ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝደንት በመሆናቸው ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ምን ይጠቀማል?
በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ቀን ከሌት ሳይሉ ዶናልድ ትራምፕን ከደግፉ ሰዎች መካከል አንዱ ኢላን መስክ ነው። ትራምፕ ፕሬዝደንት በመሆናቸው እንደ ኢላን የተደሰተ ያለ አይመስልም።
መስክ የዓለማችን ቁጥር አንድ ሀብታም ነው። የምርጫውን ምሽት ፍሎሪዳ በሚገኘው ማር አ ላጎ በተሰኘ የትራምፕ ቅንጡ የመኖሪያ ቤት ነው ያሳለፈው።
“ዛሬ ምሽት የአሜሪካ ሕዝብ ለዶናልድ ትራምፕ ግልፅ የሆነ መልዕክት እና የለውጥ ኃላፊነት ነው የሰጠው” ሲል ኤክስ በተሰኘው የማኅበራዊ ሚድያው መድረኩ ላይ ጽፏል።
ትራምፕ በበኩላቸው ማሸነፋቸውን ይፋ ባደረጉ ምሽት የኢላን መስክን ስም በማንሳት አወድሰውታል። ስፔስኤክስ የተባለውን የሮኬት ኩባንያውንም ሲያደንቁለት ተሰምተዋል።
መስክ ከተመራጩ ፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር ባለው ቁርኝት ምክንያት ቴስላ የተሰኘው የመኪና ማምረቻ ኩባንያው አክሲዮን ዋጋ ጨምሯል። ይህ ማለት የተጣራ ሀብቱም ከፍ ብሏል ማለት ነው።
ኢላን መስክ በአሁኑ ወቅት 290 ቢሊየን የተጣራ ሀብት እንዳለው ይገመታል።
ባለፈው ሐምሌ ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በፔንሲልቬኒያ ግዛት በትለር ከተማ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ ነው ኢላን መስክ ለሪፐብሊካኑ ዕጩ ያለውን ድጋፍ ይፋ ያደረገው።
ከዚህ ቀደም ራሱን “ፖለቲካን በተመለከተ ለዘብተኛ ነኝ” ሲል የገለፀው መስክ በ2024 የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ ግን ትራምፕን ከመደገፍ ውጭ ምንም አማራጭ እንደሌለው ተናግሯል።
በምጣኔ ሀብት እና በስደተኞች ጉዳይ የባይደን አስተዳደር ላይ ያለውን ስጋት ሲገልፅ ቆይቷል። በዲሞክራቶች ዘመን የመናገር ነፃነት አደጋ ላይ ወድቋል ሲልም ተሰምቷል።
ከተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ቁንጮው የሆነው ቢሊየነሩ የቴክኖሎጂ ሰው ሱፐር ኤፓክ ለተባለው ፖለቲካዊ ድርጅት 119 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል። ይህ ድርጅት ትራምፕ ድጋሚ እንዲመረጡ ይሠራ የነበረ ነው።
ከምርጫው በፊት ባሉት ጥቂት ሳምንታት ወሳኝ በሚባሉ ግዛቶች መራጮች ትራምፕን እንዲመርጡ ሲቀስቅስ ነበር። የአሜሪካ ሕገ መንግሥትን ደግፈው ፊርማ ለሚያኖሩ የተመዘገቡ መራጮች ደግሞ በየቀኑ አንድ ሚሊዮን ዶላር በዕጣ ሲሰጥ ነበር።
በሎተሪ መልክ በቀን ለአንድ ሰው የሚሰጠው 1 ሚሊዮን ዶላር ሕጋዊ ነው አይደለም የሚለው ጉዳይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ዳኛው ሕጋዊ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ስሙን፣ ገንዘቡን እና ማኅበራዊ ሚድያውን ለተመራጩ ፕሬዝደንት የሰዋው መስክ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ በመመለሳቸው ብዙ ይጠቀማል።
ተመራጩ ፕሬዝደንት በሁለተኛው ዙር የመሪነት ዘመናቸው መስክን ወደ መንግሥታቸው አምጥተው በመንግሥት ውስጥ ያለውን ብክንት እንዲቆጣጠር እንደሚያደርጉት ተናግረዋል።
ይህ መሥሪያ ቤት ስሙ ‘ዲፓርትመንት ኦፍ ገቨርንመንት ኤፊሸንሲ’ አሊያም በምህፃረ ቃሉ ዶጅ እንደሚባል መስክ ጠቁሞ ነበር። ዶጅ የሚለው ስም ደግሞ ትራምፕ የሚያስተዋውቁት ክሪፕቶከረንሲ ስም ነው።
ስፔስኤክስ የተባለው የመስክ የሮኬት ኩባንያም በትራምፕ ዘመን ሊመነደግ ይችላል። ስፔስኤክስ የመንግሥት ሳተላይቶችን ወደ ህዋ ያመላልሳል።
መስክ ዋይት ሐውስ የቅርብ ሰው አለው ማለት ኩባንያዎቹ ሊጠቀሙ ይችላሉ ማለት ነው።
ስፔስኤክስ የመሰለያ ሳተላይቶችንም መገንባት ሊጀምር ነው። ፔንታገን (የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር) እና ሌሎች የአሜሪካ የስለላ ድርጅቶች እኒህን ሳተላይቶች ለማግኘት ቢሊዮን ዶላሮችን ለመክፈል ዝግጁ ናቸው።
ቴስላ የተባለውም የመኪና ማምራቸው ኩባንያም ተጠቃሚ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው። ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ምርጫውን ሲያሸንፉ የቴስላ የአክሲዮን ድርሻ 12 በመቶ ከፍ ብሏል።
መስክ የቴስላ ሠራተኞች ማኅበርን ለማቋቋም ሲሞክሩ አግዷል የሚል ወቀሳ ይቀርብበታል። ዩናይትድ አውቶ ዎርከርስ የተባለው የሠራተኛ ማኅበራት ጥምረት ትራምፕ እና መስክ ፍትሐዊ ያልሆነ ተግባር ፈፀመዋል ሲል ይወቅሳል። መስክ ተቃውሞ ያስነሱ ሠራተኞችን አባሯል ተብሎም ይወቀሳል።
ትራምፕ ለኮርፖሬሽኖች እና ለሀብታሞች ዝቅተኛ የግብር ክፍያ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።