ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኃያላን የሚፎካከሩበት የአፍሪካ ቀንድ አገራት ትብብር የት ድረስ ይዘልቃል?
ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን ያካተተው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በአህጉሪቱ ውስጥ እንዲሁም በዓለም ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ ወሳኝ ሚና ያለው ስፍራ ነው።
የአፍሪካ ቀንድ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ነዳጅ እና ከእስያ ደግሞ ወሳኝ የኢንዱስትሪ ምርቶች ሰፊ ተጠቃሚ ወዳለባቸው የአውሮፓ እንዲሁም የአሜሪካ አህጉር የሚተላለፍበት ቁልፉ የቀይ ባሕር መተላለፊያ ያለበት ስፍራ ነው።
በዚህም የተነሳ ባለፉት ዘመናት እና በአሁኑ ወቅት ኃያላን አገራት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካሉ አገራት ጋር ወዳጅነትን በመመስረት ተጽእኗቸውን እና ቁጥጥራቸውን ማጠናከር ይፈልጋሉ።
በዚህም የተነሳ አካባቢው የኃያላን እና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚፈልጉ አገራት የትግል ሜዳ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ደግሞ በአካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች እንዲካሄዱበት በር ከፍቷል።
ያም ሆኖ የአካባቢው አገራት በተለያዩ ጊዜያት ትብብራቸውን ለማጠናከር ሲጥሩ፣ የምዕራቡ እና የምሥራቁ ኃያላን ደግሞ በሁሉም አማራጭ በአካባቢው ያላቸውን ተቀባይነት እና ጥቅም ለማስከበር ሲፎካከሩ ቆይተዋል።
የኃያላኑ ዐይን በአፍሪካ ቀንድ ላይ
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአፍሪካ ቀንድ አገራት እንዲሁም ምዕራባውያኑ፣ ቱጃሮቹ የአረብ አገራት፣ ቱርክ፣ ሩሲያ እና ቻይና በአካባቢው በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የተጽእኖ ስፍራ ለመያዝ የቻሉትን ሲያደርጉ ነበር።
ግጭት እና የፀጥታ ስጋት የማይለየው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ እና በዓለም አቀፋዊ ተጽእኖዎች እንደሚናጥ የሚገልጹት የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኙ አሰይድ አብዱራህማን አቡሃሺም፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ወገኖች እየተካሄዱ ያሉትን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎችን እንደማሳያ ይጠቅሳሉ።
በተለይ በኤርትራ፣ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በሶማሊያ በኩል የሚካሄዱ ተደጋጋሚ ቀጠናዊ ግንኙነቶች እንዲሁም የአሜሪካ፣ የቻይና እና የሩሲያ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች እንዲሁም ባለሥልጣናት ወደ አፍሪካ ቀንድ አገራት በተደጋጋሚ መመላለሳቸውን ያነሳሉ።
ከሰሞኑም የአፍሪካ ቀንድ መሪዎች ፣ሰኞ ዕለት፣ በአንድ ቀን ውስጥ ያደረጓቸው ቀጠናዊ እንቅስቃሴዎች ትኩረትን ስበዋል። በዚህም ዋነኞቹ የአፍሪካ ቀንድ መሪዎች በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ተገናኝተው በአገራቱ እና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተነግሯል።
በፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኘው ሱዳን ም/ፕሬዝዳንት ሌ/ጄኔራል ሃምዳን ዳጋሎ ወደ ኤርትራ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ደቡብ ሱዳን እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ደግሞ ወደ አሥመራ አቅንተው ነበር።
እነዚህ የአካባቢው አገራት ጉብኝቶች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በየአገራቱ እና በአካባቢው ባሉ ፖለቲካዊ እና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውን በየአገራቱ ካሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች መገንዘብ ይቻላል።
