ታይታኒክን ለመመልከት ወደ ጥልቁ ባሕር የሄዱት ሕይወታቸው አለፈ

የታይታኒክ መርከብ ቅሪትን ለመመልከት ወደ ጥልቁ ባሕር ከሄዱ በኋላ መድረሻቸው ጠፍቶ ሲፈለጉ የነበሩት አምስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

ዕድሜያቸው ከ19-77 የሚገኙት አምስቱ ወንዶች ከረዥም ዓመታት በፊት የሰጠመችውን ታይታኒክ መርከብ ለመመልከት ነበር እሁድ ዕለት ወደ ጥልቁ ባሕር ጉዞ ካደረጉ በኋላ ግንኙነታቸው የተቋረጠው።

የጠፉትን ሰዎች ለማግኘት ከተለያዩ አገራት የተሰባሰቡ ባለሙያዎች ፈለጋ ሲያደርጉ ቆይተው ትናንት የሰዎቹ ሕይወት ማለፉን ክፍያ እየተቀበለ ወደ ጥልቁ ባሕር ጉዞ የሚያደርገው ኩባንያ አስታውቋል።

ግለሰቦቹን እንዲፈልግ ወደ ባሕሩ የተላከው ሮቦት ባሕር ሰርጓክ ሰዎቹ ሲጓዙበት የነበረችው ሰርጓጅ መርከብ ስብርባሪን ከታይታኒክ መርከብ 480 ሜትር ርቆ አግኝቷል።

ግለቦቹ ሳይሞቱ አይቀሩም የተባለው ጉዞ ከጀመሩ በሰዓታት ልዩነት ሰርጓጅ መርከቧ ላይ ባጋጠመ ፍንዳታ ሳይሆን አይቀርም እየተባለ ነው። የአሜሪካ የባሕር ድንበር ጥበቃ ዘብ ግን እስካሁን ፍንዳታው የት እና መቼ እንዳጋጠመ በትክክል መግለጽ አይቻለኝም ብሏል።

ይሁን እንጂ 4 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ካለው የባሕር ወለል ከታይታኒክ መርከብ 500 ሜትር ገደማ ርቆ የሰርጓጅ መርከቧ ስብርባሪ ተገኝቷል።

ሟቾቹ ሰርጓጅ መርከቧን የሚያስተዳድረው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቶክቶን ራሽ፣ እንግሊዛዊው ብሊየነር ሃሚሽ ሃርዲንግ፣ ፈረንሳይዊ ባሕር ጠላቂ ፖል-ሄነሪ ናርጌሎት እንዲሁም እንግሊዛዊው የንግድ ሰው ሻህዛዳ ዳውድ ከልጃቸው ሱሌይማን ዳውድ ጋር የቱሪስት ሰርጓጅ መርከቧን ተሳፍረው ነበር።

ግለሰቦቹ ሕይወታቸው አልፏል ተብሎ ይደምደም እንጂ አስክሬናቸው አልተገኘም።

የአሜሪካ የባሕር ድንበር ጥበቃ ኃላፊዎች በባሕሩ ላይ ባለው ከባድ የአየር ጸባይ ምክንያት የሰዎቹን አስክሬን እናገኛለን ብለን መናገር አይቻለንም ብሏል።

የግለሰቦቹን ሞት ተከትሎ መሪዎች እና ተዋቂ ግለሰቦች የተሰማቸውን ሐዘን እየገለጹ ይገኛሉ። ዋይት ሃውስ የሟች ቤተሰቦችን አጽናንቷል። ዋይት ሃውስ ባለፉት ቀናት የቤተሰብ አባላት የቤተሰቦቻቸው እጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ሳያውቁ ከባድ ውጥረት ውስጥ መቆየታቸውን ገልጾ መጽናናትን ተመኝቷል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ደግሞ በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቤተሰቦችን በዚህ ፈታኝ ግዜ እደግፋለሁ ብላለች።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጄምስ ክሌቨርሊ መንግሥት ለእንግሊዛውያን ቤተሰቦች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው በጸሎታችን እናስባቸዋለን ብለዋል።

እአአ በ1912 በሰሜን አትላንቲክ ባሕር የሰጠመችውን ዝነኛዋን ታይታኒክን ለመመልከት 4 ኪሎ ሜትር ገደማ ወደ ጥልቁ ባሕር ለመጓዝ ኦሽን ጌት የተባለው ኩባንያ እስከ 250 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስከፈል ተገልጿል።