ዩኬ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜጎች ላይ የቪዛ ገደብ ጣለች

ዩናይትድ ኪንግደም የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት ሕገ ወጥ ስደተኞችን እና የውጭ አገር ጥፋተኞችን ለመቀበል ስምምነት ላይ ባለመድረሱ ወደ አገሪቱ በሚገቡ ዜጎች ላይ የቪዛ ገደብ ጣለች።

የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር አገሪቱ የጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ባለፈው ኅዳር ጠበቅ ያለ ማሻሻያ ካደረገ በኋላ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይህን ታሳቢ አድርጋ ማስተካከያ አላደረገችም ብሏል።

ከዚህ በኋላ ከአገሪቱ በአስቸኳይ የቪዛ ሂደት የሚያመለክቱ ሰዎች ቪዛ እንደማይሰጥ የጠቆመው ሚኒስቴሩ፤ በልዩ ሁኔታ ለሚያመለክቱ እና ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለሚመጡ ፖለቲከኞችም የተለየ አገልግሎት እንደማይሰጥም ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አንጎላ እና ናምቢያ የቪዛ እገዳ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ካወቁ በኋላ ዜጎቻቸውን ለመውሰድ ጥረታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል ብሏል።

መንግሥታዊ ምንጮች የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ሸባና ሞሐመድ ዜጎቻቸውን ለመቀበል አሻፈረኝ በሚሉ አገራት ላይ የቪዛ ማዕቀብ ለመጣል እንደማያቅማሙ አስምረው ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ እንዳለው አንጎላ እና ናምቢያ ጥረታቸውን ለማጠናከር ስምምነት ላይ መድረሳቸው የጥገኝነት ማሻሻያው የመጀመሪያውን ውጤታማ የመመለስ እንቅስቃሴ ተደርጎ ተወስዷል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የአንጎላ፣ ናምቢያ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንግግሥታት ሕገ ወጥ ስደተኞችን ለመመለስ ትብብራቸውን ከፍ ካላደረጉ ለአገራቱ ቪዛ መስጠት እንደሚያቆም ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች ስምምነቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያደርጋል ብለዋል።

የዩኬ የጥገኝነት ስርዓት ማሻሻያ የስደተኞችን ሁኔታ ጊዜያዊ እንዲሆን፣ ለጥገኛ ጠያቂዎች የሚቀርብ የመጠለያ ድጋፍ የተገደበ እና ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ደኅንነቱ የተጠበቀ የስደተኞች እንቅስቃሴን እንደሚፈጥር ይዘረዝራል።

ባለፈው ወር ማሻሻያውን ይፋ ያደረጉት ሚኒስትሯ ሸባና ሞሐመድ በመመለስ ፖሊሲው የማይተባበሩ አገራት ላይ የቪዛ እግድ እንደሚጣል አስጠንቅቀዋል።

መስሪያ ቤታቸው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አንጎላ እና ናምቢያ ስደተኞችን ለመቀበል ዳተኝነት ማሰየታቸው፤ ይህም ለስደተኞች የመቆየትን ምርጫ ሰጥቷል ብሏል።

ሚኒስቴሩ ሦስቱም አገራት በዳተኝነታቸው እና በመመለስ ሂደቱ እንቅፋት በመሆን ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስጠንቅቆ ነበር።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ "አገራት በሕግ እንዲመሩ እንጠብቃለን። አንድም ቢሆን ዜጎቻቸው እዚህ የመቆየት መብት ከሌላቸው መልሰው መውሰድ አለባቸው።

"አንጎላ እና ናምቢያ ለትብብራቸው አመሰግናለሁ። አሁን ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትክክለኛውን ነገር የማደረግ ጊዜው ነው። ዜጎቻችሁን መልሳችሁ ውሰዱ አሊያም ወደ አገር ውስጥ [ዩኬ] ለመግባት ያላችሁን ጥቅም ታጣላችሁ" ብለዋል።