ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሩሲያ እና በቻይና ያደረጉት ጉብኝት አንደምታ
ብዙም ለጉብኝት ከአገር ሲወጡ የማይስተዋሉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ከሰሞኑ ወደ ቻይና እና ሩሲያ ጉብኝት አድርገዋል።
ቤይጂንግ እና እና ሞስኮ የደረሱት በጥቂት ቀናት ልዩነት ውስጥ ነው።
ፕሬዝዳንቱን አጅበው የአገሪቷ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም አብረዋቸው ታድመዋል።
በሁለቱም አገራት የአራት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ ሞቅ ያለ አቀባበል ጠብቋቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በቻይና እና በሩሲያ ካደረጉት ጉብኝት ቀደም ብሎ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአሥመራ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ነበር።
ከወራት በፊት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ እና የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ኤርትራን ጎብኝተው፣ ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።
ለመሆኑ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ የቤይጂንግ እና የሞስኮ ጉብኝት አንድምታ ምን ይሆን?
ኤርትራ እና ጉብኝቱ
ወደ ቻይና እና ሩሲያ ያደረጉት ጉብኝት በዲፕሎማሲ ዐይን ሲታይ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ትልቅ ድል መሆኑን የፖለቲካ ተንታኙ አብዱራህማን ሰይድ አቡ ሓሽም ይናገራሉ።
“በቻይናም፣ በሩሲያም ጥሩ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ጥሩ ዕውቅናም ተሰጥቷቸዋል” ይላሉ።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባለፉት 20 ዓመታት በዲፕሎማሲ ከዓለም ተገልለው ከመኖር ባለፈ በአካባቢው እንደ ችግር ፈጣሪ ኃይል ይወሰዱ እንደነበር ያነሳሉ።
ከዚህ ዓለም አቀፍ መገለል የመውጣት ሥራው በአፍሪካ ቀንድ ነው ተጀምሮ፣ ከኬንያ፣ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች አገራት ጋር ጥሩ ስምምነትን ፈጥረዋል።
ከዚህ አስቀጥለው ነው ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ የሚገኙት ሲሉ አቡ ሓሽም ይገልጻሉ።
ሌላኛው የጉብኙቱ ዓላማ ስትራቴጂክ ሊባል ይችላል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ዓለም እየተቀያየር መሆኑን እያዩት መሆናቸውንም ተንታኙ ያነሳሉ።
በፊት አሜሪካ ብቻዋን ወይንም ከኔቶ ጋር ዓለምን ሲቆጣጠሩ እንደነበር አንስተው፣ አሁን ይህ ተቀይሮ ወደ ‘መለቲ ፖላር’ (በርካታ አገራት ወይንም ቡድኖች የሚመሩት) ዓለም እየተፈጠረ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
“በዓለም ደረጃ ቻይና እና ሩሲያ የአሜሪካ ተቀናቃኝ ሆነው ሊመጡ ነው። በዚህም [ፕሬዝዳንቱ] ወደ ቻይና እና ሩሲያን እንዳደሉም የሚያሳይ ነው” ይላሉ።
ይህ ጉብኝት ታዲያ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ለአገራቸው ኤርትራ ብቻ ሳይሆን፣ ለሞስኮ እና ለቤይጂንግም ጠቃሚነቱ የጎላ ነው።
“በአካባቢው በተለይም ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር አካባቢ አንድ ታማኝ የሆነ የተረጋጋ አገር ይዘው እንደመግቢያ ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ።”
“በተለይም ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን በአሁኑ ጊዜ የእርስ በእርስ ግጭት ላይ ናቸው። ስለዚህ ሁኔታቸው የተረጋጋ አይደለም። በሌላ በኩል ኤርትራ ደግሞ አንድ መሪ አገሪቷን በሙሉ ተቆጣጥሮ ብዙም ተቀናቃኝ የሌለው አገር ሆኖ ነው የሚቀርበው። ከዚህ አንጻር ሲታይ ለእነሱ ጠቀሜታ አለው” ይላሉ።
ኤርትራ ከሁለቱ አገራት ጋር የፈጠረችው ግንኙነት ስትራቴጂክ (ስልታዊ) የሚሆንበትን ዕድል ቢያነሱም፣ ነገር ግን ይህ የማይሆንበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል አቡ ሓሽም ሳይጠቅሱ አያልፉም።
ለፖለቲካ ተንታኙ ይህ አይነቱ ግንኙነት ዘላቂ ሊሆን አይችልም። ኤርትራ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ የምትመራ እንጂ በሕገ መንግሥት እና በሕገ መንግሥታዊ ተቋሞች የምትተደዳር አለመሆኗን በምክንያትነት ያነሳሉ።
ግንኙነቱ በግለሰብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አንስተው “እሱ ከሌለ ግን ግንኙነቱ እንደሚቀጥል ዋስትና የለም” ይላሉ።
በአማካሪዎች የታገዘ እና ፖሊሲ አጥንቶም የተሻለውን አቅጣጫ የሚጠቁም ተቋም በአገሪቱ አለመኖሩንም እንደ ችግር ያነሳሉ።
“ነገ ፕሬዝዳንት ባይደን ወደ ዋሽንግተን ከጠሯቸው እና ጥሩ አማራጭ ያለው ኢንሴንቲቭ እስከሰጧቸው ሊገለበጡ ይችላሉ። ከዚህ አንጻር ሲታይ ግንኙነቱ ብዙም ዋስትና የለውም” ብለዋል።
ጉብኝቱን ሲመለከቱ ደጋግመው የሚሉት ግን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ “ትልቅ የዲፕሎማሲ እና የፐብሊክ ሪሌሽንስ (የሕዝብ ግንኙነት) ድል ነው። በዚህም ተቀባይነት አግኝቻለሁ፤ ዕውቅና አግኝቻለሁ ማለት የሚችሉበት ነው” ይላሉ።
የምሥራቁ ኃያላን ከኤርትራ ምን ይሻሉ?
