ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ደቡብ አፍሪካዊቷ እናት የስድስት ዓመት ልጇ እንድትሸጥ አድርጋለች በሚል ተጠርጥራ ተያዘች
ከሳምንታት በፊት የደረሰችበት ያልታወቀቸውን ልጇን እንድትሸጥ አድርጋለች የተባለቸው ደቡብ አፍሪካዊት እናት እና የፍቅር አጋሯ በፖሊስ ተያዙ።
ከየካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮ የተሰወረችው ታዳጊን ለማግኘት ጥረት ቢደረግም አስካሁን ያልተገኘች ሲሆን፣ እናት በሕገ ወጥ የሰው ዝውውር እና በእገታ ወንጀል ክስ ቀርቦባታል።
ኬሊ ስሚዝ የተባለችው የስድስት ዓመቷ ታዳጊ እናት በወንጀሉ የተከሰሰችው ከፍቅር አጋሯ እና ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር በመሆን ነው። ተጠርጣሪዎቹ ሁሉም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ።
ህጻኗ ጆስሊን ኬፕታውን አቅራቢያ ከሚገኘው ቤቷ ነው የጠፋችው። አራቱም ተከሳሾች በተጠረጠሩበት ወንጀል ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ስለጉዳዩ እንዲያብራሩ ግን ዕድል አልተሰጣቸውም ተብሏል።
ከፍርድ ቤቱ መግቢያ በር ላይ የተሰባሰቡ በርካታ ሰዎች “ጆስሊንን መልሷት” እያሉ ሲጮሁ እንደነበር ተልጿል።
አንድ የግል ጋዜጣ እንደጻፈው ከሆነ የጆስሊን እናት ኬሊ ስሚዝ፣ ልጇን ለአንድ ጠንቋይ በአንድ ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንዲሸጧት ባሏን እና ሌሎች ግብረ አበሮቹን ትዕዛዝ ሰጥታቸዋለች።
በደቡብ አፍሪካ የሕጻናት መጥፋት የተለመደ ቢሆንም አብዛኞቹ ወዲያውኑ ይገኛሉ። ጆስሊን ግን እስካሁን ደብዛዋ አጠፍቷል።
ደቡብ አፍሪካ ባሕር ኃይል፣ ድሮን እና አነፍናፊ ውሾችን ያካተተ ሰፊ አሰሳ ቢደረግም እስካሁን ጆስሊንን አየሁ ያለ አልተገኘም።
አሰሳው መቀጠሉን ፖሊስ አስታውቋል። ባለፈው ቅዳሜ መርማሪዎቹ ጆስሊን ጠፍታለች የተባለበት ቦታ አካባቢ በደም የተበላሸ ልብስ ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ኬሊ እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች መደበኛ ክስ እስከሚመሠረትባቸው እስከ ሚቀጥለው ሳምንት ድረስ በእስራት እንዲቆዩ ተወስኖባቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ ሁሉም የሕግ አማካሪ እንደሚቀጥሩ ገልጸዋል።
በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ ባሕላዊ ሐኪሞች [ጠንቋዮች] ደንበኞቻቸውን ለመፈወስ ወይም ደግሞ ጸጋ ለማብዛት በሚያደርጉት ጥንቆላ የሰው የሰውነት አካላትን እንደሚጠቀሙ ይታመናል።
ተከሳሿ ኬሊ ስሚዝ ልጇን ለጠንቋይ ሸጣታለች የሚል ክስ ቢቀርብባትም፤ በልጇ እንደማትጨክን እና ልጇን ለማግኘት ተስፋ እንደማትቆርጥ ለአንድ የግል ጋዜጣ ተናግራለች።
“እንደ እናትነቴ ልጄ በሕይወት እንዳለች እና እንደማገኛት ደመ ነፍሴ ይነግረኛል። በእያንዳንዱ ጎጆ ውስጥ ፈልጌ አገኛታለሁ” ብላለች።
የአካባቢው ሕብረተሰብ ልጅቷ ጠፋች ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ፍለጋ ቢያደርጉም ያገኙት ተስፋ ሰጭ ነገር የለም።
ልጅቷ [ጆስሊን] ያለችበትን ቦታ ለጠቆመ 100 ሺህ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ወይም አምስት ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወሮታ እንደሚከፈለው ተገልጿል።
ጆስሊን የጠፋችው የእናቷ የፍቅር አጋር ከሆነው ግለሰብ ጋር በነበረችበት ወቅት ነው።
ግለሰቡ ግን ከልጅቷ መጥፋት ጋር ግንኙነት እንደሌለው ገልጿል።