ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤርትራ ኢጋድ "የተጣለበትን ኃላፊነት አልተወጣም" በሚል ከአባልነት ወጣች
የኤርትራ መንግሥት ራሱን ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባልነት ማስወጣቱን ባወጣው መግለጫ ይፋ አደረገ።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ዛሬ ታኅሣሥ 3/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ኤርትራ ከድርጅቱ ለመውጣት መወሰኗን ለኢጋድ ዋና ፀሐፊ በይፋ ማሳወቋን ገልጿል።
ኢጋድ ኤርትራ ከአባልነት መውጣቷን በይፋ ማሳወቋን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ተጨባጭ የሆኑ ተቋማዊ ወይም ፖሊሲ ለውጦች ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል ምክረ ሃሳብ ሳታቀርብ ለመውጣት መወሰኗ እንዳሳዘነው ገልጿል።
ለረጅም ዓመታት ከድርጅቱ ራሷን አግልላ የቆየችው ኤርትራ ወደ ኢጋድ የተመለሰችው ከሁለት ዓመት በፊት ነበረ።
ኤርትራ ከአባልነት ለመውጣት የወሰነችው ኢጋድ የተጣለበትን "ሕጋዊ ኃላፊነት አልተወጣም" በማለት መሆኑን በመግለጫው ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በተጨማሪም ለአባላቱ ምንም ተጨባጭ ስትራቴጂክ ጥቅም ያልሰጠ ድርጅት ነው በማለት ተችታዋለች።
ኢጋድ ቀጠናው መረጋጋት ላይ ድጋፍ ማድረግ ያልቻለ ድርጅት ነው በማለት የወቀሰችው ኤርትራ፣ በዚህ የተነሳ ራሷን ከአባልነት ለማስወጣት መወሰኗን አስታውቃለች።
ኤርትራ ከቀጣናዊ ድርጅቱ ኢጋድ ለመውጣቷ ጥቅል የሆነ ወቀሳ ከመሰንዘር ባሻገር በመግለጫዋ ላይ በይፋ ለውሳኔዋ ምክንያት የሆኑ ግልጽ ማሳያዎችን አልጠቀሰችም።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የተመሠረተው በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ በአካባቢው አጋጥሞ ለነበረው የአንበጣ ወረርሽኝ እና ድርቅ መፍትሔ ለመስጠት በሚል በተባበሩት መንግሥታት አነሳሽነት ነበር።
ዋና መቀመጫውን ጅቡቲ ያደረገውን ይህንን ድርጅት ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ኡጋንዳ የመሠረቱ ሲሆን ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን በኋላ ላይ ተቀላቅለዋል።
ከዚህ ቀደም ኤርትራ ራሷን ከድርጅቱ ካገለለች በኋላ ዳግም ወደ አባልነቷ የተመለሰችው ከ16 ዓመታት በኋላ ነበር።
የኤርትራ መንግሥት የዛሬውን ውሳኔ ተከትሎ የድርጅቱ አባላት ተመልሶ ሰባት ሆኗል።
የኤርትራ መንግሥት ከአባልነቱ መውጣቱን ባሳወቀበት መግለጫው ላይ ኢጋድ በአውሮፓውያኑ 1993 መልሶ ሲዋቀር ኤርትራ ወሳኝ ሚና መጫወቷን አስታውሷል።
ከዚያም በኋላ ከሌሎች አባል አገራት ጋር በመተባበር ለለውጡና ለውጤታማነቱ መሥራቷን ያስታወሰው መግለጫው፣ ይህም ለቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋት ዋና አንቀሳቃሽ ሆኖ እንዲያገለግል በማድረግ ለክልላዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደት መሠረት ጥሏል ብሏል።
የኤርትራ መንግሥት በድርጅቱ ላይ የተሰማውን ቅሬታ ሲገልጽ "እንደ አለመታደል ሆኖ፣ ከጊዜ በኋላ እና በተለይም ከአውሮፓውያኑ 2005 ጀምሮ፣ ኢጋድ የቀጠናውን ሕዝቦች ምኞት ማሳካት ብቻ ሳይሆን፣ በአባል አገራት ላይ በተለይም ኤርትራን ለመቃወም መሳሪያ በመሆን ጎጂ ሚና ተጫውቷል" ብሏል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነት ካደረገች በኋላ በሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን በሕገወጥ መንገድ ታስታጥቃለች በሚል ክስ ማዕቀብ በተጣለባት ጊዜ ኢጋድን ስትወቅስ ነበረ።
