የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት እና የክተት ጥሪ ስጋት ላይ የጣላቸው ቤተሰቦች

ባለፈው ሳምንት የኤርትራ መንግሥት፣ የአገሪቱ ተጠባበቂ ኃይል አባላት በየአካባቢያቸው ሪፖርት እንዲያደርጉ እና ወደሚመደቡባቸው ቦታዎች እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ማቅረቡን ቢቢሲ ታማኝ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል ለዚሁ ዘገባ በሰጡት ምላሽ “መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለማጣመም ሆን ተብሎ የተጋነነ ነው” በማለት ተችተዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ጥሪ የተደረገላቸው የተጠባባቂ ኃይሎ አባላት ቁጥር በጣም ትንሽ መሆኑን በመግለጽ፣ "አጠቃላይ የክተት ጥሪ እንደተደረገ ሆኖ መቅረቡ አሳሳች ነው" ብለዋል።

ነገር ግን በግዳጅ የታፈሱ እና ለክተት የተጠሩት ተጠባባቂ ኃይል አባላት ቤተሰቦች፣ ፍርሃታቸውን እና ስጋታቸውን ለቢቢሲ ትግርኛ አጋርተዋል።

'አባቴ እና ወንድሜ ወደ ግዳጅ ሄደዋል'

ኑሮዋን በአውሮፓ ያደረገችው ትዕግስት አባቷ የኤርትራ መንግሥት ያቀረበውን የክተት ጥሪ ተከትሎ ወደ ሠራዊቱ ከተቀላቀሉ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ትዕግስት አባቷ ብቻ ሳይሆኑ ወንድሟም የመንግሥትን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ግዳጅ ሄዷል።

የትዕግስት አባት ግን መጀመሪያ ላይ ለጥሪው ምላሽ መስጠት አልፈለጉም ነበር።

ይህ ግን በኤርትራ ባለሥልጣናት ዘንድ ግን በበጎ አልታየም።

አባቷ አልዘምትም ስላሉ ብቻ እናቷን እና ታናናሽ ወንድሞቿ ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው ሌላ ስፍራ እንዳሰፈሩዋቸው፣ ከብቶቻቸውም ከማደሪያቸው እንዳይወጡ መደረጉን ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ተናገራለች።

አባቷ ይህንን ሲመለከቱ ለቤተሰባቸው ደኅንነት ሲሉ እጃቸውን እንደሰጡ የምትናገረው ትዕግስት፣ ጦርነቱ የኤርትራ ሕዝብ እንዳልሆነ እና አባቷና ወንድሟ “ለቤተሰቧ ደኅንነት ሲሉ ተገድደው ወደ ጦርነት ተወስደዋል” ብላለች።

ማክሰኞ ዕለት፣ ከተከዜ ወንዝ እስከ ኢሮብ ባሉት የድንበር አካባቢዎች ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ እንደሆነ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሰማችው ዊንታ ደግሞ “እየደማን የምንኖረው እስከ መቼ ነው?” በማለት ትጠይቃለች።

ዊንታ በኤርትራ ሠራዊት ውስጥ ሁለት ወንድሞቿ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ለቢቢሲ አስረድታለች።

“ለትውልድ. . . ጦርነትና ሞት ለምን እናወርሳለን?” የምትለው ዊንታ፣ “ሕግና ሥርዓትን፣ ፍትሕና ርትዕን፣ ትምህርትንና እውቀትን፣ ፍቅርንና ወንድማማችነትን፣ ፈሪሐ እግዚአብሔርን ማውረስ እንጂ፣ ጦርነትንና ጥፋትን፣ ትዕቢትንና ዘረፋን አይወረስም” በማለት በምሬት ትናገራለች።

ቤተሰቦች የገቡበት የሥነ ልቦና ጫና

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ቤተሰቦቻቸው የኤርትራ መንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ግዳጅ የሄዱ ቤተሰቦች የተለያየ የሥነ ልቦና ጫና ላይ መውደቃቸውን ይናገራሉ።

