ጋር መገናኘት ያለውን ተግዳሮት ይገነዘቡታል” ብለዋል።
ይህ ውይይት እየተመራ ያለው በአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ቡድን የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጎን አቦሳንጆ፣ የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እና የኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ጄኔራሎች መሆናቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ገልጸዋል።
ኡሁሩ ኬንያታም በዚሁ ውይይት መክፈቻ ላይ “የሚቀጥለው ውይይታችን በመቀለ እንደምናደርግ ተስፋ እናደርጋለን” ያሉ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች በመጨረሻ በአዲስ አበባ በአንድነት የሰላም ስምምነቱን ያከብራሉ ብለዋል።
ኢጋድም በዚህ ውይይት ላይ የታዛቢነት ስፍራ እንዳለውም ተገልጿል።
በስምምነቱ ላይ የታዛቢነት ድርሻ እንዳላት የተገለጸው አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የተወከለች ሲሆን፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት እስኪተገበር ድረስ በቀጠናው እንደሚቆዩ እና ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃለ አቀባዩ ገልጸዋል።
አሜሪካ በዚህ ስምምነት ከፍተኛ ስፍራ እንዳላትም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ለውጭ ዲፕሎማቶች እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት መናገራቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
“አሜሪካ ህወሓትን ወደ ድርድሩ ለማምጣት፣ ለማሳመን እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ጫና በመፍጠር ወደ ደቡብ አፍሪካም በማድረስ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክታለች” ሲሉ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
በትግራይ ያለው ሁኔታ አስከፊ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት እና አጋር ድርጅቶች እየገለጹ ሲሆን መሠረታዊ መድኃኒቶች ማለቃቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
“በአሁኑ ወቅት ያለብን ብቸኛው እንቅፋት፣ ሁኔታውን ለመገምገም የጦር አዛዦቹ እስኪገናኙ ድረስ በረራዎችን መፍቀድ አሁንም አደገኛ ነው” ሲሉ አምባሳደር ሬድዋን ለዲፕሎማቶች ተናግረዋል።
የጦር አዛዦቹ በጊዜ ገደብ ከተስማሙ የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይን አየር ክልል እና አየር ማረፊያዎች ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ በኋላ “መላው የትግራይ ክልል በመንገድ እና በአየር ለእርዳታ ተደራሽ ይሆናል” በማለት ለዲፕሎማቶቹ አስረድተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን በባለፈው ሳምንት መገባደጃ መግለጫቸው በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ ድንበር እና የአየር ክልል ተጥሷል ሲሉ ተናግረዋል። “እርስ በርስ በመዋጋት ተጠምደናል። እርስ በርስ እየተዳከምን ባለንበት ወቅት ለሦስተኛ ወገን እኛን የበለጠ እንድናዳከም መንገድ ከፍቷል” ብለዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት አጋር በመሆን በጦርነቱ እየተዋጋች ያለችው ኤርትራ የድርድሩ አካል አልነበረችም። ያለፈው ሳምንቱ የግጭት ማቆም ስምምነት በቀጥታ አልጠቀሳትም።
አምባሳደር ሬድዋን ሦስተኛ ወገን ያሉትን በስም ያልጠቀሱ ሲሆን አክለውም “በዚህ የሰላም ሂደት ፍላጎትላይኖረው የሚችል ሦስተኛ አካል ሊኖር ይችላል” ብለዋል።