ለካፒታል ወጪዎች የሚመደበው በጀት ድርሻ በአምስት ዓመታት ውስጥ በ11 በመቶ ቀነሰ

አዲስ አበባ ቀላል ባቡር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የካፒታል በጀት የፌደራል መንግሥት በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ እና በሌሎች ዘርፎች የሚያከናውናቸውን የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ወጪ ለመሸፈን የሚውል ነው።

ከአጠቃላይ የፌደራል መንግሥት በጀት ድርሻ ለካፒታል ወጪ የሚመደበው ገንዘብ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አምስት ዓመታት ውስጥ በ11 በመቶ ቀነሰ።

ባለፉት ሦስት ዓመታት መንግሥት "የትኩረት አቅጣጫው" ከአዳዲስ ፕሮጀክቶች ይልቅ "በመካሄድ ላይ ያሉ ነባር ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ማድረግ" ላይ ነበር።

የካፒታል በጀት የፌደራል መንግሥት በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ እና በሌሎች ዘርፎች የሚያከናውናቸውን የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ወጪ ለመሸፈን የሚውል ነው።

የፌደራል መንግሥት ለ2018 በጀት ዓመት ከመደበው 1.93 ትሪሊዮን ብር አጠቃላይ ዓመታዊ በጀት ውስጥ ለካፒታል ወጪ የተመደበው 415.2 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ ከአጠቃላይ በጀቱ በመቶኛ 21.6 ድርሻ አለው።

ይህ የበጀት ድርሻ የተጠቀሰው ቢቢሲ የተመለከተው እና ዛሬ ሰኔ 3/2017 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የበጀት ሰነድ ላይ ነው።

ከአጠቃላይ በጀቱ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ለመደበኛ ወጪዎች የተመደበው በጀት ሲሆን፣ ከአጠቃላይ በጀቱ 61.4 በመቶ ይሸፍናል።ለክልሎች ድጋፍ የተመደበው ከመደበኛ እና ካፒታል ወጪዎች ቀጥሎ ሦስተኛውን ድርሻ ይይዛል።

ከአንድ ወር በኋላ ለሚጀምረው በጀት ዓመት ከተመደበው 1.93 ትሪሊዮን ብር መካከል 416.8 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ይታያል።

በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የበጀት መግለጫ የ2018 በጀት " የተገደበ የበጀት ጉድለት እንዲኖረው ተደርጎ የተዘጋጀ" መሆኑን ጠቁሟል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ የበጀት ጉድለት ለመጪው ዓመት ከተያዘው የካፒታል ወጪ ጋር ተስተካካይ ነው።

ለመጪው በጀት ዓመት ከተመደበው የካፒታል በጀት ውስጥ 343 ቢሊዮን የሚሆነውን ለመሸፈን የታሰበው ከትሬዠሪና ከመሥሪያ ቤቶች የውስጥ ገቢ ነው። በተጨማሪም 46 ቢሊዮን ብር ከፕሮጀክት ዕርዳታ እንዲሁም 27 ቢሊዮን ብር ከፕሮጀክት ብድር ለመሸፈን ታቅዷል።

የበጀት መግለጫው "ለካፒታል የሚመደበው በጀት በዋነኛነት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ብቻ እንደሚሆን ግምት ውስጥ ገብቷል" ሲል አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደማይኖሩ ፍንጭ ሰጥቷል።

መግለጫው ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሰው "የልማት ትብብር መቀዛቀዝ" "ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ በሚመደበው በጀት ላይ ጫና ማሳደራቸውን" ነው።

መግለጫው "የልማት ትብብር መቀዛቀዝ በአንዳንድ የመንግሥት አገልግሎቶች ላይ ጫና እንዲፈጠር በማድረጉ ጫናው ወደ መንግሥት በጀት እየመጣ ይገኛል" ይላል።

ለዚህ በምሳሌነት ያነሳውም በጤናው ዘርፍ "የልማት አጋሮች" ድጋፍ መቀነስ፤ "በጤና አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ክፍተት እንዲፈጠር" ማድረጉን ነው።

ይህን ተከትሎም የነፍስ አድን የጤና ቁሳ ቁሶች (መድኃኒትን ጨምሮ) የግዥ ወጪ በተወሰነ ደረጃ በመንግሥት በጀት ተካቶ እንዲያዝ ተደርጓል።

ከጠቅላላ የካፒታል ወጪ ውስጥ 74.5 በመቶ የሚሆነው የተመደበው "ትኩረት ለተሰጣቸው" የሥራ ዘርፎች ነው።

ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው "ለዋና እና ለአገናኝ መንገዶች ግንባታ" እንዲሁም "ነባሮቹን ለማጠናከር እና ለማሻሻል" የተመደበው 93.6 ቢሊዮን ብር ነው።

ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነባር ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያን ጨምሮ "ለአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፖኬጅ" 44.5 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።

የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት 18.3 ቢሊዮን ብር ተደግፎ መቅረቡን የበጀት መግለጫው ላይ ሰፍሯል።

መንግሥት አዳዲስ ፕሮጀክቶች ያልተጀመሩት "እየታየ ያለው የልማት ትብብር መቀዛቀዝ አዝማሚያ" ነው ቢልም ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች በጀት አልተያዘም።

የ2016 ዓ.ም በጀት ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት በተደረገበት ወቅት ለአዳዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች ግንባታ በጀት አለመያዙ በአባላት ጥያቄ ተነስቶበት ነበር።

መንግሥት በወቅቱ የ2016 የትኩረት አቅጣጫው "በመካሄድ ላይ ላሉ ነባር ፕሮጀክቶች . . . እንዲጠናቀቁ ማድረግ" እና "በግጭቱ ምክንያት የወደሙ መሠረተ ልማቶች እና አገልግሎቶች ወደ ቀድሞው ይዞታቸው መመለስ" መሆኑን አስታውቆ ነበር።

የ2016 በጀት የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የጸደቀው የመጀመሪያው በጀት ነው።

በቀጣዩ በጸደቀው የ2017 ዓ.ም በተመሳሳይ ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ በጀት አልተመደበም ነበር። የመንግሥት ትኩረትም ተመሳሳይ ነበር።

ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች የሚመደበው ገንዘብ ከቆመ ሦስት ዓመት ቢሆንም ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ዓመታት የካፒታል ወጪ በሂደት እየቀነሰ ነው የመጣው።

በ2014 የካፒታል ወጪ ከአጠቃላይ የፌደራል መንግሥት በጀት አንጻር የነበረው ድርሻ 32.67 በመቶ ነበር። በበጀት ዓመቱ ተመድቦ ከነበረው ጠቅላላ በጀት 561.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ 183.5 ቢሊዮን የሚሆነው የተመደበው ለካፒታል ወጪ ነው።

በቀጣዩ የ2015 በጀት ዓመት የካፒታል ወጪ ከጠቅላላ የመንግሥት በጀት ያለው ድርሻ ወደ 28 በመቶ ዝቅ ብሏል። በጊዜው የመንግሥት ጠቅላላ ወጪ 786.61 ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የካፒታል ወጪ ድርሻ 218.11 ቢሊዮን ብር ነው።

ለ2016 ዓ.ም. ከተመደበው 801.5 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ በጀት ውስጥ 203.44 የሚሆነው ለካፒታል ወጪ የተደለደለ ነበር። ይህ ገንዘብ ከጠቅላላው በጀት ያለው ድርሻ 25 በመቶ ነው።

የካፒታል ወጪ እየተጠናቀቀ ባለው የ2017 በጀት ዓመትም ድርሻው ወደ 22.72 በመቶ አሽቆልቁሏል። በበጀት ዓመት ከተደለደለው 1.554 ትሪሊዮን ጠቅላላ በጀት ውስጥ ለካፒታል ወጪ የተመደበው 353.2 ቢሊዮን ብር ነው።

ለመጪው የበጀት ዓመት የተመደበው የካፒታል በጀት እንደ ባለፉት ዓመታት ሁሉ ቅናሽ አሳይቷል። ከ1.93 ትሪሊዮን ብር ጠቅላላ በጀት ውስጥ የካፒታል በጀት ድርሻ 415.2 ወይም 21.6 በመቶ ነው።

ይህ የካፒታል ወጪ ድርሻ ማነስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በአባላት ጥያቄ ቀርቦበታል። ዶ/ር ከፈና ኢፋ የተባሉ የምክር ቤት አባል "ሕብረተሰቡ ትልቁን ጥቅም የሚያገኘው ለካፒታል [ወጪ] ከሚመደበው የፕሮጀክቶች በጀት ነው። ይሄ ገንዘብ በጣም አላነሰም ወይ?" ሲሉ ጠይቀዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዮ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው "መንግሥት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ስም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መተግበር የሚያቆመው መቼ ነው?" የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

"ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች ማስጨርሻ ተብሎ የሚመደበው በጀትም በቂ አይደለም" ሲሉም አክለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በምላሻቸው ". . . በጣም ብዙ ሃብት ይፈልጋል። ከዚህ በላይ ቢመደብ ጥሩ ነበር፤ ነገር ግን የፊሲካል [በጀት] አቅማችን የሚፈቅደውን ያህል ከፍተኛውን ነው የያዝነው" ብለዋል።