በኤርትራ ዓንሰባ ዞን ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሀንሱ* “ልጆቻችንን በሱዳን እና በሰሃራ በኩል በመጓዝ ለሞት አሳልፈናል ሰጥተናል። አሁን ግን ባሎቻችን እና የተቀሩት ልጆቻችን ታፍሰው ወደ ጦርነት እንዲገቡ ሲደረጉ የምናደርገውና የምንናገረው አናቅም” በማለት ተስፋ በመቁረጥ ይናገራሉ።

በርካታ ኤርትራውያን በአገሪቱ ባለው ገደብ በሌለው ብሔራዊ አገልግሎት ምክንያት አገራቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ወደሌሎች አገር ለመሰደድ መዳረጋቸውን የመብት ተቋማት ይገልጻሉ።

በዚህ ምክንያት የተፈጠረው የቤተሰብ መለያየት እና መጠፋፋት በኤርትራውያን ቤተሰቦች ላይ ትልቅ የሥነ ልቦና ጠባሳ መጣሉን ይነገራል።

ከ1998 እስከ 2000 (እኤአ) በነበረው ደም አፋሳሽ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጥፎ ትውስታ ያላቸው እና ኑሯቸውን በካናዳ ያደረጉት ሑበዲን በበኩላቸው “እኛ የከፈልነውን መስዋዕትነትን ተከትሎ በደስታ መኖር የሚገባቸው፣ ከ2000 በኋላ የተወለዱ ታናናሽ ወንድሞቻችን ናቸው አሁን ወደ ጦርነት እየተማገዱ ያሉት” ይላሉ።

“ይህ ጉዳይ በእኛ ዘንድ እንደተጠናቀቀ ነበር ያሰብነው። የሲናይን እና ሰሃራን በረሀዎችን አቋርጠን ተሰደን እስራኤልን ገባን፤ አሁን ደግሞ እዚሁ ደረስን። ነገር ግን ቤተሰቦቻችን በአገራቸው ደስተኛ እንዳልሆኑ፣ በግዳጅ የውትድርና አገልግሎት ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸው፣ የእኛ ልፋት ትርጉም የለሽ የሆነ መስሎ ይሰማናል” በማለት አቶ ሑበዲን ያስረዳሉ።

የኤርትራን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ደስበለ መሓሪ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በኤርትራ ከብቶቻቸውና ንብረታቸው የተዘረፈባቸው ቤተሰቦች፣ አረጋውያንና ነፍሰጡሮች ሳይቀሩ በሀዘንና በብስጭት እንዲሁም በጤና እክል እየተሰቃዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በኤርትራ ታሪክ ውስጥ እንደ ጥቁር ጠባሳ የሚያወሱት አጋጣሚ ሆኖ እንደሚያልፍ ይናገራሉ።

ሁለት ወንድሞቿ በጦር ግንባር የሚገኙት ዊንታም ሆነች ወ/ሮ ሀንሱ ለጭንቀታቸውን እና ስጋታቸው መፍትሄን ከመንግሥት በቅርብ እንደማያገኙ ተሰምቷቸዋል።

ወ/ሮ ሀንሱ “በሰሃራ እና በሲናይ በረሃዎች ዘመዶቻችን እና ወንድሞቻችን መጥፋታቸው ሳይበቃ አሁን ደግሞ ጦርነት ተጨምሮበታል። ይህንን ከሰማሁ ጊዜ ጀምሮ እንቅልፍ የሚባል በዐይኔ ዝር ሳይል ነው የማድረው” ይላሉ።

* ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው የተቀየረ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የኤርትራ ተሳትፎ

