የኖቤል የሰላም ሽልማት ውሳኔ- ትራምፕ የተመኙትን ያገኙ ይሆን?

እንደ አውሮፓውያኑ ከ1901 ጀምሮ በየዓመቱ በሚስጥር ይሰበሰባሉ። ሲወያዩም ለማንም አያሳውቁም፤ ጋዜጠኞች የመጨረሻ ስብሰባቸውን እንዲያዩ አይፈቅዱም፤ይህ ባህል እስካሁን ድረስ እንደቀጠለ ነው።

የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ አባላት፣የዓለማችን እጅግ የተከበረ ሽልማት ጠባቂዎች፣ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ለማን እንደሰጡ አርብ ዕለትይፋ ያደርጋሉ።

ቢቢሲ ከኖርዌይ ብሔራዊ ብሮድካስቲንግ ጋር በመሆን የኮሚቴው አባላት ምርጫቸውን ለማድረግ በተሰበሰቡበት ወቅት የመመልከት ዕድል አግኝቷል።

በሽልማቱ የ125 ዓመታት ታሪክ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ሂደቱን ከመጋረጃ ጀርባ እንዲመለከቱ ሲፈቀድላቸው ይህ የመጀመሪያው ነው።

አምስቱ አባላት እና ፀሃፊው ከመጀመርያው የኖቤል ሽልማት ጀምሮ የሚገናኙት በመብራት በተንቆጠቆጠ እና በጥንታዊ የቤት ቁሳቁሶች በደረጀው የኦስሎ የኖቤል ተቋም የኮሚቴ ክፍል ውስጥ ነው።

የክፍሉ ግድግዳ እያንዳንዱ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ምስል ተሰቅሎበታል።

መጨረሻ ላይ ደግሞ የዚህ ዓመት አሸናፊ ፎቶግራፍ የሚሰቀልበት ቦታ ተትቶለታል።

የዳይናማይት ፈጣሪ እና የሽልማቱ ጠባቂ የሆነው አልፍሬድ ኖቤል ምስል የተሰቀለበት ስር ኮሚቴው አሸናፊው ከመግለፁ አራት ቀናት ቀደም ብሎ ሰኞ ጠዋት ተሰብስበዋል።

ቡና እና ጣፋጭ ነገሮችን ከቀማመሱ በኋላ ለወራት በምርጫ ሂደት ውስጥ ያለፈውን የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ዕጩ ለመለየት ውይይታቸውን ይጀምራሉ።

የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ጆርጅን ዋትነ ፍሬድነስ "እንወያያለን፤እንከራከራለን፤ ከፍተኛ ሙግት አለ። ግን ደግሞ እንደ ሰለጠነ ማኅበረሰብ በየዓመቱ የጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመድረስ እንሞክራለን" ብለዋል።

እአአ ከ1895 ጀምሮ በኖቤል ኑዛዜ ላይ የተቀመጠውን የሽልማቱን መስፈርት ጮክ ብለው አነበቡ።

በዜጎች መካከል ያለውን ወንድማማችነት ለመጠበቅ፣ የጦር ሠራዊቶች እርምጃ ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ፣ ወይም የሰላም መስፋፋትን ለማካሄድ ወይም ለማበረታታት ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ ሁሉ እንዲሰጥ ይላል የኑዛዜው ቃል።

ከዚያ ጋዜጠኞች ወጥተው በሩ ተዘጋ።

የውሳኔ ጊዜ ነው። እና እጩ ሆነው ከቀረቡት ሁሉ የአንድ ሰው ምስል ጎልቶ ይታያል፤ ዶናልድ ትራምፕ።

እኚህ የዓለማችን ኃያል ሰው ይህንን የዓለም እጅግ የተከበረ ሽልማት ይፈልጋሉ። ከዚህ ሽልማት ጋር የሙጢኝ ያሉ ይመስላል።

በንግግሮቻቸው እና በጋዜጣዊ መግለጫዎቻቸው ላይ በተደጋጋሚ ሰባት ጦርነቶች አስቀርቻለሁ ሲሉ ይዘረዝራሉ።

ሽልማቱ ይገባኛል እና "ሁሉም ሰው ማግኘት አለብኝ ይላል" እያለ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ነገር ግን ባለፈው ወር በቨርጂኒያ ለተሰባሰቡ የአሜሪካ ወታደሮች "ለሆነ እርባና ያለው ነገር ላልሰራ ሰው ይሰጡታል። ስለ ዶናልድ ትራምፕ አእምሮ መጽሐፍ ለጻፈው ሰው ይሰጣሉ ... ለአገራችን ይህ ትልቅ ስድብ ይሆናል።"