እነዚህ ያልተገባ ድርጊቶች ኤርትራ እአአ በሚያዚያ 2007 አባልነቷን እንድታቋርጥ ምክንያት መሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ለሃያ ዓመታት ያህል ከኢትዮጵያ ጋር የቆየችበት ፍጥጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ወደ ኢጋድ ተመልሳ የነበረ ሲሆን፣ ተጥሎባት የነበረው ማዕቀብ ተነስቶላት ነበር።
ኤርትራ እአአ በሰኔ 2023 ወደ ኢጋድ አባልነቷ ዳግም መመለሷን ያስታወሰው መግለጫው፣ ድርጅቱ ኤርትራ ተሃድሶ እንዲያደርግ ያቀረበችውን ጥሪ ተቀብሎ ያለፉትን "ተግባራቱን እንደሚያስተካክል" ተስፋ አድርጋ እንደነበርም ጠቅሷል።
"በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ኢጋድ ሕጋዊ ግዴታዎቹን እየተወ የራሱን አስፈላጊነት እና ሕጋዊ ግዴታውን ዝቅ እያደረገ ነው።"
በዚህም የተነሳ ኤርትራ በውጤቱም ሕጋዊ ግዴታውን በተወ እና ለአባላቱ ምንም ተጨባጭ ስትራቴጂክ ጥቅም ከማይሰጥ በቀጠናው መረጋጋት ላይ ድጋፍ ማድረግ ካልቻለ ድርጅት ራሷን ለማስወጣት ወስናለች ብሏል።
ቀጣናዊ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ አሁንም ለውይይት ክፍት መሆኑን በመግለጽ ሴክሬቴሪያቱ የኤርትራ መንግሥትን ቀርቦ እንደሚያነጋግር እና ከአባልነት ለመውጣት ያሳለፈውን ውሳኔ ዳግም እንዲያጤነው ጥሪ አቅርቧል።
ኢጋድ ለቀጠናዊ ትብብር፣ ውይይት እና ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ለመሥራት ቁርጠኛ ነኝ ሲል በመግለጫው ላይ አስታውቋል።
ይህ ቀጠናዊ ድርጅት የአካባቢው አገራት ትብብር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ መረጋጋትና የምጣኔ ኃብት እድገት እንዲገኝ የሚሠራ ነው።
ድርጅቱ የአሁኑን ስሙን የያዘው በአውሮፓውያኑ 1996 ሲሆን የተመሠረተውም በአውሮፓውያኑ 1986 በቀጠናው እየተፈጠረ ለነበረው ድርቅና ረሃብ ምላሽ ለመስጠት ነበር።
በአካባቢው በተደጋጋሚ ይከሰት የነበረው የከፋ ድርቅ ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ከፍተኛ ረሃብ ያስከተሉ ሲሆን የችግሩ መጠንና ስፋት ቀጣናዊ ትብብሮችን እንዲኖርም በማስፈለጉም ነው።
ኢጋድ በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት በፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲቆም በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
በአፍሪካ ካሉ ቀጣናዊ ድርጅት መካከል አንዱ የሆነው የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኡጋንዳን በአባልነት የያዘ ሲሆን ዋና መቀመጫው ጂቡቲ ውስጥ ነው።
የተቋሙ ዋነኛ ትኩረት በስምንቱ የአፍሪካ ቀንድ አበበቢ አባል አገራት ውስጥ ሰላም፣ ልማት እና ትስስርን ማጎልበት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ እና የምግብ ዋስትና ችግሮች በመቅረፍ ምጣኔ ሀብታዊ ትበብር ማምጣት ዓላማው ነው።
ኢጋድ በአውሮፓውያኑ 1996 የተመሠረተውን በድርቅ እና በአንበጣ መከላከል ዙሪያ የተቋቋመውን ድርጅት በመተካት እና ዓላማውን በማስፋት በአፍሪካ ካሉ ቀጣናዊ ድርጅቶች መካከል አንዱ ለመሆን ችሏል።
በአሁኑ ወቅት ኢጋድን በዋና ፀሐፊነት እየመሩ ያሉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ናቸው።