ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እየተጠናከረ ያለው የኢጋድ አስፈላጊነት እና ኢትዮጵያ በድርጅቱ ላይ ያላት ተጽእኖ
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ በአካባቢው አጋጥሞ ለነበረው የአንበጣ ወረርሽኝ እና ድርቅ መፍትሔ ለመስጠት በሚል በተባበሩት መንግሥታት አነሳሽነት ነበር የተጠነሰሰው።
ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት አብቅቶ የ’ግሎባላይዜሽን’ ጉዳይ ወደፊት መምጣት ሲጀምር፣ በአፍሪካ አገራትም ኢኮኖሚያዊ ትብብር ትልቅ አጀንዳ ለመሆን በቃ።
የተለያዩ አፍሪካ ቀጠናዎችም የሚያስተሳስራቸውን የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር ጀመሩ።
ዘግይቶም ቢሆን የአፍሪካ ቀንድ ተመሳሳይ መንገድ ተከተለ። ዋና መቀመጫውን ጅቡቲ በማድረግ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት እና የድርቅ መከላከል ድርጅት ተቋቋመ።
አሁን ላይ ስምንት አባል አገራት ያሉት ድርጅት የመጀመሪያ አላማው የአካባቢው አገራትን በተደጋጋሚ የሚያጠቃውን ድርቅ በጋራ መከላከል እና የጋራ ስትራቴጂ እየነደፉ ለልማት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ነበር።
ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ ሱዳን እና ኡጋንዳ መሥራች አገራት ሲሆኑ፣ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን በኋላ ላይ ተቀላቅለዋል።
ይህ ቀጠናዊ ድርጅት ከ10 ዓመት በኋላ በ1996 (እአአ) ዓላማውን እና ግቡን አስፍቶ ድጋሚ በአዲስ ማሻሻያ ብቅ አለ። ምንም እንኳን ድርቅ ከአካባቢው አገራት ውስጥ ባይጠፋም፣ ድርቅ የሚለውን ቅጥያ በማስወገድ የአሁኑን ስም ለመያዝ በቃ።
“ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች እየተቀያየሩ በመጡበት ወቅት፣ እነዚህ የአፍሪካ ቀንድ አገራትም ለሚመጣው ዕድል እና ፈተና ለመዘጋጀት በማሰብ በአዲስ መልኩ ኅብረቱን ለማጠናከርና ሰፊ ተልዕኮ ለመስጠት ችለዋል። በዚህም መሠረት በ1996 የሠላም እና ፀጥታ፣ የኢኮኖሚ መተባበር እና አንድነትን አጠቃሎ ሥራውን ቀጠለ” በማለት በደቡባዊ አፍሪካ ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት (ሳዴክ) የሰላም፣ የፀጥታ እና የመልካም አስተዳደር አማካሪ የሆኑት አዳነ ገብረመስቀል (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ቀጠናዊ ኅብረቱ በተደራጀ መልኩ ሥራውን ወደ ተግባር ሊለወጥ በተዘጋጀበት ወቅት ነበር የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት የፈነዳው። ይህም በአባላት መካከል የመከፋፈል ሁኔታ መፍጠሩን የሚያስታውሱት ዶ/ር አዳነ፤ በዓላማው እና በዕቅዶቹ አፈጻጸም፣ በተለይም የፖለቲካ ተልዕኮዎቹ እንደታሰበው ስኬታማ ነበር ማለት እንደማይቻል ያስረዳሉ።
ኢጋድ እና ስኬቶቹ
ኢጋድ ከግቡ አንጻር አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር አዳነ ቀጠናዊ ኅብረቱ ከተቋቋመ ጀምሮ ያሳካቸው ዓበይት ውጤቶች እንዳሉ ግን ያምናሉ።
“በድርቅ፣ በሜቲዮሮሎጂ እና የአካባቢ አየር ጥበቃ ጉዳይ ላይ ውጤታማ ሥራዎችን ሠርቷል። ዕውቀት በማስፋት ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ኃይል አቅም እንዲጠናከር ሥልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም በአገራቱ መካከል መተባበር እንዲኖር ሲሠራ ቆይቷል። በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን መካከል ተፈጥሮ የነበረው ጦርነትን በማስቆም ላይ መሪ ተዋናይ የነበረው ኢጋድ ነው” ይላሉ።
ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም መምህር ናቸው።
