ሞ ሳላ ቀጣዩ የሳዑዲ ሊግን የሚቀላቀለው ኮከብ ይሆን? የራይስ፣ ማዲሰን፣ ማውንት ዝውውር ከምን ደረሰ?

የሊቨርፑሉ የፊት መስመር ተጫዋች ሞሐመድ ሳላ ወደ ሳዑዲ ሊግ ሊያመራ ይችላል የሚሉ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።

እንደ ካሪም ቤንዜማ እና ኢንጎሎ ካንቴ ያሉ ኮከቦች ወደ ሳዑዲ ፕሮ ሊግ ከተዘዋወሩ በኋላ የሊጉ ክለቦች ቀጣይ ትኩረታቸው ሞ ሳላ ነው ብሏል ፎር ፎር ቱ የተባለው ጋዜጣ።

በአርሰናል ቤት ደግሞ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የዌስት ሃሙ አማካይ ደክላን ራይስ ወደ ሰሜን ለንደን ከመጣ የመድፈኞቹ አምበል ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ሜይል አስነብቧል።

አርሰናል ራይስን ለማስፈረም ሁለት ግዜ ይፋዊ ጥያቄ ቢያቀርብም ዌስት ሃም በቀረበው ገንዘብ ደስተኛ ሳይሆን ቀርቶ የዝውውር ጥያቄው ውድቅ ተደርጓል።

በዚህ መሃል ቻምፒዮኖቹ ማንቸስተር ሲቲዎች አማካዩን ለመወሰድ ለዌስት ሃም ጥያቄ ሊያቀርቡ መሆኑ ተገልጿል።

አሁን እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚጠቀሙት አርሰናል ራይስን ለመውደስ 100 ሚሊዮን ፓዎንድ የሚደርስ ከፍያን ለዌስት ሃም ለማቅረብ ዝግጅት ላይ ነው።

አማካዩ ራይስን የክለቡ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ወደ ሰሜን ለንደን ለማምጣት እየጣረ የሚገኘው አርሰናል ጋናዊውን አማካይ ለመሸጥ ዝግጁ ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው።

ስካይ ሰፖርት ጣሊያን የ30 ዓመቱ ቶማስ ፓርቴ ከጣሊያኑ ጁቬንቱስ ጥያቄ የሚቀርብለት ከሆነ ወደ ክለቡ ለማቅናት ፍላገት እንዳለው ተገልጿል።

ሚረር ደግሞ ቼልሲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በሜሰን ማውንት ዝውውር ላይ ከመግባባት እየደረሱ ነው ሲል አስነብቧል።

እንደ ሚረር ዘገባ ከሆነ ዩናይትድ እና ቼልሲ ለ24 ዓመቱ እንግሊዛዊ አማካይ 60 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ክፍያ ለመፈጸም ከጫፋ ደርሰዋል።

በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት ችሎታውን ማሳየት የተሳነው ዶኒ ቫን ዲ ቢክ ወደ ሮማ ሊያቀና እንደሚችል የዘገበው ደግሞ ሜትሮ ነው። ዩናይትድ ለሞሪኒዮው ሮማ የሆላንዱን የ26 ዓመት አማካይ ውሰዱልኝ ስለማለቱ በሜትሮ ዘገባ ተመላክቷል።

ጋርዲያን ደግሞ የሌስተር ሲቲው ጄምስ ማዲሰን የለንደኑን ክለብ ቶተነሃምን የመቀላቀል ትልቅ ዕድል አለው ብሏል። የ26 ዓመቱ ማዲሰን ክለቡ ሌስተር ሲቲ ከፕሪሚየር ሊጉ ከወረደ በኋላ ክለቡን ከሚለቁ ኮከቦች መካከል ስሙ በስፋት ሲነሳ ቆይቷል።

ባየር ሚዩኒክ ደግሞ የማንቸስተር ሲቲውን የቀኝ መስመር ተከላካይ ካየል ዎከርን ሊያስፈርም ፍላጎት እንዳለው ብሊንድ ዘግቧል። የ32 ዓመቱ ዎከር ከጀርመኑ ክለብ የሁለት ዓመት ውል ቀርቦለታል።

ፉልሃም ደግሞ እንግሊዛዊውን ጄምስ ዎርድ ፕራወስ ከሳውዝሃምፕተን ለመወሰድ በሚደረገው ፉክክር ቀዳሚ መሆኑ ተገልጿል። ሳውዝሃምፕተን ከፕሪሚየር ሊጉ ከወረደ በኋላ ፕራዎስ ወደ ክራቨን ኮቴጅ ለመሄድ ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል።