ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባይደን ከ1962 ወዲህ ከፍተኛ የኒውክሌር ስጋት አንዣቧል አሉ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከእአአ 1962ቱ የኩባው የኒውክሌር ቀውስ በኋላ ከፍተኛ የኒውክሌር ስጋት ያየለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል አሉ።
ባይደን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ጦር ሜዳዎች ፈተና እየገጠማቸው መሆኑን ተከትሎ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መጠቀምን በተመለከተ ሲናገሩ “የቀልዳቸውን አይደለም” ብለዋል።
ፑቲን ከገቡበት ጦርነት ለመውጣት ምን እያሴሩ እንደሆነ አሜሪካ ለመረዳት ጥረት እያደረገች እንደሆነም ጆ ባይደን ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት የፑቲን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እጠቀማለሁ ዛቻ በአጽንኦት መታየት አለበት ብለው ነበር።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን፣ ባሳለፍነው ሳምንት ሩሲያ በየትኛው ጊዜ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ዝግጅት እያደረገች መሆኗን የሚያሳይ ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል።
ባይደን ደግሞ የፑቲን በዩክሬን ጦርነት የኒውክሌር፣ባዮሎጂካል ወይም የኬሚካል ጦር መሳሪያ የመጠቀም ሃሳብ ሲያነሱ “እየቀለዱ አይደለም” ብለዋል።
“ከኩባው የኒውክሌር ቀውስ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበት ስጋት ተደቅኖብናል” ብለዋል ፕሬዝዳንት ባይደን።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎደሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው የሞስኮን የኒውክሌር ጦር ማስፈራሪያ ከፕሮፖጋንዳ የዘለለ አይደለም ሲሉ አጣጥለውታል።
የኩባ ሚሳኤል ቀውስ ተብሎ የሚታወቀው ክስተት የወቅቱ የዓለማችን ኃያላንን ወደ ኒውክሌር ጦርነት እንዲገቡ ከጫፍ አድርሶ ነበር።
በወቅቱ ሶቪየት ኅብረት የኩባን ደኅንነት ከአሜሪካ ጥቃት ለመጠበቅ በሚል፣ ኩባ ውስጥ የአሜሪካ ከተሞችን መምታት በሚያስችሉ ስፍራዎች ላይ የኒውክሌር አረሮችን ማስወንጨፍ የሚችሉ ሚሳኤሎችን ተክላ ነበር።
ባይደን በአንድ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ሥነ-ስርዓት ላይ ለዴሞክራት ፓርቲ አባላቶቻቸው ባደረጉት ንግግር፤ የኒውክሌር፣ የባዮሎጂካል እና የኬሚካል ጦር መሳሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቁጥጥር ውጪ ሊያደርጉ ይችላሉ ብለዋል።
ለበርካታ ወራት የአሜሪካ ባለስልጣናት ሩሲያ በዩክሬን ጦር ሜዳዎች ላይ ፈተናዎች የሚገጥሟት ከሆነ ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያዎችን ለመጠቀም አማራጭ ልትወስድ ትችላለች ሲሉ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።
ቭላድሚር ፑቲንም በተመሳሳይ የሩሲያን ግዛት ለመጠበቅ ማድረግ የሚችሉትን በሙሉ እንደሚፈጽሙ ገልጸው ነበር።
ፑቲን የዩክሬን አካል የሆኑትን ሉሃንስክ፣ ዶኔስክ፣ ዛፖሪዢያ እና ክሄርሰን ግዛቶች ጠቅልለው የሞስኮ አካል መሆናቸውን ይፋ ቢያደርጉም፣ የዩክሬን ጦር በእነዚህ ግዛቶች ጭምር ወደፊት እየገፉ ነው።