እሳቸውም የኢጋድ ጉዞ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ይጠቅሳሉ።
በአሁኑ ጊዜ እንደ አካባቢው የኢኮኖሚ ቀጠናዊ ኃይል ጥሩ ነገር እየሠራ ይገኛል በማለት ገልጸው “ከአልሻባብ እና ከመሰል የሽብር ቡድኖች ጋር በተያያዘ ድንበር ዘለል ጥቃቶችን በመከላከል ዙሪያ የሚሰራውን ሥራ የሚያስመሰግነው ነው” ብለዋል።
የኢጋድ አባል አገራት በውስጣዊም ሆነ በውጫዊ ጦርነት ይታወቃሉ። ብዙዎች የአካባቢው አገራት ዜጎችም ከቀጠናው በመነሳት ለስደት ሲዳረጉ ይታያሉ።
“ከዚህ አንጻር አሁን ባለበት አውድ ጦርነቶችን ለማስቆም የሚያደርጋቸውን ሥራዎች፤ ልማትን በተለይ ለወጣቶች ተስፋ ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት ትልቅ” መሆኑን ያነሳሉ።
ኢጋድ እና ድክመቶቹ
አዳነ (ዶ/ር) ኢጋድን ከሌሎች የአፍሪካ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ጋር በማነፃፀር ሲያስቀምጡት “ብዙ መራመድ ያልቻለ” ሲሉ ነው የሚገልፁት።
“በደቡባዊ አፍሪካ ከሚገኘው የደቡባዊ አፍሪካ ልማት ትብብር ኮንፈረንስ (ሳዴክ)፣ የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኤኮዋስ) እንዲሁም ከምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ጋር ካነፃፀርነው ብዙ ልዩነት እናይበታለን” በማለት አስረግጠው ይናገራሉ።
ምክንያት ያሉትም “ዋነኛው ጉዳይ በአገራቱ መካከል እንዲኖር የሚፈለገው ጠንካራ የሆነ መተባበር አለመቆየቱ ነው። በአባል አገራት መካከል በቀላሉ ግጭቶች እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል። የኢኮኖሚ ትስስሩ ጠንካራ ባለመሆኑ ወደ ግጭት መግባት ለአገራቱ ቀላል ነው የሚሆነው።”
ዶ/ር ዮናስም ኢጋድን የሚያነጻጽሩት ከምዕራብ አፍሪካው ኤኮዋስ ጋር ነው። በቀጠናው በኃይል ሥልጣን የያዙ ቡድኖችን ከሥልጣን እስከማውረድ መድረሳቸውን፣ በአንድ ፓስፖርት ከመጠቀም ባለፈ በልማት መተሳሰራቸውን አንስተው “ኢጋድ ብዙ ይቀረዋል” ይላሉ።
የአካባቢው አገራት ባለባቸው በርካታ መዋቅራዊ ችግሮች ምክንያት “እርስ በእርስ መጠራጠር አላቆሙም” በማለት ተቋሙ እንደሚጠበቀቀው አለመራመዱን ይጠቅሳሉ።
“እንደ ሶማሊያ ያሉ ደካማ መንግሥታት በአካባቢው በመኖራቸው እንደ አልሻባብ እና አይኤስ ያሉ ቡድኖች ድንበር ዘለል ጥቃት እና ሽብር እንዲፈጽሙ መንገድ ስለሚከፍት (ኢጋድ) እነዚህን ገና ለመቋቋም አቅም አልገነባም” ብለዋል።
ተቋማዊ የሆነ እና ቀደም ሲል የወረሳቸው ችግሮች ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ብዙ ላለመጓዙም አንድ ምክንያት እንደሆነ ዶ/ር ዮናስ ያነሳሉ።
ኢጋድ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖዎችም አሉበት።
በአካባቢው እንደ ጂቡቲ ያሉ አገራት የበርካታ ሃገራትን የጦር ሠፈሮች መያዛቸውን በማንሳት የዜጎቻቸውን አጀንዳ ወደ ጎን በመተው “የእነሱን አጀንዳ ለማስፈጸም ነው ኢጋድን የሚጠቀሙት” ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ኢጋድ
ኢጋድን ከማቋቋም አሁን እስካለበት እንዲደርስ የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። በአንፃሩ ደግሞ የበላይነቱን ወስዳ ተቋሙን ተጠቅማበታለች የሚል ትችትንም የሚያነሱ አሉ።
የሳዴክ የሠላም፣ የፀጥታ እና የመልካም አስተዳደር አማካሪ የሆኑት አዳነም (ዶ/ር) በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ።
“በመሠረቱ እንደዚህ ዓይነት የበላይነትን ወስዶ መምራት በሁሉም ቀጠናዊ ትብብሮች የሚታይ ነው። በኢጋድ ብቻ የሚታይ አይደለም። ደቡብ አፍሪካ ሳዴክ ውስጥ ትልቅ ሚና አላት። የምዕራብ አፍሪካዊውን ኤኮዋስን ካየነው ናይጄሪያ የበላይነትን ትወስዳለች” ሲሉ ያስረዳሉ።
