የእርዳታ እህል ሲጠባበቁ የነበሩ 51 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር መገደላቸውን እማኞች እና የነፍስ አድን ሠራተኞች ተናገሩ

የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ የእርዳታ ማከፋፈያ ቦታ አጠገብ በከፈተው ተኩስ ከ51 በላይ ፍልስጤማውያንን መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች እና የነፍስ አድን ሠራተኞች ተናገሩ።

በሃማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ የእስራኤል ወታደሮች በካን ዮኒስ የእርዳታ ቦታ አቅራቢያ በተሰበሰበው ሕዝብ ላይ ተኩስ መክፈታቸውን እና ከ200 በላይ ሰዎች ቆስለዋል አስታውቋል።

የእስራኤል ጦር ዘገባዎቹን እየተከታተለ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

በቅርብ ጊዜ በጋዛ የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች አካባቢ በየቀኑ ከሞላ ጎደል እየተፈጸሙ ካሉት ግድያዎች አዲሱ እና ምናልባትም አስከፊው ነው።

በቅርብ ቀናት ውስጥ በጋዛ የደረሰው ጉዳት በሙሉ ማለት ይቻላል እስራኤል በሃማስ ዒላማዎች ላይ ከምታደርገው ጥቃት ይልቅ ከእርዳታ ቦታዎች ጋር የተያያዘ ነው።

ከካን ዮኒስ በስተምሥራቅ በሚገኝ መጋጠሚያ አቅራቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጣቢያ ዱቄት እናገኛለን በሚል ተስፋ ተሰብስበው በነበሩ ሰዎች ላይ የእስራኤል ኃይሎች ተኩስ መክፈታቸውን እማኞች ይናገራሉ።

የአካባቢው ጋዜጠኛ እና የዓይን እማኞች እንዳሉት የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች ሁለት ሚሳኤሎችን ከተከሱ በኋለ ብዙም ሳይቆይ ከተሰበሰበው ሕዝብ ከ400 እስከ 500 ሜትር ርቀት ላይ ከነበረ የእስራኤል ታንክ ተኩስ ከፍቷል። ፍንዳታዎቹ ብዙ ጉዳት አድርሰዋል።

ሕዝቡ የተሰበሰበው ወደ ባኒ ሱሄይላ ከተማ በሚወስደው ቁልፍ መንገድ አቅራቢያ ሲሆን ይህም አካባቢ ለሳምንታት የእስራኤል ወታደራዊ እንቅስቃሴን ያሳየ ነበር።

በአካባቢው ዋና አገልግሎት የሚሰጠው የናስር ሆስፒታል በጥቃቱ ተጎጂዎች ተጨናንቋል።

በጣም ከመጨናነቁ የተነሳ ብዙ የቆሰሉ ሰዎች መሬት ላይ ተኝተው ጉዳታቸውን የሕክምና ባለሙያዎች እያከሙ ይገኛሉ።

ክስተቱን ወዲያው የሚያሳይ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጨ ቪዲዮ በካን ዮኒስ የሚገኝ መሆኑን 'ቢቢሲ ቬሪፋይ' ለይቷል።

የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት በትንሹ 50 ሰዎች ተገድለዋል።

"የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ ዜጎቹ ተኩሰዋል። ከደቂቃዎች በኋላ የእስራኤል ታንኮች በዜጎቹ ላይ ባደረጉት የጥይት ድብደባ ብዙዎች ሰማዕት ሆነዋል፤ ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል" ብለዋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ "በካን ዮኒስ አካባቢ ከተጣበቀው የእርዳታ ማከፋፈያ መኪና እና በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የእስራኤል ወታደሮች አቅራቢያ አንድ ስብሰባ ተለይቷል" ብሏል።

"የሕዝቡን አካሄድ ተከትሎ ከመከላከያ ሠራዊት በተተኮሰ ጥይት በርካታ የተጎዱ ግለሰቦችን በተመለከተ ሪፖርቶችን እንደሚያውቅ" እና ድርጊቱ እየተገመገመ ነው ብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት በጅምላ ጉዳት የደረሰበት ሪፖርት እንደደረሰው ገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋ ቀዶ ጥገና ሐኪም ታኖስ ጋርጋቫኒስ "ይህ እንደገና የሌላ የምግብ ማከፋፈያ ላይ የደረሰ ውጤት ነው" ብለዋል።

"ከአራቱ የምግብ ማከፋፈያ ቦታዎች አቀማመጥ እና በቅርቡ የተከሰቱት የጅምላ ጉዳቶች የማያቋርጥ ግንኙነት አላቸው" ሲሉ አክለዋል።

ለሳምንታት ያህል የሕክምና ሠራተኞች የናስር ሆስፒታል ከአቅሙ በላይ ተጨናንቆ በበርካታ ተጎጂዎች ጫና ፣ በሕክምና ቁሳቁስ እጥረት እና በእስራኤል የመልቀቂያ ትእዛዝ መሥራቱን መቀጠል እንደማይችል አስጠንቅቀዋል ።

በቅርብ ቀናት ውስጥ ሆስፒታሉ በእስራኤል እና በአሜሪካ የሚደገፈው የጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን በደቡባዊ እና መካከለኛው ጋዛ በሚያስተዳድራቸው የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያ አቅራቢያ በተከሰተ ተኩስ በየቀኑ ማለት ይቻላል የሚጎርፉ ተጎጂዎችን እያስተናገደ ነው።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ምላሹ በተለምዶ ወታደሮቹ ሰዎች ወደ እነሱ እንዳይቀርቡ ያስጠነቅቃሉ፤ ከዚያም የመከላከያ ሠራዊቱ "አጠራጣሪ" ብሎ የሚጠራው እና ስጋት ይፈጥራል ተብሎ በሚታሰብ እንቅስቃሴ ሲያጋጥመው የማስጠንቀቂያ ጥይት ይተኩሳል የሚል ነው። የ

እስራኤል ጦር ከዚህ በዘለለ ምንም ዓይነት ዝርዝር ነገር አላቀረበም።

እስራኤል ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የዜና ድርጅቶች ጋዛ እንዲገቡ አትፈቅድም፤

ይህም እዚያ እየሆነ ያለውን ነገር ማረጋገጥ ከባድ ያደርገዋል።

የጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽ ጥቃቶቹ ከጣቢያዎቻቸው ርቀው እንደተፈጠሩ በመጥቀስ ከፋውንዴሽኑ ስራ ጋር በተያያዘ መጠቀስ እንደሌለባቸው በመግለጽ ምላሽ ሰጥቷል።