ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወሲባዊ ይዘት ባላቸው የታዳጊዎች ፎቶዎች የተከሰሰው የቀድሞ የቢቢሲ ጋዜጠኛ 200 ሺህ ፓውንድ ደመወዙን እንዲመልስ ተጠየቀ
ታዳጊዎች የተጋለጡበት ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ፎቶዎች ለማግኘት ገንዘብ በመክፈል የተከሰሰው የቀድሞ የቢቢሲ ጋዜጠኛ 200 ሺህ ፓውንድ ደመወዙን እንዲመልስ በተቋሙ ተጠየቀ።
ቢቢሲ ከነበሩት ስመ ጥር የቴሌቪዥን አቅራቢዎች አንዱ ለሆነው ሂው ኤድዋርድስ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ የወሰደውን ገንዘብ እንዲመልስ ደብዳቤ ጽፏል።
ሂው ኤድዋርድስ የቀረቡበትን ክሶች ጥፋተኛ መሆኑን እያወቀ ደመወዙን እንደተቀበለ ቢቢሲ እንደሚያምን ጠቅሰው የተቋሙ ሊቀመንበር ሳሚር ሻህ ደብዳቤ ጽፈዋል።
በተቋሙ ውስጥ ከፍተኛ ደመወዝ ከሚከፈላቸውም አንዱ የነበረው ሂው ኤድዋርድስ ታዳጊዎች እና ህጻናት የተጋለጡበት ፎቶ ጋር በተያያዘ በሶስት ክሶች በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ለአምስት ወራት ደመወዙን እንደተቀበለ ተገልጿል።
በዚህም ከ200 ሺህ ፓውንድ በላይ ተከፍሎታል።
ጋዜጠኛው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ከስራ ከታገደ ከአራት ወራት በኋላ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው። ጋዜጠኛው ከስራው ታግዶ የነበረ ቢሆንም እስከ ዘንድሮው ዓመት ሚያዝያ ድረስ ከስራው አልለቀቀም ነበር።
ጋዜጠኛው የተጠየቀውን ገንዘብ ለመመለስ ፈቃደኛ ካልሆነ ቢቢሲ ጉዳዩን በህጋዊ መንገድ ይፈታው እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም።
የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጋዜጠኛው በህዳር ወር ከበድ ባለው ህጻናት እና ታዳጊዎች የተጋለጡበት ፎቶዎች ጋር በተያያዘ መታሰሩ ይታወቅ እንደነበር አረጋግጠዋል።
የቢቢሲ ቦርድ “በዚህ ወቅት በዋና ዳይሬክተሩ እና በቡድናቸው የተላለፉ ውሳኔዎችን ይደግፋል” ብሏል በመግለጫው።
ኤድዋርድስ በቁጥጥር ስር ስለመዋሉ በቢቢሲ በተጠየቀበት ወቅት ትክክል መሆኑን እንዳመነ የገለጸው ቦርዱ “ይህ ባይሆን ደመወዙን በመክፈል አንቀጥልም ነበር። በቢቢሲ ላይ ያለውን እምነት በግልጽ አሳጥቶናል። ስማችንም እንዲጠፋ አድርጓል” ብሏል።
ጋዜጠኛው በሐምሌ ወር የተጋለጡ የህጻናት ፎቶዎች ጋር በተያየዘ የቀረቡበትን ሶስት ክሶች ጥፋተኛ መሆኑን አምኖ በዋስ የተፈታ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ለመስከረም ቀጠሮ ተይዟል።
ወንጀሎቹ ከ2020 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ በዋትስአፕ የተጋሩ 37 ምስሎች ጋር የተያያዘ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።አብዛኛዎቹ ከ13- እስከ 15 ዕድሜ ቢሆኑም አንዱ ከ7- እስከ 9 ዕድሜ ያለው ህጻን መሆኑ ተገልጿል።
ለአራት አስርት ዓመታት በቢቢሲ ጋዜጠኝነት የሰራው ሂው ኤድዋርድስ በተቋሙ ውስጥ ከፍተኛ ደመወዝ ከሚከፈላቸውም አንዱ ነው። በአውሮፓውያኑ 2022፣ 435 ሺህ ፓውንድ እንዲሁም በ2023፣ 439 ሺህ 999 እንደተከፈለው መረጃዎች ያሳያሉ። ጋዜጠኛው ከባለቤቱና ከአምስት ልጆቹ ጋር በለንደን ይኖራል።