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ዳግም ማገርሸቱንም ተከትሎ በኤርትራ ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በታች የሆኑ ተጠባባቂ የጦር ኃይሉ አባላት በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የካናዳ መንግሥት በትዊተር በኩል ያሰራጨውን የጉዞ ማሳሰቢያን ጠቅሶ እንደዘገበው በኤርትራ አጠቃላይ ጥሪ ለሠራዊቱ አባላት መቅረቡን አመልክቷል።

“በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ተከትሎ የአካባቢ ባለሥልጣናት ለሠራዊቱ በአጠቃላይ የክተት ጥሪ አቅርበዋል” ብሏል ከካናዳ መንግሥት ኤርትራን አስመልክቶ የወጣው የጉዞ ማሰሰቢያ።

ይህ የትዊት መልዕክት እንዳለው ጥሪው አስከ 60 ዓመት የሚሆኑ የተጠባባቂ ኃይል አባላትን ይመለከታል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።

የሠራዊት እንቅስቃሴ ጥሪ መቅረቡን ተከትሎ ካለ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ተጨማሪ የደኅንነት እርምጃዎች በመላዋ ኤርትራ ሊወሰዱ ይችላሉ ካለው የካናዳ መንግሥት በተጨማሪ፣ የብሪታኒያ መንግሥትም በኤርትራ ላሉ ዜጎቹ የጉዞ ማሳሰቢያ አውጥቷል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት አቶ የማነ ገብረመስቀል ለተጠባባቂው ኃይል የቀረበውን ጥሪ በተመለከተ “ሆን ተብሎ እውነታው እንዲዛባ እና እንዲጋነን ተደርጓል” ሲሉ ለአንድ የጀርመን ድረገጽ ተናግረዋል።

እርሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ አንድ ዲፕሎማት ለሮይተርስ እንደተናገሩት “በኤምባሲዎች፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግቢ እና በመኖሪያዎች ውስጥ የሚሰሩ የጥበቃ ሠራተኞች በስፋት እየተካሄደ ባለው ምልመላ ምክንያት እነሱም ሊካተቱ እንደሚችሉ በመግለጽ ስጋት ውስጥ ናቸው” ብለዋል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት አባላት ተሳታፊ መሆናቸው በስፋት የተዘገበ ሲሆን፣ በትግራይ ውስጥ ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀሎችና ከባድ የመብት ጥሰቶችን በመፈጸም በዓለም አቀፍ የመብት ተቋማት ይከሰሳሉ።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር ኤርትራ አጠቃላዩን ሕዝቧን ወደ ሠራዊቷ እያስገባች አይደለም ሲሉ ያስተባብላሉ።

መሬት ላይ ያለው እውነታ ሆን ተብሎ እንዲዛባ እና እንዲጋነን ተደርጓል ያሉት ሚኒስትሩ፤ “የተወሰኑ የተጠባባቂ ኃይል አባላት የተጠሩ ቢሆንም ቁጥራቸው በጣም ጥቂት ነው” ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ግን በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የኤርትራ ጦር ተሳትፎ ሰላም ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል በማለት በቃል አቀባዩ በኩል ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ የኤርትራ ሠራዊት ሰሞኑን ድንበር አቋርጦ ወደ ትግራይ ክልል ስለመግባቱ አሜሪካ እንደምታውቅ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ማይክ ሐመር “የኤርትራ ጦር ከድንበር ማዶ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ስንከታተል ቆይተናል” ካሉ በኋላ ይህንኑ የኤርትራ እንቅስቃሴ አገራቸው እንደምታወግዝ ተናግረዋል። 

የአሜሪካ መንግሥት እና የአውሮፓ ኅብረት የኤርትራ ሠራዊት ዳግም ወደ ተቀሰቀሰው ጦርነት ተመልሰው መግባታቸውን በመጥቀስ ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወቃል።

የትግራይ ኃይሎች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሠራዊቶች ጥቃት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ሲገልጹ፣ ከሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት በኩል ግን እስካሁን የተባለ ነገር የለም።