እነዚህ ቀጠናዊ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ባሉበት ወቅት የአፍሪካ ቀንድ እንደ አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይና ካሉ ታላላቅ ኃያላን አገሮች ትኩረት ነጻ አልነበረም።
ባለፉት ወራት የሩሲያ፣ የቻይና እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ በተደጋጋሚ ጉብኝት አድርገዋል።
የኃያላኑ ፉክክር
ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ በአፍሪካ ውስጥ ያላት ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተጽእኖ ሰፍቶ የቆየው አሜሪካ “በአሁኑ ወቅት በተለይ በቻይና እና በሩሲያ እየተፈተነ ነው” ይላሉ አሰይድ አብዱራህማን።
በተለይ ባለፉት ጥቂት አስርታት ውስጥ በዓለም መድረክ ኃያልነቷ እየጎላ የመጣው ቻይና ከወታደራዊ እና ከፀጥታ ጉዳዮች በተለየ፣ የአፍሪካ አገራት በዋናነት በሚሹት የመሠረተ ልማት ግንባታ እና የምጣኔ ሃብት ልማት በኩል ትስስሯን ያጠናከረችው ቻይና ለአሜሪካ ስጋት ሆናለች ይላሉ።
ጨምረውም ቻይና ምጣኔ ሃብታዊውን ትስስሩን ቅድሚያ ሰጥታ እየመጣች ነው፤ “ነገር ግን የቻይና በቀጠናው መገኘት ከኢኮኖሚ ይጀምር እንጂ ውሎ አድሮ ወደ ወታደራዊው መስክ መሸጋገሩ ስለማይቀር ለአሜሪካ ትልቅ ስጋት ነው።”
አሜሪካ በአፍሪካ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ እያደረገችው ያለው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ደግሞ እየጨመረ የመጣውን የሩሲያ እና የቻይናን ተፅዕኖ ለማክሸፍ ያለመ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አቡሃሺም ይገልጻሉ።
የቀጠናው አገራት ትስስር
የአፍሪካ ቀንድ አገራት ካለባቸው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የምጣኔ ሃብት ቀውስ፣ የጦርነት እና የፀጥታ ችግር አንጻር በተለያዩ ጊዜያት ትስስራቸውን ለማጠናከር ሞክረዋል። ለዚህም ኢጋድ ተጠቃሹ የጋራ ተቋማቸው ሆኖ ቆይቷል።
ከዚህ በሻገርም ከወቅታዊ ተግዳሮቶቻቸው እና ፍላጎቶቻቸው አንጻር የአካባቢው አገራት የሁለትዮሽ እና ከዚያም በላይ የሆኑ ጥምረቶችን ሲመሠርቱ ቆይተዋል።
አገራቱ አንድ ላይ በመሆን በጋራ መቆም ካልቻሉ በቀጠናው እና በዓለም አቀፍ መድረክ ደካማ ሊሆኑ እንደሚችሉ “የአፍሪካ ቀንድ አገራት የገባቸው ይመስላሉ ማለት እንችላለን” ይላሉ አቡ ሃሺም።
ይህ ኢኮኖሚያዊ ስበት ያለው እና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ የሚኖርበት ቀጠና፣ ከስትራቴጂ አንጻር የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በጋራ ለመሥራት ከጥቂት ዓመታት በፊት ጥብቅ ግንኙነት መሥርተው እንደነበር ይታወሳል።
“ነገር ግን ይህ ጥምረት ሁለት ችግሮች ገጥሞታል” የሚሉት አቡ ሃሺም “የመጀመሪያው ትብብሩ በአካባቢው ፍላጎት ካላቸው ከውጭ ኃይሎች ጥቅም አንጻር ሊታይ አልቻለም” ይላሉ።
ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥቅምን አገናዝቦ ያልተነሳ አጋርነት ተቃውሞ እንደሚገጥመው የሚጠቅሱት ተንታኙ፣ ከዚህ አኳያም በቀጠናው ውስጥ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ግብፅ እና አሜሪካ ጥቅማቸውን የሚቃረን መስሎ ከታያቸው መቃወማቸው አይቀርም።
“ስለዚህም ግንኙነቶች ግልጽ ሊሆን፣ ከቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፍላጎቶች እንዲሁም አመለካከቶች ጋር የተቃኙ ሊሆኑ ይገባል።”
ሁለተኛው ችግር የሦስትዮሽ ግንኙነቱ ድክመት ከአገሮቹ ውስጣዊ መዋቅራዊ ድክመቶች የመነጨ እንደሆነ አቡሃሺም ያስረዳሉ።
“የእነዚህ ሦስት አገራት መንግሥታት ለምሳሌ ሕዝብን የሚወክሉ፣ ሰፊ ዴሞክራሲያዊ መድረክን የፈጠሩ እና ተቀባይነት ያላቸው ጠንካራ መንግሥታት አይደሉም።”
የአገራቱ ተግዳሮት
ኤርትራ በአንድ ፓርቲ እና መሪ ጥብቅ ቁጥጥር መሆኗ፣ ኢትዮጵያም በውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ እና በግጭት የምትናጥ እንዲሁም ሶማሊያ በአልሻባብ ጥቃት እና በክልላዊ የፖለቲካ ፉክክር ስር የሚንገዳገድ መንግሥት ያላት መሆኑ አገራቱ የየራሳቸው ተግዳሮት ያለባቸው ናቸው።
