ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሩሲያ “ታሪካዊ ኃላፊነቷን” እንድትወጣ ፕሬዝዳንት ፑቲንን ጠየቁ
በሩሲያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሩሲያ “ታሪካዊ ኃላፊነቷን” እንድትወጣ መጠየቃቸውን የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ገለጸ።
ለአራት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ሞስኮ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ረቡዕ ዕለት በተገናኙበት ወቅት ነው ይህንን ሃሳብ የሰነዘሩት።
ሩሲያ ዓለም አቀፋዊ ሰላም እና ፍትሕን በማስፈን በኩል ያለባትን ታሪካዊ ኃላፊነት እንድትወጣ ነው ለፕሬዝዳንት ፑቲን ጥሪያቸውን ያቀረቡት።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጨምረውም በአሜሪካ የበላይነት በአንድ ኃይል እየተመራ ያለው የዓለም ሥርዓት፣ በዓለም ዙሪያ “ለተስፋፋው ቀውስ እና ውድመት” አስተዋጽኦ አድርጓል ማለታቸውም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው ጋር ለይፋዊ ጉብኝት ማክሰኞ ዕለት ወደ ሞስኮው ያመሩት በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግብዣ መሆኑ ተዘግቧል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ በቻይና ለቀናት የቆየ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ወደ አገራቸው ከተመለሱ ከቀናት በኋላ ነው ወደ ሩሲያ ያመሩት።
ባለፉት ዓመታት በሩሲያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፣ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀረበውን ሩሲያን የሚያወግዝ የውሳኔ ሃሳብ ከተቃወሙት ጥቂት አገራት መካከል ኤርትራ አንዷ ናት።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራትም ሩሲያን ከማውገዝ ተቆጥበው ድምጸ ተዕቅቦ ታድረጋቸው ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት 32ኛ የነጻነት በዓሏን ያከበረችው ኤርትራ ባለፉት ዓመታት ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት መልካም የሚባል አይደለም።
ምዕራባውያኑም በአካባቢው በሚከሰቱ ግጭቶች ውስጥ ኤርትራ ሚና አላት ከማለት በተጨማሪ በአገሪቱ ውስጥ በዜጎቿ ላይ ጭቆናን ትፈጽማለች በሚል ይወቅሷታል።
ኤርትራ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች ሲሆን፣ የፕሬዝዳንት ኢሳያስም ጉብኝት የዚህ ማሳያ ነው።
ፕሬዝዳንቱ በቻይና ካደረጉት እንዲሁም አሁን በሩሲያ እያደረጉት ካለው ጉብኝት ቀደም ብሎ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኤርትራ ይፋዊ ጉብኝት አካሂደው ነበር።
ከወራት በፊት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ እናዲሁም የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በኤርትራ ጉብኝት አድርገው ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።