ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሎስ አንጀለስ ፖሊስ በፍሬንድሱ ተዋናይ ማቲው ፔሪ አሟሟት ላይ ምርመራ ከፈተ
የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ቻንድለር ቢንግ በተሰኘ ገጸ ባህርይ በመጫወት ዕውቅና ባተረፈው የፍሬንድስ ተከታታይ ፊልም ተዋናይ ማቲው ፔሪ አሟሟት ላይ ምርመራ መክፈቱን አስታወቀ።
በዘንድሮው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ህይወቱ ያለፈው ማቲው ፔሪ ኬታሚን የተባለውን መድኃኒት ከልክ በላይ በመውሰዱ እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎች ገልጸው ነበር።
አብዛኛውን ጊዜ በህክምና ወቅት ለማደንዛዣነት የሚውለው ኬታሚን እንዴት በዚህ መጠን ተዋናዩ እንዴት ሊያገኘው እንደቻለ ምርመራው ያተኩራል ተብሏል።
ኬታሚን ባስከተለው መደንዘዝ ውሃ ውስጥ ሰጥሞ እንደሞተ የተገለጸው ተዋናዩ ሞቱም አደጋ ነው በሚል ተፈርጆ ነበር።
የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ዲፓርትመንት ማክሰኞ ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ ከአሜሪካ የመድኃኒት ማስፈጸሚያ ኤጀንሲ እና የፖስታ አገልግሎት ጋር በመጣመር በ54 ዓመቱ ተዋናይ አሟሟት ምርመራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።
በቲኤምዚ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘገበው የምርመራው ሂደት ምን ያህል ርቀት እንደተጓዘ ወይም እነማን ጥያቄ እንደቀረበላቸው እስካሁን ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።
ማቲው ፔሪ ለመጀመሪያ ጊዜ መሞቱን የዘገቡት ኤልኤ ታይምስ እና ቲኤምዚ በሎስ አንጀለስ በሚገኘው ቤቱ ውስጥ በሚገኝ ገንዳ ራሱን ስቶ መገኘቱን እና በስፍራው እንደሞተ አስነብበዋል።
የሎስ አንጀለስ ግዛት የህክምና መርማሪ ቢሮ በማቲው ፔሪ አሟሟት ላይ ባደረገው ምርመራ “በደም ናሙናው ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኬታሚን መጠን ተገኝቷል” ብሏል።
የህክምና ምርምሩ ከፍተኛ ምክትል ኃላፊ የሆኑት ራፊ ዲጃቦሪያን አክለውም ለተዋናዩ ሞት መንስዔ የሆኑት ሌሎች ጉዳዮች የደም ቧንቧ ችግር እና ኦፒዮድ የተሰኘውን አደንዛዥ ዕፅ ችግር ለማከም የሚጠቅመው የቡፕረኖርፎን መድኃኒት ተጽእኖ ነው ብለው ነበር።
ማቲው ፔሪ ከጭንቀት እና ድብርት ህመም ጋር በተያያዘ በህክምና የታዘዙ የኬታሚን እንክብሎችን ይወስድ የነበረ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ ይህ መድኃኒት የታዘዘለት ከመሞቱ አንድ ሳምንት ተኩል በፊት ቀደም ብሎ ነበር ተብሏል።
ተዋናዩ ለብዙዎች የፈገግታ ምንጭ ቢሆንም ከፍተኛ ታዋቂነትን ባገኘበት ወቅት ከህመም ማስታገሻዎች እና የአልኮል ሱስን እየታገለ ነበር።
በርካታ ጊዜያትም የመልሶ ማገገሚያ ክሊኒኮችም ገብቶ ነበር።
ፍሬንድስ ተከታታይ ፊልም በሚቀረጽበት ወቅት በመጠጥ እና በአደንዛዥ ዕጽ ለሶስት ዓመታት ያህል ቀረጻውን እንደማያስታውስ ከቢቢሲ ጋር ከአውሮፓውያኑ 2016 ባደረገው ቆይታ ገልጾ ነበር።
በዚህም የተነሳ በርካታ የጤና ዕክሎች የገጠሙት ሲሆን ከነዚህም መካከል አንጀቱ በመፈንዳቱ ለሰባት ሰዓታት ቀዶ ጥገኛ አድርጎ ነበር። ለሁለት ሳምንታትም ያህል በጽኑ ህሙማን ማቆያ አሳልፏል።
ማቲው ፔሪ በሌሎች ፊልሞች ላይ ቢተውንም ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ለአስር ዓመታት ከአውሮፓውያኑ 1994- 2004 በታየው ተወዳጁ ሲትኮም ‘ፍሬንድስ’ ነው።
በስድስት ጓደኞች ላይ የሚያተኩረው ‘ፍሬንድስ’ በጓደኝነት ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ከተሰራበት አሜሪካ ውጪም በርካታ የዓለማችን የፊልም አፍቃሪዎች ተወዳጅነትን አግኝቷል።
የመጨረሻው የፊልሙ ክፍል በ52.5 ሚሊዮን ህዝብ የታየ ሲሆን በ2000ዎቹ በከፍተኛነት በመታየት የመጀመሪያ ደረጃ ተቀምጧል።