የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የመንግሥት ድርድር ለምን ያለስምምነት ተቋጨ?

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላለፉት አምስት ዓመታት ያደረጉትን ጦርነት በንግግር ለመፍታት በመወሰን በዛንዚባር ንግግር የጀመሩት ከወራት በፊት ነበር።

በመጀመሪያው ዙር ድርድር ማን ምን ይፈልጋል የሚለውን የለዩበት አንደነበር የሚናገሩት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ወክለው የተሳተፉት አቶ ጅሬኛ ጉደታ ይህም ለሁለተኛ ዙር ድርድር መንገድ የጠረገ እንደነበር ይጠቅሳሉ።

ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው ንግግር በመልካም መግባባት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ለሁለተኛ ዙር ድርድር በታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬ ሰላም ተገናኝተው ነበር።

የሁለተኛው ዙር ድርድር በሁለቱም ወገን ደጋፊዎች በኩል መግባባት ላይ ተደርሶ የሰላም ንግግሩ በፊርማ ይጠናቀቃል የሚል እምነት አሳድሮ ነበር።

ለዚህም ምክንያት የሆነው ከፍተኛ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መኮንኖች በንግግሩ ላይ መሳተፋቸው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥትም ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮቹ በቀጥታ በውይይቱ ላይ ተሳትፈው ነበር።

በኦሮሞ ነጻነት ግንባር በኩል ዋና አዛዡ መሮ ድሪባ፣ ምክትሉ ገመቹ አቦዬ እና ሌሎችም ሲሳተፉ በኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ የነበሩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዲሁም የፍትህ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር) ተሳታፊ ነበሩ።

በአደራዳሪነት ደግሞ አሜሪካ፣ ኖርዌይ እንዲሁም የኢጋድ ተወካዮች ሲሳተፉ፣ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድጋፍ መስጠቱን ቢቢሲ በወቅቱ ተሳታፊ ከነበሩ አካላት መረዳት አችሏል።

ይህ ከሳምንት በላይ በዝግ የተካሄደው ስብሰባ ባለመግባባት ተጠናቅቋል።

በወቅቱ ሁለቱ አካላት እንዳልተስማሙ ከመግለጻቸው በስተቀር ያላግባቧቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ምንም ዓይነት ማብራሪያ እስከ ዛሬ ድረስ አልሰጡም።

የኦሮሞ ነጻነተ ሠራዊት አዛዥ መሮ ድሪባ ዋና አማካሪ የሆኑት እና በድርድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ጅሬኛ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ የዳሬሰላሙ ድርድር ለምን ሳይሳካ እንደቀረ ሲናገሩ “ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ” ጉዳዮች እንዳላግባቧቸው ተናግረዋል።

አቶ ጅሬኛ በዳሬሰላሙ ድርድር መጀመሪያ ላይ በሁለቱም ወገኖች በኩል ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኝነት የነበረበት ነው ይላሉ።

“ለዚህ አንዱ ማሳያ ብዙ ጊዜ ተገድሏል ሲባል የነበረው መሮ ድሪባ እና ሌሎች የጦሩ አመራሮች መገኘታቸው ነው።”

አደራዳሪዎቹም ቢሆኑ እነ መሮ ይመጣሉ የሚል ሙሉ እምነት አንዳልነበራቸው የሚያስታውሱት አቶ ጅሬኛ “ሲመጣ ግን እኛንም አስደስቶናል” ሲሉ በወቅቱ የነበውን ስሜት ያስታውሳሉ።

እርሱን ከምዕራብ ኦሮሚያ ዳሬሰላም ለማምጣትም ቢሆን አደራዳሪዎቹ ከፍተኛ ኦፕሬሽን ማካሄዳቸውን ይናገራሉ።

“እንግዲህ ሁለተኛ ዙር ውይይት ላይ ብዙ ርዕሶችን አንስተን ተነጋግረናል። ግን ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ዋና ዋና አከራካሪ ሀሳቦች አንዱ የአገሪቱ ወታደራዊ እና ደኅንነት እና የፖለቲካ ጉዳዮች" እንደነበሩ አቶ ጅሬኛ ጠቅሰዋል።

