ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠፈርተኞችን ወደ መሬት ለመመለስ የሄደችው የኢላን መስክ መንኩራኩር የሕዋ ምርምር ተቋም ደረሰች
ያለዕቅዳቸው ሕዋ ላይ የከረሙትን ሁለት ጠፈርተኞች ለማምጣት ያቀናችው የስፔክኤክስ መንኩራኩር ዓለም አቀፉ የሕዋ ምርምር ተቋም ደርሳለች።
ድራገን የተባለችው መንኩራኩር ሁለት ባዶ ወንበሮች አዝላ ነው ቡች ዊልሞር እና ሱኒ ዊሊያምስን ወደ መሬት ለማምጣት ያቀናችው።
ሁለቱ ጠፈርተኞች ቦይንግ ስታርላይነር በተሰኘችው መንኩራኩር ባለፈው ሰኔ ነበር ሕዋ ላይ ወደሚገኘው የምርመር ተቋም ያመሩት።
ጠፈርተኞቹ ሐሳባቸው በተቋሙ ለስምንት ቀናት ቆይቶ መመለስ ነበር። ነገር ግን የቦይንግ መንኩራኩር እክል ስለገጠማት ወደመሬት የሚመለሱበት መንገድ እስኪመቻች ጣቢያው ውስጥ ለመቆየት ተገደዋል።
ሁለቱ ሳይንቲስቶች በሚመጣው የካቲት ወደ መሬት ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ድራገን መንኩራኩር ባለፈው ቅዳሜ በናሳ ጠፈርተኞ ኒክ ሄግ እና ሩሲያዊው አሌክሳንደር ጎርቡኖቭን እየተመራች ወደ ሕዋ አቅንታለች።
መንኩራኩሯ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ እንድትመነጠቅ ዕቅድ ቢያዝላትም በፍሎሪዳ ግዛት ባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ (ሀሪኬን) ምክንያት ዘግይታለች።
መንኩራኩሯ 426 ኪሎ ተጉዛ በወቅቱ ከደቡባዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ቦትስዋና በላይ እየተንሳፈፈ የነበረው ዓለም አቀፉ የምርመር ተቋም ደርሳለች።
መንኩራኩሯን እየሾፈሩ ወደ ሕዋ የተጓዙት ሄግ እና ጎርቡኖቭ ከደረሱ በኋላ በተቋሙ የነበሩ ሌሎች ጠፈርተኞች በደስታ ሲቀበሏቸው በቪድዮ ታይተዋል።
ቦይንግ የሚያመርተው ስታርላይነር መንኩራኩር ባለፈው ዓመት ሰኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕዋ ያደረገው በረራ በቴክኒካዊ ችግር ምክንያት ያልተሳካ ሆኗል።
የናሳ እና ቦይንግ ኢንጂነሮች ብልሽቱን ለማስተካከል ወራት ቢወስድባቸውም ናሳ ሁለቱ ጠፈርተኞች በሌላ መንኩራኩር ቢመለሱ ይሻላል የሚል ውሳኔ አስተላልፏል።
የቦይንግ የጠፈር መንኩራኩር ሙከራ ላይ ሳለች ብዙ ጊዜ ችግር ይገጥማት እንደነበር ተስተውሏል። መንኩራኩሯ በአወሮፓውያኑ 2019 እና 2022 ያለሰው ያደረገችው በረራ እክሎ እንደገጠመው ይታወሳል።
ናሳ ሁለቱ አሜሪካዊያን ድርጅቶች ማለትም ቦይንግ እና የኢላን መስክ ስፔስኤክስ በሕዋ በረራ ላይ እንዲሳተፉ በሚል በ2014 ኮንራክት መስጠቱ ይታወሳል።
ቦይንግ 4.2 ቢሊዮን ዶላር ሲያገኝ ስፔስኤክስ ደግሞ የ2.6 ቢሊዮን ኮትራክት ተፈራርሟል።
በቢሊየነሩ ኢላን መስክ የተቋቋመው ስፔስኤክስ በ2020 ጠፈርተኞችን ወደ ሕዋ በማጓጓዝ የመጀመሪያው ድርጅት ሆኗል።