የአገራቱ የኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ የሕዝብ ብዛት እና ያላቸው የቆዳ ስፋት በማኅበራቱ ውስጥ ለሚኖራቸው የበላይነት በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። ሌላው ደግሞ እነዚህ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች በጥቂት አገራት ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ የውጭ ኃይሎች ካላቸው ፍላጎትም እንደሚመነጭ ይናገራሉ።
“እንደ አሜሪካ፣ ቻይና እና ሌሎች አገራት አካባቢያዊ ጫና መፍጠር ሲፈልጉ ወደ ትንንሽ አገራት አይደለም የሚሄዱት። ብዙ ነገር ሊያስገኙላቸው እንዲሁም ጫና መፍጠር በሚችሉ አገራት በኩል ነው ፍላጎታቸውን ማስፈፀም የሚፈልጉት። ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያ በኢጋድ ላይ ጫና ማሳደሯ የሚጠበቅ ነው” ይላሉ።
አክለውም “ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በኢጋድ ላይ “ከልክ ያለፈ” ጫና መፍጠሯ እና የበላይነት መያዟ ለጥምረቱ ጠቀመው ወይስ ጎዳው? ዓላማዎቹን እንዲያሳካ ረድቶታል ወይ? ከሚለው አንፃር ከገመገምነው እንደ ድክመት ያነሳናቸው ጉዳዮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል” ሲሉ ዶ/ር አዳነ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ይህንን በምሳሌ ሲያስደግፉ “የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በተነሳበት ወቅት ኢትዮጵያ በተቋሙ ላይ የነበራትን የበላይነት ተጠቅማበታለች። የዲፕሎማሲ ብልጫ ወስዳበታለች። ኤርትራ ግን የመነጠል ስሜት ነው የተሰማት። ከዚህ የመነጠል ስሜት የተነሳም በቀጠናዊ ትስስሩ ስር ሆና ወደ ድርድር መምጣት እንደማትችል እና ጥቅም እንደማይኖረው በመገንዘብ ልትወጣ ችላለች” ብለዋል።
ኬንያ እና ኡጋንዳ ከኢጋድ በተጨማሪ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባላት መሆናቸውን የሚያነሱት አዳነ (ዶ/ር)፣ ሁለቱም አገራት ግን ለምሥራቅ አፍሪካው የትብብር መድረክ ቅድሚያ ስለሚሰጡ በኢጋድ ውስጥ የበላይነት የመውሰድ ፍላጎት ሳይኖራቸው በመቅረቱ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላት ይገልፃሉ።
ኢትዮጵያ በኢጋድ ውስጥ ትልቅ ሚና እንደነበራት ዶ/ር ዮናስም ይስማማሉ።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር እና በሠላም ለመኖር የተጠቀመችበት የውጭ ፖሊሲ ደግሞ ለዚህ ትልቁን አስተዋጽኦ ማድረጉን ያክላሉ።
ኢትዮጵያ ለዓመታት በኢጋድ ውስጥ አመራርነት ሚና ስለነበራት ልዩነቶች እስከመፈጠር ደርሰው እንደነበርም አስታውሰዋል።
“አሁንም ግን ኢትዮጵያ ኢጋድ ውስጥ ጥሩ ድምጽ አላት ብዬ አስባለሁ። የኢጋድ አደረጃጀት በየአባል አገራቱ ውስጥ እየሠራ መሆኑን አውቃለሁ። በተለይም በደኅንነት እና በልማት ዙሪያ እየሠሩ ነው። በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና አዎንታዊ እና ለሌሎችም የሚተርፍ ሆኖ ነው ያገኘሁት” ብለዋል።
በኢትዮጵያዊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የሚመራው ኢጋድ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በሠላም እንዲጠናቀቅ ከፕሪቶሪያ እስከ ናይሮቢ ቁልፍ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።
ኢጋድ እና ኤርትራ
“የሠላም ፉንጋ፣ የጦርነት ቆንጆ የለውም” የሚሉት ዶ/ር ዮናስ ከጎረቤት አገራት ጋር በሠላም መኖር አንዱ የሠላም መለኪያ መሆኑን ያነሳሉ።
አሁን ኤርትራ ከ16 ዓመታት በኋላ ወደ መድረኩ ተመልሳለች።