የዓለም መሪዎች የኖቤል ሽልማት እንደሚገባቸው በመናገር ወደ ልባቸው መቅረብ እንደሚቻል የተገነዘቡ ይመስላል።

የእስራኤሉ ቤንያሚን ኔታንያሁ በዋይት ሐውስ የእጩነት ደብዳቤውን በአደባባይ አሳይተዋል። የአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ለትራምፕ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ሽልማቱ ይገባቸዋል ብለዋል ። የፓኪስታን መንግሥት በእጩነት መምረጡን አስታውቆ፣ የፕሬዚዳንቱን ምስጋናዎች አግኝቷል።

የራሳቸው የካቢኔ ባልደረቦችም ይህንን መንገድ መከተል መርጠዋል።

ጋዜጠኞች ባሉበት ዋና መልዕክተኛቸው የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ ምኞታቸው የኖቤል ኮሚቴ ትራምፕ በሽልማቱ ታሪክ ውስጥ "አንድ ምርጥ እጩ" መሆናቸውን እንዲያውቅ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጆርገን ዋትኔ ፍራይድነስ ባለው የሕዝብ ግፊት ያልተደናገጠ ይመስላል።

"በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ደብዳቤዎች፣ ኢሜይሎች፣ጥያቄዎች፣ 'ይህ ነው መምረጥ ያለባችሁ' የሚሉ ጥያቄዎች እንቀበላለን። ስለዚህ ያንን ዘመቻ ለማድረግ፣ ግፊቱ… በእውነት አዲስ ነገር አይደለም" ብሏል።

ነገር ግን በዚህ ዓመት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የመጡ ጠንካራ ውትወታዎችን እንዳላዩ ማለፍ እንደማይቻል ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ተናግሯል።

"ዓለም እየሰማን እንደሆነ ይሰማናል፣ ዓለምም እየተወያየ ነው፣ እናም ሰላም እንዴት ማግኘት እንደምንችል መወያየቱ ጥሩ ነገር ነው። እናም በምርጫችን ጠንካራ እና በመርህ ላይ የተመሰረተ መሆን አለብን... ያ ሥራችን ነው።"

የኖርዌይ ኮሚቴ የሚሾመው በአገሪቱ ፓርላማ ነው። እና አባላቶቹ - ብዙ ጊዜ ጡረታ የወጡ የፓርላማ አባላት ናቸው።

ነፃነታቸውን አጥብቀው የያዙ እና ብዙዎቹ ጥብቅ አመለካከቶች አላቸው።

ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚያበረታታ ማህበር ቅርንጫፍን በኖርዌይ የሚመሩት ፍሬድነስ ከዚህ ቀደም ትራምፕን "በዲሞክራሲያዊ አገራት ውስጥ እንኳን" ነጻነትን ይጋፋሉ ሲሉ ተችተዋቸው ያውቃሉ።

የኖርዌይ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የዩኤስ ፕሬዝዳንት የቀድሞው የኔቶ ኃላፊ እና አሁን ደግሞ የኖርዌይ የገንዘብ ሚንስትር ለሆኑት ጄንስ ስቶልተንበርግን ስልክ ደውለው ስለ ሽልማቱ አውርተዋቸው ነበር።

እናም ትራምፕ ካላሸነፉ አገሪቱን ሊነቅፉ ይችላሉ ወይ የሚለው ግልፅ መወያያ ሆኗል።

እአአ በ2010 የቻይናው ተቃዋሚ ሊዩ ዚያኦቦ ሽልማቱን ሲያገኙ፣ ቤዢንግ ከኦስሎ ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጣ ለስድስት ዓመታት የዘለቀ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥላ ታውቃለች።

ስለዚህ የአሜሪካ ዋልታ ረገጥ ፕሬዝዳንት ሊያሸንፉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል?