ዋና አከራካሪ የነበረው እና ያላስማማቸው ነጥብ በአገሪቱ የሚገኙ የፀጥታ አካላት አወቃቀር እና አመራርን በተመለከተ አካታች እንዲሆን የተነሳው ነጥብ ነው ይላሉ።

በዚህ ንግግር የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፌደራል እስከ ክልል ባሉ የፀጥታ አካላት አወቃቀር ላይ አካታች በሆነ መልኩ እንደገና እንዲዋቀሩ መጠየቁን አቶ ጅሬኛ ጠቅሰዋል።

“ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ፣ አመራር ውስጥ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል የሚል አንስተናል። እነርሱ አልተቀበሉትም።”

ቢቢሲ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራር የአገሪቱ መከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ ውስጥ እንዲካተት ስለመጠየቃቸው አቶ ጅሬኛን ጠይቆ ይኸው መከናወኑን አመልክተዋል።

“እዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር ያለባቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና መንግሥት ናቸው ብለን እናምናለን። በሌሎች ፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲካተቱ አንስተናል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኩል በኢትዮጵያ ከፍተኛ ችግር ነው ብሎ የሚያነሳው የፖለቲካ ጉዳይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጅሬኛ፣ “እርሱ መፍትሄ ስላላገኘ ነው ወደ ትጥቅ ትግል የገባነው” ይላሉ።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሳተፈ ሁኔታ የዜጎች መብት የሚከበርበት፣ የሚዲያ ነጻነት የሚረጋገጠበት፣ ነጻ ምርጫ ቦርድ የሚኖርበት፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሰፋበት ሥርዓት እንዲገነባ፣ የፍትህ አካላት ነጻነት እንዲኖራቸው በወቅቱ መጠየቁን ይገልጻሉ።

አቶ ጅሬኛ “ይህ ጉዳይ ሲነሳ መንግሥትን የወከሉ ተደራዳሪዎች አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ጥያቄ የለም። በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ነው ሥልጣን የያዘው። ሕገ መንግሥቱን በጠበቀ መልኩ ትጥቃችሁን ፈትታችሁ ግቡ” የሚል ምላሽ መስጠቱን ያነሳሉ።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ “የሕዝብ ጥያቄ አለ፣ የአገሪቱን ወታደር እና የፖሊስ ኃይልን መንግሥት ይዞ ሕዝቡን እያፈነ እና ነጻነቱን እያሳጣ መሆኑን በመጥቀስ የራሱን ዕድል በራሱ አንዳይወስን እያደረገ መሆኑን” በመጥቀስ መከራከራቸውን ይናገራሉ።

“የአገር ጦር ሠራዊት ፖለቲካ ውስጥ መግባት የለበትም፣ ለፓርቲም ተገዢ አይሁን” ሲሉ መከራከራቸውንም አክለው ተናግረዋል።

“መንግሥት የራሱን ሥልጣን ለመከላከል የአገሪቱን ፖሊስ እና ወታደር እየተጠቀመበት ነው” የሚሉት አቶ ጅሬኛ፣ የፀጥታ ኃይሉ የተቃዋሚውም ሆነ የገዢው ፓርቲም መከታ መሆን አለበት ብለው ቢከራከሩም ከመንግሥት ወገን ይህ ተቀባይነት አለማግኘቱን አቶ ጅሬኛ ይናገራሉ።

መንግሥት የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በተከተለ እና ባከበረ ሁኔታ እየሠራ መሆኑን በመጥቀስ መከራከራሩን ጨምረው አስረድተዋል።

ሌሎች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ወሰንን በተመለከተ በወሎ፣ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ባከበረ እና ባለቤትነት በተረጋገጠ መልኩ እንዲሆን መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት ይህንን ጥያቄ ሕገ መንግሥቱን በጠበቀ መንገድን እንመልሳለን የሚል መልስ መስጠቱን እና መግባባት ላይ መድረሳቸውን ያስረዳሉ።

