ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካ ለውጭ አገር ዜጎች ሃሰተኛ የጋብቻ ሰነድ ያዘጋጁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
በደቡብ አፍሪካ የውጭ አገር ዜጎች የአገሪቱን ዜግነት እንዲያገኙ ለመርዳት በሚል ሃሰተኛ የጋብቻ ሰነድ በማዘጋጀት የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
ሰኞ እለት በደቡብ አፍሪካዋ ደርባን ከተማ በሚገኝ ህንጻ ላይ ፖሊሶች በገቡበት ወቅት የማመልከቻ ቅጾችን፣ የመታወቂያ ቅጂዎችን እንዲሁም ሌሎች ማስረጃዎችን ማግኘታቸው ተገልጿል።
አንደኛው ተጠርጣሪም መረጃዎቹን ሊያጠፋ ሲሞክር እጅ ከፍንጅ ተይዟል ተብሏል።
በስፍራው የተገኙት በርካታዎቹ መታወቂያዎች ከደቡብ አፍሪካውያን ሴቶች የተሰረቁ እንደሆኑ ፖሊስ ገልጾ ከዚያም ሃሰተኛ የጋብቻ ሰርቲፊኬት እና ለውጭ አገር ዜጎች ቪዛ ይሰራ ነበር ብሏል።
“ከአገራቸው ሲመጡ ደቡብ አፍሪካውያን ሴቶች ጋር የተጋቡ ባለትዳር ሆነው ነው። እዚህ ከደረሱ በኋላ ፍች ይፈጽማሉ” ሲሉ የክልላዊ ፖሊስ ቃለ አቀባይ ኮሎኔል ሮበርት ኔትሺውንዳ ለኒውስ 24 የዜና ወኪል ተናግረዋል።
“ በዚህ የማጭበርበር ተግባር ዜግነት አግኝተው ሌሎች ሰዎችን እያመጡ ነው” ብለዋል።
በዚህ ሃሰተኛ የጋብቻ ሰነድ በማዘጋጀት ምን ያህል ሰዎች እንደተሳተፉ እንዲሁም ከፋዮቹ የተባሉት ከየትኞቹ አገራት እንደመጡ የተገለጸ ነገር የለም።
ፖሊስ ከስፍራው የተገኙ ኮምፒውተሮችን ለበለጠ መረጃ እየመረመርኩ ነው ብሏል።
አጭበርባሪዎቹ ሲገለገሉበት የነበረው ህንጻ በከተማ ዳርቻ ላይ የሚገኝ እና የማይጠረጠር ነው ተብሏል።
ህንጻው የስደተኞችን ጉዳይ እንደሚመለከተው የአገር ውስጥ ቢሮ ሆኖ “በሚስጥራዊነት እያገለገለ ነበር ሲሉ ኮሌኔሉ ተናግረዋል።
“የአገር ውስጥ ቢሮ ለደቡብ አፍሪካውያን እንደሚሰጠው አገልግሎት ጋብቻዎችን እያሳለጡ፣ ቪዛ እና ሌሎች አገልግሎትን ያመቻቹ ነበር” ብለዋል።
ስፍራው እየሰጠ የነበረው አገልግሎት ከመራቀቁ ብዛት በአገር ውስጥ ቢሮ ውስጥ ያለ ውስጥ አዋቂ ሳይሳተፍበት እንዳልቀረ የገለጸው ፖሊስ ተጠርጣሪ የለየ ቢሆንም በቁጥጥር ስር አላዋልኩም ብሏል።
በአፍሪካ ካሉት አገራት በምጣኔ ኃብቷ የምትሞካሸው ደቡብ አፍሪካ የተሻለ ህይወት ለሚፈልጉ ከተለያየ አፍሪካ አገራት የሚመጡ ስደተኞች እና ስራ ፈላጊዎች ተመራጭ ናት። በዚህም የተነሳ በባለፉት ጥቂት ዓመታት በስደተኞች ላይ ያነጣጠሩ መጤ ጠል ጥቃቶች እና ተቃውሞዎች ተስተናግደዋል።
ደቡብ አፍሪካ ከሁለት ዓመት በፊት ባደረገችው የሕዝብ ቆጠራ መሠረት ቢያንስ 2.4 ሚሊዮን ከሌሎች አገራት የመጡ ስደተኞች አሏት።
ከእነዚህም ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከጎረቤት አገር ዚምባብዌ ቢሆኑም ከኢትዮጵያ፣ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ከሶማሊያ፣ ከባንግላዴሽ እና ከሌሴቶም የመጡ ስደተኞች ቁጥር በርካታ ነው።
ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተሻለ ሥራ እና ኑሮ ፈልገው የሄዱት ስደተኞች 62 ሚሊዮን ሕዝብ ካላት ደቡብ አፍሪካ አንጻር ሲሰላ 3 በመቶ ብቻ ናቸው።
ሆኖም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ስደተኞች ሥራ እና የተለያዩ ዕድሎችን ተሻምተውናል በሚሉ መጤ ጠል (ዜኖፎቢክ) የአገሪቱ ዜጎች ጥቃቶች ያጋጥማቸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች አፍሪካ አገራት የመጡ ስደተኞች ግድያ፣ ዝርፊያ እና የንብረት ውድመቶች አጋጥሟቸዋል።