ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ደቡብ አፍሪካ ከሩሲያ እና ከቻይና ጋራ ወታደራዊ ልምምድ ልታደርግ ነው
ደቡብ አፍሪካ በሚቀጥለው ወር ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር በመሆን ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ልትጀምር መሆኑን አስታወቀች።
የደቡብ አፍሪካ ጦር ሠራዊት ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በሚቀጥለው ወር በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ ከኃያላኒ አገራት ጋር ወታደራዊ ልምምድ ያደርጋል።
ወታደራዊ ልምምዱ የደቡብ አፍሪካ የወደብ ከተሞች በሆኑት ደርባን እና ሪቻርድስ ቤይ ለ10 ቀን እንደሚደረግ ተገልጿል።
የዚህ ወታደራዊ ልምምድ ዓላማ ለደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይል ወታደራዊ ክህሎትን እና እውቀትን ማካፈል ነው ተብሏል።
ደቡብ አፍሪካ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ድጋፍም ተቃውሞም ካላሰሙ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ናት።
ደቡብ አፍሪካ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና አባል በሆኑበት በምህጻረ ቃል ብሪክስ ተብሎ በሚጠራው የአገራት ስብስብ ውስጥ ሊቀመንበር ሆና እያገለገለች ትገኛለች።
ይህ ደቡብ አፍሪካ ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር የምታደርገው ወታደራዊ ልምምድ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበበት ጊዜ መሆኑ ትኩረትን ስቧል።
በአፍሪካ አህጉር በምጣኔ ሃብትም በተደማጭነትም ቀዳሚዋ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ፣ የሩሲያን ወረራ በማውገዝ የአፍሪካ አገራትን ከጎኗ እንድታሰልፍ በምዕራባውያን በኩል ፍላጎት ቢኖርም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
በተጨማሪም ከቀናት በኋላ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጉብኝት ለማድረግ እና ከአገሪቱ አቻቸው ጋር ለመወያየት በደቡብ አፍሪካ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተነግሯል።
ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር ወታደራዊ ልምምድ የሚያደርገው የአገሪቱን የምድር፣ የአየር እና የባሕር ኃይሎችን ያካተተው የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይል “ልምምዱ በሦስቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናክረዋል” ብሏል።
ደቡብ አፍሪካ ከሁለቱ አገራት ጋር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ስታደርግ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ለመጀመርያ ጊዜ ወታደራዊ ልምምድ ያካሄደችው በ2019 ኅዳር ወር ላይ በኬፕታውን ነበር።
በዚህ ዓመት የጋራ ወታደራዊ የጋራ ልምምድ ላይ 350 ከተለያየ የሠራዊት ክፍሏ የተውጣጡ ወታደሮቿ እንሚሳተፉ ይፋ አድርጋለች።