ሌላው መግባባት ላይ የደረሱበት ኦሮምኛ የፌደራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን የሚለው ጥያቄ መሆኑን ያነሱት አቶ ጅሬኛ፣ ይህም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተፈጻሚ አንደሚሆን መግባባታቸውን አመልክተዋል።

ድርድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በኩል መንግሥት መሮ ድሪባን ጨምሮ ለኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ሥልጣን ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ተጠይቀው ይህንን አረጋግጠዋል።

“ለሺህ ሰው የሚሆን ከፌደራል እስከ ክልል የታችኛው መዋቅር ድረስ ሥልጣን የመስጠት ጥያቄ ለማቅረብ አስበው ነበር” በማለት አለመቀበላቸውን ተናግረዋል።

“እኛ እንደ ግል የጠየቅነው ሥልጣን የለም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሠራ ሥርዓት እንዲገነባ ነው የጠየቅነው። ያ ሥርዓተ ሲኖር በጦርነት እና በጉልበት ሕዝቡንም አታስቸግርም። . . . ሥልጣን የመጨረሻ ግባችን አይደለም። ጠንካራ ሥርዓትን መገንባት ነው። እነርሱ ደግሞ ሥልጣን የመጨረሻ ግባችን እንደሆነ አድርገው ነው ለግለሰቦች ሥልጣን ለመስጠት ያሰቡት።”

መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከሳምንት በላይ በዳሬ ሰላም ያደረጉት ድርድር ባለመስማማት መጠናቀቁን ተከትሎ የመንግሥት ተወካዮቸ አዳራሹን ጥለው መውጣታቸውን አቶ ጅሬኛ ይናገራሉ።

ለአቶ ጅሬኛ ሦስተኛ ዙር ድርድር ይኖራል ተብለው ተጠይቀው “የሁለተኛው ዙር ድርድር አጨራረስ ጥሩ ስላልነበረ ከአደራዳሪዎቹ ጋር ሳንነጋገር ቆይተናል” ይላሉ።

አደራዳሪዎቹ ሰሞኑን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮችን ስለ ሦስተኛ ዙር ድርድር ማነጋገራቸውን የተናገሩት አቶ ጅሬኛ “በተጨባጭ ግን መቼ እና የት ይካሄዳል የሚል ስምምነት የለም” ብለዋል።

መሮ ወደ ዳሬሰላም እንዴት ሄደ?

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዥ ይገኝበታል ከሚባለው የምዕራብ ኦሮሚያ ድርድሩ ወደ ሚካሄድበት ዳሬሰላም ማን ወሰደው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል አቶ ጅሬኛ።

“ከመንግሥት ጋር አንድም ቀን መተማመን የለንም” ካሉ በኋላ፣ ነገር ግን አደራዳሪዎቹ ከመንግሥት ጋር መግባባት ላይ የደረሱበት ነገር መኖሩን ያነሳሉ።

መሮን ከነበረበት በሂሊኮፕተር አንስቶ ወደ ደምቢዶሎ ከተማ የወሰደው የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከደምቢዶሎም በአውሮፕላን ናይሮቢ፣ ከናይሮቢ ዳሬሰላም እንደሄደ አቶ ጅሬኛ ጨምረው ተናግረዋል።

ከድርድሩ በኋላስ የአማጺው ቡድን መሪ ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ለመመለስ ግን ያጋጠመ ችግር ነበር ይላሉ አቶ ጅሬኛ።

“የኢትዮጵያ መንግሥት ቃሉን አልጠበቀም። ቀይ መስቀል እና ሌሎቹ መካከላችን የነበሩ አካላት ወዳመጡበት የመመለስ ኃላፊነት ቢኖርባቸውም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለመፍቀዱ መመለስ አንዳልቻሉ ነገሩን።”

“እኛ በራሳችን መንገድ ወደ መጡበት አንዲመለሱ አድርገናል፤ ዝርዝሩን ሌላ ጊዜ” በማለት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል ሲሉ ተናገረዋል።