ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ190 ሰዎችን አስክሬን የደበቀው ቀብር አስፈጻሚ 950 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ታዘዘ
በአሜሪካ፣ ኮሎራዶ ግዛት የ190 ሰዎችን አስክሬን ከቤተሰቦቻቸው ደብቆ ያስቀመጠው ቀብር አስፈጻሚ ተቋም ለሟች ቤተሰቦች 950 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ታዘዘ።
ቀብር አስፈጻሚው ተቋም የሰዎቹን አስክሬን ከደበቀ በኋላ ለቤተሰቦቻቸው ሐሰተኛ የተቃጠለ አስክሬን አመድ ሰጥቷል።
እነዚህ ቤተሰቦች የተረከቡት አመድ የሟች ቤተሰቦቻቸው እንደሆነ አምነው ተቀብለው ነበር።
‘ሪተርን ቱ ኔቸር’ የተባለው ቀብር አስፈጻሚ ለቤተሰቦቹ ካሳ እንዲከፍል በዳኛ ውሳኔ ተላልፏል።
የቀብር አስፈጻሚው ባለቤቶች የሆኑት ጥንዶች ጆን ሀልፎርድ እና ካሪ ሀልፎርድ ግን የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ስለገቡ ይህን ካሳ መክፈላቸው ያጠራጥራል።
ባልየው አሁንም በቁጥጥር ሥር ሲሆኑ ሚስታቸው በዋስ ተለቀዋል።
የልጇን አስክሬን አቃጥለው አመዱን እንዲሰጧት በሚል እአአ በ2019 የቀጠረቻቸው ክርስቲና ፔጅ “ምንም ገንዘብ እንደማይሰጡኝ አውቃለሁ። በጣም ያበሳጫል” ብላለች።
ለአራት ዓመታት ያህል የልጇ አስክሬን ተቃጥሎ አመዱ እንደተሰጣት ነበር የምታምነው። የልጇ አስክሬን ግን በቀብር አስፈጻሚ ተቋሙ ውስጥ በስብሶ ተገኝቷል።
የቀብር አስፈጻሚው ባለቤት የሆኑት ጥንዶች ፍርድ ቤት ውሳኔውን ሲያስተላልፍ አለመገኘታቸውም ተጎጂዎችን አስቆጥቷል።
ተጎጂዎቹን የወከለው ጠበቃ አንድሪው ስዋን ለአሶሽየትድ ፕረስ እንዳለው፣ ጥንዶቹ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ መሆናቸው ቢታወቅም ደንበኞቹ አንዳች ምላሽ ይሻሉ።
“ጥንዶቹን ምስክር አድርጌ ባቀርባቸው ደስ ይለኝ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አስክሬን ነው የደበቁት። ለምን ይሄንን እንዳደረጉ እንዲናገሩ እፈልግ ነበር” ብሏል።
ከ100 በላይ ቤተሰቦች በክሱ ተካተዋል። ሌሎች ተጎጂ ቤተሰቦችም ክሱን እንዲቀላቀሉ ክፍት ተደርጓል።
ጥንዶቹ በኮሎራዶና በፌደራል ደረጃም በመቶዎች የሚቆጠሩ ክሶች ይጠብቋቸዋል። የሰዎችን አስክሬን ማንገላታት፣ ዝርፊያ፣ ማስመሰል እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ከክሶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ጥፋተኛ መሆናቸውን እንዲያምኑ እንደተጠየቁ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል። ይህ ከምን እንደደረሰ ግን ግልጽ አይደለም።
ቀብር አስፈጻሚ ተቋሙ እሰጣለው ያለው አገልግሎት የሰዎች አስክሬን ምንም ንጥረ ነገር ሳይታከልበት በተፈጥሯዊ መንገድ መበስበስ በሚችልበት ሬሳ ሳጥን መቅበር ነው።
በተቋሙ መጥፎ ሽታ ያስተዋሉ ሰዎች ጥቆማ አድርገው ነበር ምርመራ የተጀመረው። 115 አስክሬኖችም ተገኝተዋል።
እንዲህ ዓይነት ተፈጥሯዊ የአቀባበር ሥርዓቶች በኮሎራዶ የሚፈቀዱ ቢሆንም፣ ሰዎች በ24 ሰዓት ውስጥ እንዲቀበሩ ሕጉ ያዛል።
የሰዎችን አስክሬን በማጥናት ዲግሪ ያለው ወይም ሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀ ሰው ቀብር ማስፈጸሚያ እንዲከፍት ይፈቀዳል።
ጥንዶቹ የሰዎችን አስክሬን መደበቃቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ግን በኮሎራዶ ጥብቅ ሕግ እንዲወጣ ተወስኗል። ሕጉ የሚተገበረው እአአ በ2026 ይሆናል።