ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የብላክ ላይቭስ ማተር ተሟጋቹን ተኩሶ የገደለው የአሜሪካ ወታደር ይቅርታ ተደረገለት
የቴክሳሱ ገዥ ግሬግ አቦት ከአራት ዓመታት በፊት የብላክ ላይቭስ ማተር እንቀስቃሴ ተሟጋቹን በመግደል የተከሰሰውን ግለሰብ በይቅርታ ለቀቁት።
የቀድሞው የአሜሪካ ወታደር ሳጅን ዳንኤል ፔሪ በኦስቲን የኡበር ሹፌር ሆኖ ሲሠራ ነበር ሰልፈኞች ወደተሰበሰቡበት ጎዳና ያመራው።
ከተቃውሞ ሰልፈኞቹ አንዱ የሆነው ጋሬት ፎስተር ጠመንጃ ይዞ ወደ መኪናው ሲቀርብ፤ ፔሪ ተኩሶ ይገድለዋል።
ፔሪ እራሱን ለመከላከል ያደረገው መሆኑን ቢናገርም ፍርድ ቤት 25 ዓመት እስራት አስተላልፎበታል።
28 ዓመቱ የነበረው የቀድሞ የአሜሪካ አየር ኃይል መካኒክ ፎስተር፤ ህይወቱ ባለፈበት ወቅት ከፊል-አውቶማቲክ ኤኬ-47 ጠመንጃ ይዞ ነበር።
በቴክሳስ ሕግ ጠመንጃ ይዞ መንቀሳቀስ ይፈቀዳል። ፎስተር እና ፔሪ ነጮች ናቸው።
አሁን 37 ዓመት የሆነው ፔሪ በታክሲ ተሳፋሪ እንዳልነበረ እና በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ምክንያት በሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ የተሰበሰቡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች መኪናውን መምታት መጀመራቸውን ተናግሯል።
ተቃዋሚዎቹ ተሽከርካሪው እየገጨ ሊገድለን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በችሎቱ ወቅት የፔሪ ጠበቆች ፎስተር ጠመንጃውን እንዳነሳ ቢጠቅሱም፤ አንዳንድ ምስክሮች በፍጹም ሲሉ ተከራክረዋል። ፔሪ መስታወቱን ዝቅ አድርጎ ፎስተርን አምስት ጊዜ ከተኮሰበት በኋላ እየነዳ ቢያመልጥም በኋላ ላይ እርዳታ እንዲደርስ መደወሉ ታውቋል።
ጉዳዩ ወግ አጥባቂዎች ያሰባሰበ ሲሆን አገረ ገዥው አቦት ደግሞ ይፋዊ ጥያቄ እንደደረሳቸው ፔሪን ይቅርታ እንደሚያደርጉለት ተናግረው ነበር። ፔሪ በ 2023 ነው በግድያ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት።
ሪፐብሊካኑ ሀገረ ገዥ ሐሙስ ዕለት ይቅርታ መደረጉን ሲያበስሩ እንደተናገሩት ከሆነ የቴክሳስ የይቅርታ ቦርድ ስለ ጉዳዩ እና የፔሪ ግላዊ ታሪክ "በጥልቀት ግምግሟል።"
"ቴክሳስ በዳኞች ወይም በተራማጅ ጠበቃዎች ሊሻሩ የማይችሉ በጣም ጠንካራ የሆኑ ራስን መከላከል ህጎች አሏት" ሲል ገዥው አቦት በመግለጫቸው ዴሞክራቱን የትራቪስ ካውንቲ ዓቃቤ ህግ ሆሴ ጋርዛን በመጥቀስ ተናግረዋል።
አንድ ግለሰብ ግድያ ወይም ሌሎች ከባድ ወንጀሎች ሊፈጽምብኝ ነው ብሎ ካመነ ግድያን ጨምሮ ኃይልን እንዲጠቀም የሚፈቀድበት ‘ስታንድ ዩር ግራውንድ’ የሚባል ሕግ አለ።
ጋርዛ በሰጡት መግለጫ “ቦርዱ እና ገዥው ፖለቲካቸውን ከፍትህ በላይ አስቀምጠው ሕጋዊ ስርዓታችንን መሳለቂያ አድርገውታል። በራሳቸው ማፈር አለባቸው” ብለዋል።
የፍርድ ቤት ሰነዶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ፔሪ ከግድያው ከሳምንታት በፊት ጀምሮ የብላክ ላይቭስ ማተር እንስቃሴ ተሟጋቾችን ሲፈልግ እና ተሟጋቾቹንም “በእንስሳት መካነ አራዊት ውስጥ ከሚሯሯጡ የዝንጀሮዎች ስብስብ” ጋር በማነጻጸር ለጓደኞቹ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መልዕክት አስተላልፏል።
ፍሎይድ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “ዘራፊዎችን ለመግደል ወደ ዳላስ ልሄድ እችላለሁ” የሚል የጽሑፍ መልዕክትም ልኳል።
"ሙስሊሞችን ስለ ማደን" እና "ትንሽ ጥቁር ወንድ" ያፈቀረች ሴት ስለመግደልም ጨምሮ መልዕክት ልኳል።