በመቱ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት እና የሦስተኛ ዲግሪ ጥናታቸውን የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት እና በአፍሪቃ ቀንድ ላይ እየሰሩ የሚገኙት ነገራ ጉደታ፣ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።
ሦስቱ አገራት ከምዕራባዊያን ጋር ያላቸውን የሻከረ ግንኙነት የሚያነሱት ነገራ፣ ትስስራቸው መልከ ብዙ መሆኑን ይናገራሉ።
ዲፕሎማሲ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ዋነኛው ነው። ኤርትራ ወደ ኋላ የቀረውን መሠረተ ልማቷን ለማሳደግ የቻይና ድጋፍ ያስፈልጋታል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል ከምዕራባዊያን የሚመጣባትን ጫና እና ማዕቀብን ለመመከት ሞስኮ እና ቤይጂንግ አቅም እንዳላቸው ይጠቅሳሉ።
አክለውም ማዕቀብ በኤርትራ ላይ ሊጣል ቢል “ሁለቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ይጠቀሙበታል።”
ባለፉት ዓመታት በሩሲያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀረበውን ሩሲያን የሚያወግዝ የውሳኔ ሃሳብ ከተቃወሙት ጥቂት አገራት መካከል ኤርትራ አንዷ ናት።
‘በጦር መሣሪያ ዲፕሎማሲ’ ከታየም “ሩሲያ ለኤርትራ የጦር መሳሪያ ልትሸጥ ትችላለች” በማለት፣ ከሁሉም የሚልቀው እና ሦስቱን አገራቱን ሊያስተሳስር የሚችለው የጦር ሠፈር ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ።
ኤርትራ ዓለም አቀፍ ንግድ በሚሳለጥበት የቀይ ባሕር ዐይን ቦታ ላይ መገኘቷ ደግሞ ለዚህ ቀዳሚ ምክንያታቸው ነው።
አካባቢው በርካታ መርከቦች የሚመላለሱበት የዓለም ቁልፍ የንግድ መስመር ነው።
በዚህ ቀጠና የጦር ሠፈር ያላቸው ምዕራባዊያን አገራትም በርካታ ናቸው።
ይህ ጉብኝትም በዚህ በኩል ለቻይና እና ለሩሲያ ዕድል ለመሰጠት ያለመ ሊሆን እንደሚችል ነገራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኤርትራ ባላት ረጅም የባሕር ዳርቻ በአንዱ ላይ “[ሩሲያ እና ቻይና] የጦር ሰፈር እንዲያቋቁሙ ቦታ መስጠት ወይም ማከራየት ትችላለች” ብለዋል።
ምሥራቅ አፍሪቃ እና ጉብኝቱ
እንደ ነገራ ከሆነ ኤርትራ ካላት ሕዝብ ቁጥር እና ኢኮኖሚ ማነስ በተቃራኒ በአፍሪካ ቀንድ ተጽዕኖዋ የጎላ ነው።
ኤርትራ ቀደም ሲል ከኢራን እና ከኳታር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራት አንስተው “በኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በኮንጎም ጉዳይም ተጽዕኖ ስታሳድር ነበር” ብለዋል።
የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮችን ከማሠልጠን ባለፈ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መሳተፏንም በመጥቀስ በአካባቢው ውስጥ ያላት ሚና ያስታውሳሉ።
ይህም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደፊት በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ይዘው መዝለቅ እንደሚፈልጉም አመላካች ነው ይላሉ።
“እንደቀጠናው አንጋፋ መሪነታቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አገራቸው በአካባቢው ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን አለባት ይላሉ። በአፍሪካ ቀንድ ያላቸውን ልምድም መጠቀም ይፈልጋሉ” ሲሉ ነገራ ያክላሉ።
የአፍሪካ ቀንድ አገራት በተለያየ ጎራ ያሉ አገራትን መደገፍ ከቀጠሉ የቀዝቃዛው ጦርነት ታሪክ ሊደገም ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ የተቀሰቀሰው የቀዝቃዛው ጦርነት ፍጥጫ አሜሪካ እና ሶቪየት ኅብረት በእጅ አዙር ሲፎካከሩ እና ሲፋለሙ ቆይተዋል።
ሁለቱ ኃያላን ፊት ለፊት ቃታ ባልተሳበበት ወታደራዊ ትግል ውስጥ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ አጋሮቻቸውን በመደገፍ ከኋላ በመሆን ተሰልፈው ነበር።
