ኩዌት ኢትዮጵያዊት ሴትን ጨምሮ ሰባት ሰዎችን በስቅላት ቀጣች

ኩዌት የአለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾችን የምህረት ተማጽኖ ችላ በማለት ዛሬ ህዳር 7፣ 2015 ዓ.ም ሰባት እስረኞችን በስቅላት ቀጥታለች።

ከነዚህም ውስጥ አንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት የምትገኝበት ሲሆን ሌላ የኩዌት ዜጋ እንደምትገኝበትም ተገልጿል።

ኩዌት በአምስት ዓመታት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያውን የሞት ፍርድም ተፈጻሚ ማድረጓም ተገልጿል።

አቃቤ ህግ እንደገለጸው የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው መካከል ከኢትዮጵያ የመጣች አንዲት ግለሰብ፣ የኩዌት ዜግነት ያላት ሌላ ሴትና፣ ሶሪያዊ፣ ፓኪስታናዊ እና ሌሎቹ ደግሞ የኩዌት ዜግነት ያላቸው ናቸው ብሏል።

በስቅላት የተቀጡት እነዚህ እስረኞች በግድያ ወንጀልና ሌሎች ወንጀሎች የተከሰሱ መሆናቸውን የመንግሥት ዜና ወኪል የሆነው ኩና መዘገቡን አሶሺዬትድ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።

የሞት ፍርዱም የተፈጸመው በማዕከላዊ እስር ቤትም እንደሆነ ከኤፒ ዘገባ መረዳት ተችሏል።

የሞት ቅጣቱ ይፋ የሆነው በአገሪቱ የህዝብ አቃቤ ህግ አማካሪ መሃመድ አል ዱአይጂ ህዳር 5፣ 2015 ዓ.ም መሆኑን አምነስቲ ህዳር 6፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አትቷል።

ሰባቱ ግለሰቦች ነፍስ በማጥፋት ወንጀል የተፈረደባቸው እንደሆነ ገልጸው ከሁለት ቀናት በኋላ ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል። አማካሪው እንዲህ አይነት የሞት ቅጣት መታወጁ “እንዲህ አይነት ወንጀሎችን ለመከላከል” እንዲሁም ለጠፋውም ጥፋት ተገቢ ቅጣት ነው ሲሉም የቁርዓን አንቀጽ መጥቀሳቸውን የኩዌት ዕለታዊ ጋዜጣን አል ቃባስን ዋቢ አድርጎም አምነስቲ አስፍሯል።

ይህ የሞት ቅጣት ተፈጻሚም እንዳይሆን አምነስቲ በዚሁ መግለጫ ጠይቆ ነበር።

“የኩዌት ባለስልጣናት እነዚህን የሞት ቅጣቶች በአስቸኳይ ማቆም አለባቸው። የሞት ቅጣቱ የሰው ልጅ በህይወት መኖርን የጣሰ እና ጭካኔ የተሞላበት ኢሰብዓዊና ዘግናኝ ቅጣት ነው። አምነስቲ ኢንተርናሽናል የትኛውም አይነት ወንጀል ቢፈጸምም የሞት ቅጣት ተፈጻሚነትን ይቃወማል” ሲሉም የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ምክትል ቀጣና ዳይሬክተር አምና ጉሌሊ ተናግረው ነበር።

የአውሮፓ ህብረት የሞት ቅጣቱን የተቸ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ባለስልጣን ማርጋሪቲስ ሺናስ ሃገሪቱን ከጎበኙበት ጊዜም ጋር የተገጣጠመ ነው ብሏል።

“በኩዌት የሞት ቅጣትን ሙሉ በሙሉ የማቆም እርምጃ እንድትወስድ ህብረቱ ይጠይቃል። ይህ ቅጣት ጭካኔ የተሞላበት እና ኢሰብዓዊ ነው” ብሏል በመግለጫው

አብዛኛውን ጊዜ በኩዌት የሞት ቅጣት ተፈጻሚ የሚሆነው በስቅላት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ አልሞ ተኳሾችን በመጠቀምም ሞቱ ተፈጻሚ ይሆናል።

ኩዌት አሁን ተፈጻሚ ካደረገችው የሞት ቅጣት በፊት በአውሮፓውያኑ 2017 የአንድ የንጉሳውያን ቤተሰብ አባልን ጨምሮ በሰባት እስረኞች ላይ የጅምላ ግድያ ፈጽማለች።

ኩዌት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ወደ 80 የሚሆኑ ሰዎችን በሞት ስትቀጣ ብዙዎችም በግድያ ወንጀልና ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ ነበር።