ቀይ መስቀል በኦሮሚያ ያለው ግጭት በጤና ስርዓቱ ላይ ቀውስ ፈጥሯል አለ

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበር በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት በመሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል አለ።

ቀይ መስቀል ግጭቱ የጤና እና የንፁህ ውሃ አቅርቦት ስርዓትን ቀውስ ውስጥ ከትቷል ብሏል።

አንደ ማሳያም በምዕራብ ወለጋ ቤጊ ወረዳ የሚገኙት የጤና ተቋማት እና የንፁህ ውሃ አቅርቦት መሠረት ልማቶች ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸዋል።

እንደ ቀይ መስቀል ከሆነ በወረዳው ለ100 ሺህ ሕዝብ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ 42 የጤና ማዕከላት እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል አልያም ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል።

የጤና ማዕከላቱ በደረሰባቸው ከፍተኛ ውድመት አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ ለሕይወት አስጊ የሆነ የጤና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሕክምና ማግኘት አልቻሉም።

በዞኑ የአምስት ወረዳ ሕዝብን የሚያገለግለው ጉዱሩ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግድግዳዎች በጥይት ተበሳስተዋል። የውሃ ማጠራቀሚያው ወድሟል። በሽተኞች ተኝተው የሚታከሙባቸው አልጋዎች፣ ሕክምና መስጫ መሳሪያዎች፣ መድሃኒቶች እና አምቡላንሶች ተዘርፈዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ግጭትን ሽሽት ወደ ቤጊ ከተማ በርካቶች መሰደዳቸውን ተከትሎ የጤና አገልግሎት ፈላጊዎች ቁጥር መጨመሩን ቀይ መስቀል ገልጿል።

“በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢው በመምጣታቸው የሥራ ባልደረቦች ለሕዝቡ የጤና አገልግሎት ለማቅረብ ተስኗቸዋል” ይላል ትናንት ምሽት የወጣው የቀይ መስቀል መግለጫ።

“የአደጋ ጊዜ መድሃኒት እጥረት አለብን። ቀዶ ሕክምና መስጫ ክፍል የለም። በሽተኛ የሚተኛበት አልጋ የለንም። በውሃ ማጠራቀሚያው ላይ ውድመት በማጋጠሙ አሁን ደግሞ የውሃ እጥረት ተከስቷል። የማሕብረሰብ መድሃኒት ቤትም ወድሟል፤ ሁሉም መድሃኒቶች እና መሳሪያዎች ተወስደዋል” በማለት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ኪሪ ተናግረዋል።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን በሚያደርገው የትጥቅ እንቅስቃሴ በኦሮሚያ ክልል መረጋጋት ከጠፋ ዓመታት ተቆጥረዋል።

መንግሥት ‘ሸኔ’ ብሎ የሚጠራው ቡድን የትጥቅ ትግሉን ሲጀምር በስፋት ይንቀሳቀስ የነበረው በምዕራብ ኦሮሚያ የወለጋ ዞኖች እንዲሁም በጉጂ እና ቦረና አካባቢዎች ነበር።

አሁን ግን ታጣቂ ቡድኑ የትጥቅ ትግሉን እንቅስቃሴ በማስፋት ከላይ ከተጠቀሱት የኦሮሚያ አካባቢዎች በተጨማሪ በመካከለኛው የኦሮሚያ አካባቢዎች በስፋት ይንቀሳቀሳል።

ይህ ቡድን የመንግሥት ባለስልጣናትን እና ሰላማዊ ሰዎችን በማገት እና በመግደል እንዲሁም የሕዝብ ንብረትን በመዝረፍ እና በማውደም ሲከሰስ ቆይቷል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበር ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ላይ ችግር አስከትሏል ብሏል።

ከእነዚህም መካከል በርካቶች አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል ያለ ሲሆን፤ ግጭት በተካሄደ ቁጥር ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ አዳጋች ስለሚሆን የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቁጥር ይጨምራል ብሏል።

ማሕበሩ በጉጂ፣ በወለጋ ዞኖች እና በቦረና የሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን አመልክቷል።

“የጦር መሳሪያ ተኩስ መቋቋም የሚቻል አይደለም፤ ሕይወታችንን ለማዳን ተሰደድን። እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ ለልጆቼ በጣም ከባድ ነበር። ሁሉንም ነገር አጥተናል። እዚህ ከመጣን ምንም አይነት ዕርዳታ አላገኘንም። ስላለንበት ሁኔታ መጥቶ እንኳ የጠየቀን የለም” በማለት የ7 ልጆች እናት የሆነችው ተፈናቃይ ሙሉ ታከለ ቃሏን ለማሕበሩ ገልጻለች።

ቀይ መስቀል በኦሮሚያ ግጭት ሸሽተው የተፈናቀሉትን ሲረዳ መቆየቱን ይገልጻል።

ማሕበሩ ባለፉት ስድስት ወራት ከ62ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ምግብ፣ መገልገያ ቁሳ ቁስ፣ መጠለያ እና የጥሬ ገንዘብ ዕርዳታ ማድረጉን ገልጿል።