በዚህ ሂደት በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች መካሄዳቸውን አቡ ሓሽም ያስታውሳሉ።
ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜም “[ሩሲያ እና አሜሪካ] የየራሳቸውን ደጋፊ አገራትን በመደገፍ እነሱን ሲያጋጩ ነበር። እንደሱ አይነት ሁኔታ ሊመለስ ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
ዓለምም ከሁለት ኃያላን የበላይነት ወደ በርካታ አገራት የበላይነት እየገባች መሆኑን ደግመው በማንሳትም ከዚህ ባለፈ መልኩም “መልቲ ፖላር [ብዙ ኃያላን የሚሳተፉበት] ብቻ ሳይሆን መልቲ ሌየርም [ድርብርብ] ነው” በማለት ከቀደመው የተወሳሰበ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
“የዓለምን አስተዳደር የሚዘውሩት ከሦስት እና አራት አገራት በላይ ሲሆኑ፣ አነስተኛ ሚና ያላቸው እንደ ሕንድ፣ ብራዚል፣ ቱርክ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኢራን ያሉትም ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉ ያስረዳሉ።
የተለያዩ አገራት ተጠናክሮ መውጣት እና በአፍሪካ ቀንድ ያላቸው ፍላጎት መጨመር፣ የቀዝቃዛው ጦርነት አይነት ፍጥጫ ሊያስከትል መቻሉ “ትንሽ ጠለቅ ያለ ትንታኔ ያስፈልገው ይሆናል። ፍላጎቶች ሲጋጩ ግን የአፍሪካ ቀንድ መሬት ላይ ሊንጸባረቅ ይችላል” ብለዋል።
ይህም አገራቱ የጦር መሣሪያ ገዢ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ፣ የአዳዲስ መሣሪያዎችም መሞከሪያ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ሊኖር የሚችለውን ሁኔታ ያስቀምጣሉ።
በዚህም ሳቢያ “ያላቸው ትንሽ ሃብት ወደዚያ ስለሚውል ለሕዝቦቻቸው ምንም ጥቅም አይኖረውም” ሲሉ ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ እና ጉብኝቱ
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ቤይጂንግ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ሞስኮ ያደረጉት ጉብኝት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ግንኙነት ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖን በተመለከተ በርካቶች ጥያቄ ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላለፉት ዓመታት የነበራቸውን አለመግባባት ወደ ጎን አድርገው ግንኙነታቸውን ማጠናከር ጀምረዋል።
በተጨማሪም ለሁለት ዓመታት በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ተሰልፈው መሳተፋቸው ይታወቃል።
አቶ ነገራ ጦርነቱ በፕሪቶሪያው ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ከምዕራባዊያን በተለይም ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙት እያጠናከረ ይመስላል ይላሉ።
ይህ ደግሞ ኤርትራ ሌላ አማራጭ እንድታይ አድርጓታል።
“አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን ካጠናከረች እኔም አማራጭ አለኝ” በማለት ወደ እነዚህ አገሮች [ቻይና እና ሩሲያ] እንደሄደች ተናግረዋል።
ለአቡ ሓሽም የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት በመንግሥታቱ ተገዢነት የሚወሰን ነው።
“በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ነጻ የሆነ ፖሊሲ ሊከተል ያሰበ ይመስላል። እስካሁን እንደዚያ ያለ ሁኔታን ነው እያሳየ የቆየው። ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከአሜሪካ ጋር በጣም ጥሩ ግንኙነት እያላቸው ነበር ከቻይና ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊመሠርቱ የቻሉት” ሲሉ ይገልጻሉ።
አሁንም ተመሳሳይ ነጻ የሆነ ፖሊሲ ከተከተሉ ብዙ ተጽዕኖ እንደማይኖር ያምናሉ።
“እንደ ክላያንት ስቴት (ቅጥረኛ አገር) ከሆኑ ግን [የሚደግፏቸውን አገራት] ፍላጎት ለማስጠበቅ ሲባል እንደፈለጉ ወደ ጦርነት ሊከቷቸው ይችላሉ” ሲሉ አብዱራህማን ሰይድ አቡ ሓሽም አጠቃልለዋል።