በትግራይ በሕጻናት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች እየጨመሩ መሆናቸው ተነገረ

በትግራይ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት የክትባት መጠን በመቀነሱ በክትባት መከላከል የሚቻሉ በሕጻናት ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ ዓይነት በሽታዎች እየጨመሩ መሆኑ ተነገረ።

የክልሉ የጤና ባለሥልጣናት እንዳሉት ክትባት የሚያገኙ ሕጻናት ቁጥር በመቀነሱ ልጆችን የሚያጠቁ ኩፍኝን፣ ፖሊዮን እና ቲታነስን የመሳሰሉ በሽታዎች እየጨመሩ ነው።

ከትግራይ ጤና ቢሮ የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት ውስጥ በክልሉ መደበኛ የበሽታዎች መከላከያ ክትባቶችን የሚያገኙ ልጆች መጠን ከ10 በመቶ በታች አሽቆልቁሏል።

የጤና ቢሮው ‘ጋቪ’ በመባል ለሚታወቀው በዓለም ዙሪያ ክትባቶችን የሚያቀርበው ዓለም አቀፍ ትብብር በጻፈው ደብዳቤ ላይ፤ “የጨቅላ ሕጻናት እና የልጆች ክትባትን ጨምሮ ሕይወት አድን የሆኑ መድኃኒቶች እና የሕክምና አቅርቦቶች እንዳያገኙ በመደረጋቸው” ለተለያዩ በሽታዎች ተዳርገዋል ብሏል።

በዚህም ሳቢያ የኩፍኝ፣ የተቅማጥ፣ የማጅራት ገትር፣ የልጅነት ልምሻ [ፖሊዮ] እና የመሳሰሉ ወረርሽኞች በክልሉ ውስጥ መከሰታቸውን የጤና ቢሮው በጻፈው ደብዳቤ ላይ አመልክቷል።

ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው በክልሉ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የክትባት አቅርቦት በመቀነሱ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ ከትባቶችን በተገቢው መጠን አቀዝቅዞ ለማስቀመጥ ባለመቻሉ እና በገጠር አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ወደ ጤና ተቋማት ለክትባት መምጣት ባለመቻላቸው እንደሆነ የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጿል።

የኩፍኝ ወረርሽኝ በክልሉ ውስጥ ካሉ 35 ዞኖች በ10 ዞኖች ውስጥ መከሰቱን ሪፖርት መደረጉን የገለጸው ቢሮው፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 ዜሮ የነበረው በጨቅላ ሕጻናት ላይ የሚከሰት ቲታነስ አሁን 25 መድረሱን አመልክቷል።

በመጪው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ሁለተኛ ዓመቱን በሚይዘው በትግራይ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በርካታ የጤና ተቋማት ላይ ውድመት ማጋጠሙንና ከሥራ ውጪ መሆናቸውን ከዚህ በፊት የወጡ ሪፖርቶች አመለክተዋል።

ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት በቅርቡ መቀስቀሱ ደግሞ በክልሉ ውስጥ ያለውን የጤና አገልግሎት የአቅርቦት ችግር የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።