“ኤርትራ ወደ ኢጋድ መመለሷ አፍሪካዊ ማንነት ለማሳየት አዎንታዊ ሚና አለው። ለማደገም ከሌሎች አገራት ጋር መተባበር የግድ ይላል። በዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን በንግዱ እና በሌሎች ዘርፎች ከሌሎች ጋር መሥራት ለውስጣዊ ሠላሟ ሙሉ ዋስትና እንኳን ባይሆን የሚያረጋጋ፤ ለወደፊትም ተስፋ የሚሆን ነው ብዬ አስባለሁ።
“ሁለተኛ ለአስተዳደሩ ከጎረቤቶች ጋር አብሮ መኖር ትልቅ ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነው። አብሮ ተቻችሎ መኖር፣ አብሮ ማደግ ፖለቲካዊ ማቹሪቲ (ዕድገት) ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ለኤርትራ ጠቃሚ መሆኑን ዮናስ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ይቅር እና ኤርትራ ሌሎች ትልልቅ አገራትም ቢሆኑ ተነጥለው የሚያደርጉት ነገር የለም። አፍሪካ ቀንድን ከተመለከትን የድርቅ፣ የፀጥታ እና ሌሎች ችግሮች በዋነኝነት ደግሞ ድህነትን ለመቅረፍ ጥምረት፣ ውህደት እና መተባበር አስፈላጊ ነው። ኤርትራም ከዚህ ብዙ መጠቀም ትችላልች” በማለት በቀጠናው የሚካሄድ ማንኛውም የለውጥ እንቅስቃሴ ለአገሪቱ የሚበጅ እንጂ የሚጎዳ እንደማይሆን ዶ/ር አዳነ ያስቀምጣሉ።
ሰለሆነም ወደ ቀጠናዊ ኅብረቱ መመለሷ “ወደ ቤተሰብ እንደ መመለስ” ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ እና ለሌሎች አባል አገራት ከሚኖረው ጥቅም አንፃር ሲመዘንም መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ዶክተሩ ያምናሉ።
“ለምን አሁን ልትመለስ ቻለች?” የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ መሆኑ በማንሳትም፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአካባቢው ብዙ ለውጥ መታየቱ እንደ ምክንያት በመጥቀስ “አንደኛው በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ ፖለቲካዊ ለውጥ ያስከተለው ቀውስ ብቻ ሳይሆን ዕድሎችም ስላሉ ነው” ብለዋል።
በዓለም አቀፋዊ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎቶች፤ በተለይም በዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ጎራዎችን መፍጠራቸው እና የቻይና ጂኦ-ስትራቴጂክ ፍላጎት እየሰፋ መምጣት የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ተፈላጊ እንዲሆን ማድረጉንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የቆየ ውጥረት መፈታቱ አገሪቱ ወደ አባልነት እንድትመለስ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን እንደ ዋና ምክንያት በማስቀመጥ “በቅርቡ ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር እያጠናከረች ያለችውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብቻዋን ማስቀጠል እንደማትችል በመገንዘቧ ነው ወደ ቀጠናው ኅብረት ለመመለስ የፈለገችው” ይላሉ።
አክለውም “የቀይ ባሕር ዕድሎችን እና የጂኦ-ስትራቴጂ ሽሚያዎችን ኤርትራ መጠቀም ከፈለገች ብቻዋን ተነጥላ ማስፈጸም አትችልም። ከሌሎች ሃገራት ጋር በመወሃድ የሚፈፀም ነው የሚሆነው። አዲሱ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ በአዲስ መልክ ከያዙት ፍላጎት እና አቅጣጫም የሚነሳ ሊሆን ይችላል የኤርትራ ወደ ኢጋድ መመለስ” ሲሉ ያብራራሉ - ዶ/ር ዮናስ።
እንደ ኤኮዋስ ሁሉ በኢጋድ አገራት በሙሉ አንድ ፓስፖርት ቢኖር፤ ቀስ በቀስ ደግሞ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የፀጥታ እና የደኅንነት አንድነት ቢፈጠር በአካባቢው አገራት ውስጥ የተንሰራፋውን ድህነት መቅረፍ እንደሚቻል ያምናሉ።
“ከአየርን ንብረት ለውጥ ጋር ያሉ ችግሮችን መቅረፍ የምንችለው ስንተባበር በመሆኑ፣ መተባበሩ ለሁላችንም ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።