በእርግጥ ትራምፕ በአገር ውስጥ እና በውጭ ደጋፊዎቹ አሏቸው።

ነገር ግን ስለ ሰላም የሚሰራው ፕሪዮ ዳይሬክተር ኒና ግሬገር፣ የማሸነፍ ዕድሉ ትንሽ ነው ይላሉ።

"የትራምፕ አስተዳደር እንደ የዓለም ጤና ድርጅት እና የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነቶች ካሉ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ራሱን አግልሏል። እናም ትራምፕ ግሪንላንድን ከዴንማርክ ለመውሰድ ያላቸውን ፍላጎት ከተመለከትክ ይህ ስለ ዓለም አቀፍ ትብብር አይናገርም።"

ለትራምፕ እንቅፋት የሚሆነው ሌላው በዚህ ዓመት ለሽልማቱ እጩዎች ሆነው የቀረቡት 338 ዕጩዎች ናቸው።

የመጠቆሚያ ጊዜው በጥር ወር መጨረሻ ላይ የተዘጋ ሲሆን ይህም ኮሚቴው እንዲገመግም ጊዜ ለመስጠት ነው። ፕሬዚዳንቱ ወደ ቢሮ የተመለሱት በዚያ ወር ብቻ ነበር።

ነገር ግን ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ያቀረቡት እና እስራኤል እና ሐማስ በመጀመርያው ምዕራፍ ላይ የተስማሙበት የጋዛ የሰላም ዕቅዳቸው እውን ከሆነ እና ከቀጠለ ግሬገር በሚቀጥለው ዓመት ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ያምናሉ።

"ያኔ ወደ እሱ አቅጣጫ አለመመልከት አስቸጋሪ ይመስለኛል" ብለዋል።

ይህ ሁሉ በኦስሎ ዩኒቨርሲቲ በጦርነት፣በሰላም እና በኖቤል ሽልማት ላይ በሚሰጠው ኮርስ ላይ ሰፊ ክርክር እንዲካሄድበት አድርጓል።

ሁለተኛ ዲግሪውን እየተማረ የሚገኘው ታኖስ ማሪዚስ በዩኒቨርሲቲው ቤተመጻሕፍት ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር ተቀምጦ ሳለ "ከአሸናፊዎች ጋር የሚያያዝ የክብር እና ትህትና አለ" ብሏል።

"ሽልማቱ የሰው ልጅን ከመጥቀም አንፃር ለሰላም ፍለጋ የሚሰጥ እውቅና እንጂ ራስን ለመጥቀም አይደለም" ሲልም ያክላል።

የ21 ዓመቷ ካትሊን ራይት ደግሞ "ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋለጡ እና ይህንን ሽልማት የተሰጣቸውን ሰዎች ማየት፣ በታሊባን በጥይት የተመታችው ማላላ ዮሳፍዛይን የመሰሉ፣ እና ከዚያ ደግሞ በራስ ፍቅር ወድቀህ እና ጓደኞችህ ለኮሚቴው ሲደውሉ የሚያስቅ ነው ብዬ የማስበው፣ ንቀት ነው" ስትል ተናግራለች።

የሽልማቱ ዋና ነገር ብዙም ያልታወቁ ሰዎችን ወይም ድርጅቶችን ወሳኝ ሥራዎችን ማክበር እንደሆነ ታምናለች። "ለሰላም ሲሰራ፣ በታዋቂ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በትናንሽ ቡድኖች ይጀምራል፤ እና ይህ ማክበር አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ።"

ብዙ የዓለም መሪዎች በእርግጥ ከተሸላሚዎቹ መካከል ናቸው። በኖቤል ኮሚቴ ክፍል ግድግዳ ላይ ባራክ ኦባማን ጨምሮ ያሸነፉት አራት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ፎቶ ተሰቅሏል።

"ኦባማ ብባል ኖሮ የኖቤል ሽልማት በአስር ሰከንድ ውስጥ ይሰጠኝ ነበር" ሲሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቅሬታቸውን ገልጸው ያውቃሉ።

እነዚያ ግድግዳዎች እአአ ከ1901 ጀምሮ ተሸላሚዎቹ ስላለፉባቸው ብዙ ጉዳዮች ይመሰክራሉ። ጦርነቶች፣ አፓርታይድ፣ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች፣ የአየር ንብረት ለውጥ።

ዘንድሮ ከዋይት ሐውስ በሚደረገው ዘመቻ በተወሰነ ደረጃ ሊደበዝዝ ይችላል።

ነገር ግን ዶናልድ ትራምፕ ከዚያ የኮሚቴው በር ጀርባ ምን እንደተፈጠረ፣ ማንን እንደመረጠ እና ማን እንደተቃወመ ለማወቅ ከፈለጉ ችግር ይገጥማቸዋል።

ሰነዶቹ ለ50 ዓመታት በሚስጥር ተይዘው ይቆያሉ።