ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፑቲን የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ውጤት አልባ እየሆነ ነው አሉ
የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ውጤት አልባ እየሆነ ነው አሉ።
ፕሬዝዳንቱ ለጦርነት ዘጋቢዎች ሲናገሩ ሩሲያ ላይ የተከፈተው ዘመቻ በዩክሬን ጦር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ነው ብለዋል።
ፑቲን ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ ዩክሬን 160 ታንኮች ሲወድሙባት ሩስያ ያጣችው 54 ታንኮችን ብቻ ነው ብለዋል።
ፑቲን ጨምረውም የዩክሬናውያን ወታደሮች እልቂት ከሩስያ ጋር ሲነጻጸር በ10 እጥፍ ይበልጣል ብለዋል።
ኪዬቭ “በየትኛውም ዘርፍ ውጤታማ አይደለችም” ብለዋል ፑቲን።
ይህ የፑቲን አስተያየት በገለልተኛ ወገን የተረጋገጠ አይደለም። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪም ከፑቲን የተለየ አስተያየት ሰጥተዋል።
“ወደፊት እየገሰገሰን ነው” ያሉት ዜሌንስኪ፤ የዩክሬንን አንድ ሰንዝር መሬት “ከሰይጣናዊው የሩስያ ኃይል ነጻ እያወጡ ላሉ ዩክሬናውያን ወታደሮች ምስገና ይድረስ” ብለዋል።
ዩክሬን በሩስያ ኃይሎች ላይ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ከፍቻለሁ ካለች በኋላ በዶኔስክ እና ዛፖሬዢያ ጥቂት መንደሮችን ነጻ ማውጣቷን አስታውቋለች።
ትናንት ማክሰኞ ቢቢሲ በምሥራቅ ዶኔስክ የዩክሬን ወታደሮች ከሩስያ ኃይል ነጻ ያወጡትን ሰፍራ መጎብኘት ችሏል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና አዛዥ ጄንስ ስቶለተንበርግ ገና በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ብንገኝም የሩስያ ወታደሮችን በማስወገድ ለውጦች እየመጡ ነው ብለዋል።
“በትክክል የምናውቀው ነገር ዩክሬናውያኑ ብዙ መሬት ነጻ አወጡ ማለት በድርድር ጠረጴዛው ላይ የበላይነት ይኖራቸዋል” ሲሉ ዋና አዛዡ ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዋይት ሃውስ በነበራቸው ስብሰባ ተናግረዋል።
ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን መልሶ ማጥቃት ዘመቻ በተመለከት የሰጡት አስተያየት በአሜሪካ ባለስልጣናትም ውድቅ ሆነዋል።
በስም ያልተጠቀሱ አንድ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን ሁኔታውን በተመለት ፑቲን የሰጡት አስተያየት ‘እውነት አይደለም’ ብለዋል።
ፑቲን በትናንቱ ንግግራቸው ዩክሬን በድንበር ዘለል ጥቃቶች ሩስያን ዒላማ ያደረገችባቸውን ጥቃቶች ለመመከት የጦር ኃላፊዎቻቸው የተሻለ ዝግጅት ማድረግ ይችሉ ነበር ሲሉ መከላከሉ ላይ ከፍተት መኖሩን አምነዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፑቲን ምንም እንኳ ከባለፈው ዓመት ወዲህ የጦር መሳሪያ ምርት ቢጨምረም ጦራቸው፤ “የተተኳሽ፣ የግንኙነት መሳሪያ፣ ድሮን እና የመሳሰሉት” እጥረት እንዳለበት አልካዱም።
ዜሌንስኪ ግን ሩስያ ላይ አሁንም ጠንካራ ማዕቀብ እንዲጣል በትናንትናው ንግግራቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዜሌንስኪ ሩስያ ከዩክሬን አጋር አገራት የሚላኩ የጦር መሳሪያ ግብዓቶችን በመጠቀም ሚሳኤል እያመረተች ነው በሚል ነው ተጨማሪ ማዕቀብ ሞስኮ ላይ እንዲጣል የጠየቁት።
በተመሳሳይ ቀን አሜሪካ 325 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር ድጋፍ ለዩክሬን አድርጋለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቤላሩስ መሪ አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አገራቸው ከሩስያ የኒውክለር ጦር መሳሪያ ድጋፍ ልትቀበል ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሄሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ ጥቅም ላይ ከዋሉት አቶሚክ ቦምቦች ሦስት እጥፍ ኃይለኛ የሆኑትን ኒውክለር መቀበሉ ቤላሩስ ወደፊት ከሚቃጣበት ጥቃት እራሷን መከላከል ያስችላታል ብለዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሩስያ ታክቲካለ የኑክለር ጦር መሳሪያዎችን ከሐምሌ ወር ጀምሮ በቤላሩስ ተክላለሁ ማለቷ ምዕራባውያንን ስጋት ውስጥ ከትቶ ነበር።