“አገራት ውስጣዊ ችግሮቻቸውን ሳይፈቱ እና ሳይጠናከሩ የሚፈጥሩት ማንኛውም ጥምረት ጊዜያዊ ካልሆነ በስተቀር ጠንካራ፣ ዘላቂ እና ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ስለዚህም የቀጠናዊ ጥምረት ኃይል ከውስጣዊ ጥንካሬ የሚመነጭ ነው” ይላሉ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን በቅርበት የሚከታተሉት ተንታኝ።
ነገር ግን የአካባቢው አገራት በተለያየ መስኩ የየራሳቸው ጥንካሬ እና ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የሚጠቅሱት አቡ ሃሽም ኤርትራን በምሳሌነት ያነሳሉ።
“ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ደካማዋ አገር ብትሆንም፣ በተለይ በቀጠናው ያላት ሚና እና ተፅዕኖ ግን እንደቀላል የሚታይ አይደለም። ኤርትራን በአፍሪካ ቀንድ እንደ ዋና ተዋናይ በመሆን በአሜሪካም ይሁን በሩሲያ ወይም በቻይና ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት ፍላጎት አላት።”
በተቃራኒው ደግሞ ኤርትራ ወደ ወታደራዊ ካምፕነት ተቀይራ ደካማ አገር ሆና ቀጣይነት ያለው ተፅዕኖ መፍጠር እንደማትችል በመጥቀስ፣ የሕዝብ ብዛት ማነስ፣ ደካማ ኢኮኖሚ፣ ደካማ አስተዳደር እና የመንግሥት ተቋማት ያሉት አገር ተፅዕኖ መፍጠር አዳጋች እንደሚሆንበት ያነሳሉ።
ቢሆንም ግን በአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል ቢያንስ ግንኙነት እና ውይይት እና ትብብር ለመፍጠር ፍላጎት መኖሩ እንደ አንድ አወንታዊ ነጥብ ሊወሰድ ይችላል ሲሉ አቡ ሃሽም ይናገራሉ።
ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ትብብር
ይህ ሁኔታም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባሉ አገራት መካከል እና በአገራቱ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ተጨማሪ ፖለቲካዊ ውጥረቶችን እና ግጭቶችን ለማርገብ ማገልገሉንም ያመለክታሉ።
ለዚህም በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስን ለመፍታት በአካባቢው አገራት የሚደረገው፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ወደ ግጭት እንዳያመራ የሚደረጉ ግንኙነቶች አብነቶች ናቸው።
“በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው አሳሳቢ ፍጥጫ ወደ ጦርነት አለመግባቱ መልካም ነገር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የጉዳዩን ታሪካዊ ዳራ በመረዳት፣ የሦስተኛ አገር እጅ እየገባበት እንደሆነ በመረዳት ያሳየው ትዕግስት ውጤት” መሆኑንም ጠቅሰዋል አቡ ሃሽም።
የአፍሪካ ቀንድ አገራት በዲፕሎማሲ እና በወታደራዊው መስክም በጋራ አብረው የመሰለፍ ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል። ለዚህም የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግሥትን ከአል ሻባብ ለመከላከል ቀደሚ ድርሻ የነበራት ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ሠራዊታቸውን በአገሪቱ ውስጥ አሰማርተዋል።
በተጨማሪም ምንም እንኳን በርካታ ጥያቄዎች ሲነሱበት ቢቆይም ኤርትራ በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮችን በማሰልጠን በአልሻባብ ላይ ዘመቻ የከፈተውን የሶማሊያን መንግሥት መደገፏ ሲነገር ቆይቷል።
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት የቀጠናው አገራት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሚና እንደነበራቸው የተለያዩ አገራት እና ተቋማት ሲናገሩ ቆይተዋል።
ኤርትራ ከፍተኛ መጠን ያለውን ሠራዊቷን አሰማርታ የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት ጋር ገብቶበት የነበረውን ጦርነት ደግፋለች።
ይኹን አንጂ የአፍሪካ ቀንድ አገራት በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ እና በወታደራዊ መስኩ በተናጠል ከሚቀራረቡት ጋር ሲደጋገፉ እና አብረው ሲቆሙ ቢታዩም ጠንካራ እና ዘላቂ የትብብር ማዕቀፍ ግን ለማዳበር አልቻሉም።
በዚህም የተነሳ የተለያዩ የዓለም ኃያላን ከፍላጎታቸው አንጻር ወደ ሚፈልጉት አቅጣጫ እየጎተቷቸው እንዲሁም ጫና እያሳደሩባቸው ይገኛሉ።